የፈርዖን የታወከ እንቅልፍ
ፈርዖን ማንም ሊፈታው ያልቻለውን የላሞችና የእሸት ሕልም አለመ። ዮሴፍ ከጉድጓድ እስር ቤት በችኮላ ወጥቶ መልሱን ለአብ ሰጠ፤ ከዚያም ዕቅድ አቀረበ፤ ለሰባት ዓመት አንድ አምስተኛውን ማከማቸት። በአንድ ጠዋት ከእስረኛነት ወደ ገዢነት ተሸጋገረ።
41 1ሁለት ዓመት ሙሉ ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም አለመ፤ በአባይ ወንዝ አጠገብ ቆሞ ነበር። 2ለምለሞችና የወፈሩ ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ወጥተው በቄጠማው መካከል ይሰማሩ ነበር። 3ከእነርሱም በኋላ መልካቸው የከፋና የከሱ ሌሎች ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ወጥተው በወንዙ ዳር አጠገባቸው ቆሙ። 4መልካቸው የከፋውና የከሱ ላሞች ያማሩትንና የወፈሩትን ሰባቱን ላሞች በሉ፤ ፈርዖንም ከእንቅልፉ ነቃ። 5ዳግመኛ ተኝቶ ሁለተኛ ሕልም አለመ፤ ፍሬ የሞሉና መልካም የሆኑ ሰባት የእህል ዛላዎች በአንድ አገዳ ላይ በቀሉ። 6ከእነርሱም በኋላ ቀጭንና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የእህል ዛላዎች ወጡ። 7ቀጭኖቹ ዛላዎች ሰባቱን ፍሬ የሞሉና የወፈሩ ዛላዎች ዋጧቸው። ፈርዖንም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ሕልም ሆኖ ነበር። 8በማለዳም መንፈሱ ታወከ፤ ልኮ የግብፅን ጠንቋዮች ሁሉና ጠቢባንዋን ሁሉ አስጠራ። ፈርዖንም ሕልሞቹን ነገራቸው፤ ነገር ግን ሊተረጕምለት የሚችል አንድም አልነበረም።
9ከዚያም የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “ዛሬ በደሌ ትዝ አለኝ። 10ፈርዖን በባሪያዎቹ ተቈጥቶ እኔንና የእንጀራ ጋጋሪዎች አለቃን በዘበኞች አለቃ ቤት ውስጥ በእስር አኖረን። 11እኔና እርሱ በአንድ ሌሊት እያንዳንዳችን ሕልም አለምን፤ እያንዳንዱም ሕልም የራሱ ትርጓሜ ነበረው። 12በዚያም የዘበኞች አለቃ ባሪያ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጎልማሳ ከእኛ ጋር ነበር። ሕልማችንን ነገርነው፤ እርሱም ለእያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ተረጐመልን። 13እርሱም እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ሥራዬ ተመለስሁ፤ ሌላውም ተሰቀለ።”
14ፈርዖንም ዮሴፍን አስጠራ፤ ፈጥነውም ከጕድጓድ እስር ቤት አመጡት። ተላጭቶ ልብሱን ቀይሮ ወደ ፈርዖን ቀረበ። 15ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሊተረጕመው የሚችል የሌለ ሕልም አልሜአለሁ፤ አንተ ግን ሕልም በሰማህ ጊዜ ልትተረጕመው እንደምትችል ስለ አንተ ሰምቻለሁ።”
16ዮሴፍም መልሶ፣ “ይህን በራሴ ማድረግ አልችልም፤ አባታችን ለፈርዖን መልካም መልስ ይሰጣል” አለ።
17ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18የወፈሩና ለምለሞች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በቄጠማው መካከል ይሰማሩ ነበር። 19ከእነርሱም በኋላ የከሱ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና ሥጋቸው የቀጨጨ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እንደ እነርሱ ያለ በግብፅ ምድር ሁሉ አይቼ አላውቅም። 20የከሱትና መልካቸው የከፋው ላሞች ፊተኞቹን የወፈሩ ሰባቱን ላሞች በሉ። 21ነገር ግን ከበሏቸው በኋላ እንደ በሏቸው የሚያስታውቅ አልነበረም፤ እንደ ቀድሞው መልካቸው የከፋ ሆነው ነበርና። ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ። 22ደግሞም በሕልሜ ፍሬ የሞሉና መልካም የሆኑ ሰባት የእህል ዛላዎች በአንድ አገዳ ላይ ሲበቅሉ አየሁ። 23ከእነርሱም በኋላ የደረቁ፣ ቀጭኖችና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የእህል ዛላዎች ወጡ። 24ቀጭኖቹ ዛላዎች ሰባቱን መልካም ዛላዎች ዋጧቸው። ለጠንቋዮቹም ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ሊገልጥልኝ የሚችል አንድም አልነበረም።”
25ዮሴፍም ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ሕልሞች አንድ ናቸው፤ አባታችን ሊያደርግ ያለውን ለፈርዖን ገልጦአል። 26ሰባቱ መልካም ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሰባቱ መልካም የእህል ዛላዎችም ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙ አንድ ነው። 27ከእነርሱ በኋላ የወጡት የከሱትና መልካቸው የከፋው ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱትም ሰባቱ ባዶ ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። 28ለፈርዖን የነገርሁት ይህ ነው፤ አባታችን ሊያደርግ ያለውን ለፈርዖን አሳይቶታል። 29በግብፅ ምድር ሁሉ ታላቅ ጥጋብ ያለባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30ከዚያም በኋላ ሰባት የራብ ዓመታት ይከተላሉ፤ በግብፅ የነበረውም ጥጋብ ሁሉ ይረሳል፤ ራቡም ምድሪቱን ይበላታል። 31ከዚያ በኋላ የሚመጣው ራብ እጅግ የጸና ስለሚሆን ጥጋቡ በምድሪቱ ይረሳል። 32ሕልሙ ለፈርዖን ሁለት ጊዜ የተደገመበት ምክንያት አባታችን ነገሩን አጽንቶ ስለ ወሰነውና አባታችንም ፈጥኖ ስለሚፈጽመው ነው።
33እንግዲህ ፈርዖን አስተዋይና ጠቢብ ሰው ይፈልግ፤ በግብፅ ምድርም ላይ ይሹመው። 34ፈርዖን ይህን ያድርግ፤ በምድሪቱ ላይ ተቈጣጣሪዎች ይሹም፤ በሰባቱ የጥጋብ ዓመታትም ከግብፅ ፍሬ አንድ አምስተኛውን ይውሰድ። 35እነዚህን የሚመጡ መልካም ዓመታት ምግብ ሁሉ ይሰብስቡ፤ እህሉንም በፈርዖን እጅ ሥር በከተሞች ውስጥ ለምግብ ያከማቹ፤ ይጠብቁትም። 36ያም ምግብ በግብፅ ምድር ለሚመጡት ሰባት የራብ ዓመታት ለምድሪቱ መጠባበቂያ ይሆናል፤ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም።”
ለሚመጡት ዓመታት ጥበብ የተሞላበት ዕቅድ
37ይህም ነገር ፈርዖንንና ባሪያዎቹን ሁሉ ደስ አሰኘ። 38ፈርዖንም ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፤ “እንደዚህ ያለ ሰው፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን ሰው እናገኝ ይሆንን?” 39ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስላሳየህ፣ እንዳንተ አስተዋይና ጠቢብ ማንም የለም። 40አንተ በቤቴ ላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለትእዛዝህ ይታዘዛሉ፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኑ ብቻ ነው።” 41ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “እነሆ፣ በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾሜሃለሁ” አለው።
42ፈርዖንም የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ በዮሴፍ እጅ ላይ አደረገው፤ ከቀጭን በፍታ የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በአንገቱም ላይ የወርቅ ሐብል አደረገለት። 43ፈርዖን ዮሴፍን በራሱ ሁለተኛ ሰረገላ ላይ አስቀመጠው፤ በፊቱም፣ “ተንበርከኩ!” እያሉ እንዲጮኹ አደረገ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ ላይ ሾመው። 44ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ያለ አንተ ፈቃድ በግብፅ ምድር ሁሉ ማንም እጁን ወይም እግሩን አያነሣም።” 45ፈርዖንም ዮሴፍን ጸፍናት ጳዕናህ ብሎ ሰየመው፤ የኦን ካህን የጲጥፋራ ልጅ አስናትን ሚስት አድርጎ ሰጠው። ዮሴፍም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ወጣ። a a v45 ኦን ትልቅ የግብፅ ከተማና የፀሓይ አምልኮ ማዕከል ነበረች፤ በግሪኮች ዘንድ ሄሊዮፖሊስ ተብላ ትታወቅ ነበር፤ ከዛሬዋ ካይሮ አጠገብ ትገኝ ነበር።
46ዮሴፍም በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ከፈርዖንም ፊት ወጥቶ በግብፅ ምድር ሁሉ ተዘዋወረ። 47በሰባቱ የጥጋብ ዓመታትም ምድሪቱ በእጅጉ አፈራች። 48በግብፅ ውስጥ የነበረውን የሰባቱን ዓመታት ምግብ ሁሉ ሰብስቦ በከተሞች ውስጥ አከማቸ፤ በእያንዳንዱም ከተማ በዙሪያዋ ያሉትን እርሻዎች ምግብ አኖረ። 49ዮሴፍም እንደ ባሕር አሸዋ እጅግ ብዙ እህል አከማቸ፤ ከመቍጠርም እስኪተው ድረስ፣ ስፍር ቍጥር አልነበረውም። 50የራብ ዓመታት ሳይመጡ የኦን ካህን የጲጥፋራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 51ዮሴፍም የበኵር ልጁን ምናሴ ብሎ ሰየመው፤ “አባታችን መከራዬን ሁሉና የአባቴን ቤት ሁሉ አስረስቶኛልና” አለ። b b v51 ምናሴ የሚለው ስም “ማስረሳት” ማለት ነው። 52ሁለተኛውንም ኤፍሬም ብሎ ሰየመው፤ “አባታችን በመከራዬ ምድር ፍሬያማ አድርጎኛልና” አለ። c c v52 ኤፍሬም የሚለው ስም “ፍሬያማ” ማለት ነው።
53በግብፅ ምድር የነበሩት ሰባቱ የጥጋብ ዓመታት አለቁ። 54ዮሴፍም እንደ ተናገረ ሰባቱ የራብ ዓመታት ጀመሩ። ራብም በየአገሩ ሁሉ ሆነ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ግን እንጀራ ነበረ። 55ግብፅ ሁሉ በተራበች ጊዜ ሕዝቡ ስለ እንጀራ ወደ ፈርዖን ጮኹ። ፈርዖንም ግብፃውያንን ሁሉ፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱ፤ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አላቸው። 56ራቡም በምድሪቱ ሁሉ ላይ በተስፋፋ ጊዜ ዮሴፍ ጎተራዎቹን ሁሉ ከፍቶ ለግብፃውያን እህል ሸጠ፤ በግብፅ ራቡ የጸና ነበርና። 57ራቡ ምድርን ሁሉ ስለ ያዘ፣ ምድር ሁሉ ከዮሴፍ እህል ይገዙ ዘንድ ወደ ግብፅ መጡ።