ወግ ከአባታችን ቃል በላይ
ፈሪሳውያን ባልታጠበ እጅ መብላትን ይቃወማሉ፤ ኢየሱስ ወጋቸው የአብ አባታችንን ትእዛዝ እንደሚሽር፣ የሚያረክሰውም ከልብ የሚወጣው እንደ ሆነ ይናገራል። አንዲት ሲሮፊኒቃዊት ሴት ስለ ፍርፋሪ ለተናገረው ጠንካራ ቃል መልስ ትሰጣለች፤ ልጅዋም ነጻ ትወጣለች። ደንቆሮ ሰው ይሰማል።
7 1ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በኢየሱስ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ 2ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ርኩስ በሆነ እጅ፣ ይኸውም ባልታጠበ እጅ፣ እንጀራ ሲበሉ አዩ። 3(ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የሽማግሌዎችን ወግ ጠብቀው እጃቸውን አጥብቀው ካልታጠቡ በቀር አይበሉምና። 4ከገበያ በመጡ ጊዜ ሳይታጠቡ አይበሉም። ጽዋዎችን፣ ማድጋዎችንና የናስ ዕቃዎችን ማጠብ የመሳሰሉ የተቀበሏቸውን ሌሎች ብዙ ወጎችም ይጠብቃሉ።)። 5ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ ሳይከተሉ በርኩስ እጅ እንጀራ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
6እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ በእውነት ትንቢት ተናግሯል፤ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው።’ 7‘በከንቱ ያመልኩኛል፤ የሰውን ትእዛዛት እንደ ትምህርት እያስተማሩ።’
8የአባታችንን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ ትይዛላችሁ።” 9እንዲህም አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ትጠብቁ ዘንድ የአባታችንን ትእዛዝ እጅግ ጥሩ አድርጋችሁ ትሽራላችሁ!” 10ሙሴ፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤’ ደግሞም፣ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ይገደል፤’ ብሏልና። 11“እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፤ ማንም ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ‘ከእኔ የምታገኘው ጥቅም ሁሉ ቍርባን ነው’ (ይኸውም ለአባታችን የተሰጠ መባ ነው) ቢል፣ a a v11 ቍርባን ገንዘብን ወይም ንብረትን ለቤተ መቅደስ የመስጠት ስእለት ነበር፤ ይህም ለሌላ ለማንኛውም ዐላማ—ለገዛ ወላጆችን ለመንከባከብ እንኳ—እንዳይውል ያደርገዋል። 12ከዚያ ወዲያ ለአባቱ ወይም ለእናቱ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። 13እናንተም ካስተላለፋችሁት ወጋችሁ የተነሣ የአባታችንን ቃል ትሽራላችሁ። እንደዚህ ያለ ብዙ ነገርም ታደርጋላችሁ።”
14ሕዝቡንም እንደገና ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም እኔን ስሙኝ፤ አስተውሉም፦ 15ከሰው ውጭ ያለ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም፤ ነገር ግን ከሰው የሚወጣው ነው የሚያረክሰው።” b b v15 ቀደምት ቅጂዎች እዚህ ላይ ቍጥር 16 የላቸውም፤ የኋለኞቹ ቅጂዎች ግን፣ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ሰው ይስማ” የሚለውን ይጨምራሉ።
17ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት።
18እንዲህም አላቸው፤ “እናንተም እንዲህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ምንም ነገር ሊያረክሰው እንደማይችል አታስተውሉምን? 19ወደ ሆዱ እንጂ ወደ ልቡ ስለማይገባ፣ ከዚያም ወደ መፀዳጃ ስለሚወጣ ነው።” (ይህን በማለት ምግብን ሁሉ ንጹሕ አደረገ።)። 20እንዲህም አለ፤ “ከሰው የሚወጣው፣ ሰውን የሚያረክሰው እርሱ ነው። 21ከውስጥ፣ ከሰው ልብ ክፉ አሳብ ይወጣልና፤ ዝሙት፣ ስርቆት፣ ነፍስ መግደል፣ 22ምንዝር፣ ስግብግብነት፣ ክፋት፣ ተንኰል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትዕቢትና ሞኝነት። 23እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከውስጥ ይወጣሉ፤ ሰውንም ያረክሳሉ።”
የአንዲት አሕዛብ ሴት ጽኑ እምነት
24ኢየሱስም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ። ማንም እንዳያውቅ ፈልጎ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ ነገር ግን ሊሰወር አልቻለም። 25ይልቁንም ታናሽ ልጇ ርኩስ መንፈስ የነበረባት አንዲት ሴት ወዲያውኑ ስለ እርሱ ሰምታ መጥታ በእግሩ ሥር ወደቀች። 26ሴቲቱም ግሪካዊት፣ በትውልድም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። ጋኔኑን ከልጇ እንዲያወጣላትም ደጋግማ ለመነችው።
27እርሱም፣ “መጀመሪያ ልጆች ይጥገቡ፤ የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል አይገባምና” አላት።
28እርሷ ግን መልሳ፣ “ጌታ ሆይ፣ ከጠረጴዛ በታች ያሉ ውሾች እንኳ ከልጆች ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው።
29እርሱም፣ “ስለዚህ መልስ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል” አላት።
30ወደ ቤቷም ሄዳ ልጇ በአልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ወጥቶ አገኘች።
ኢየሱስ የደንቆሮን ጆሮ ከፈተ
31ኢየሱስም ከጢሮስ አገር ወጥቶ፣ በሲዶና አልፎ፣ በዐሥሩ ከተሞች አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ። c c v31 ዴካፖሊስ ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅና በስተ ደቡብ የሚገኙ ዐሥር የግሪክ ከተሞች ያሉበት አገር ነበር። 32ደንቆሮ የሆነና በቅጡ መናገር የማይችል አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። 33ኢየሱስም ከሕዝቡ ለይቶ ብቻውን ወደ ጎን ወሰደው፤ ጣቶቹንም በጆሮዎቹ ውስጥ አግብቶ፣ ተፍቶ፣ ምላሱን ዳሰሰ።
34ከዚያም ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ በጥልቅ ተነፈሰ፤ “ኤፍታህ!” አለው፤ (ይኸውም፣ “ተከፈት!” ማለት ነው)።
35ወዲያውኑም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ የምላሱም እስራት ተፈታ፤ አጥርቶም መናገር ጀመረ። 36ኢየሱስም ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው፤ ነገር ግን ይበልጥ ባዘዛቸው መጠን፣ ይበልጥ አወሩት። 37እጅግም እጅግ ተደነቁ፤ “ሁሉን ነገር መልካም አድርጓል፤ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፣ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል” አሉ።