ኢየሱስ አራት ሺ ሰዎችን መገበ
ኢየሱስ አራት ሺህ ሰዎችን ይመግባል፣ ምልክት ለመስጠት እምቢ ይላል፣ ስለ ፈሪሳውያንም እርሾ ያስጠነቅቃል። አንድ ዕውር በሁለት ደረጃ ያያል። ጴጥሮስ ክርስቶስ ነህ ይለዋል፤ ከዚያም መሞት አለብኝ በማለቱ ይገሥጸዋል፤ የአብ አባታችንን ሳይሆን የሰውን ነገር ስለሚያስብም ሰይጣን ተብሎ ይጠራል።
8 1በዚያን ወራት እንደ ገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ የሚበሉትም ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤
2“ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ፤ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ሆኖአቸዋል፤ የሚበሉትም የላቸውም። 3ተርበው ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው በመንገድ ላይ ይዝላሉ፤ አንዳንዶቹም ከሩቅ መጥተዋል።”
4ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፣ “እዚህ ምድረ በዳ ውስጥ ይህን ሕዝብ በእንጀራ ማን ሊያጠግበው ይችላል?” አሉት።
5እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉ።
6ሕዝቡም መሬት ላይ እንዲቀመጥ አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አቀረቡ። 7ጥቂት ታናናሽ ዓሣዎችም ነበሩአቸው፤ እነርሱንም ባርኮ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። 8በልተውም ጠገቡ፤ ከተረፈውም ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሰበሰቡ። 9በዚያም አራት ሺ የሚያህል ሕዝብ ነበር፤ አሰናበታቸውም።
10ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ ወደ ድልማኑታ አውራጃ ሄደ።
ምልክት የሚሻ ትውልድ
11ፈሪሳውያንም መጥተው ሊከራከሩት ጀመሩ፤ ሊፈትኑትም ከሰማይ ምልክት ጠየቁት።
12በመንፈሱም እጅግ ቃተተና እንዲህ አለ፤ “ይህ ትውልድ ለምን ምልክት ይሻል? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም።”
13ትቷቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳ ገብቶ ወደ ማዶ ተሻገረ።
ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ
14ደቀ መዛሙርቱም እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር፤ በታንኳውም ውስጥ ከአንዲት እንጀራ በስተቀር አልነበራቸውም።
15እርሱም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አስጠነቀቃቸው።
16እነርሱም እንጀራ ስለሌላቸው እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር።
17ኢየሱስም ይህን ዐውቆ እንዲህ አለ፤ “እንጀራ ስለሌላችሁ ለምን ትነጋገራላችሁ? እስከ አሁን አታስተውሉም፤ አትረዱምም? ልባችሁ ደንድኖአልን? 18ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? 19አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺ በቈረስሁ ጊዜ፣ ስንት ቅርጫት ሙሉ ቍርስራሽ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት።
20“ሰባቱንም ለአራት ሺ በቈረስሁ ጊዜ፣ ስንት መሶብ ሙሉ ቍርስራሽ ሰበሰባችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።
21እርሱም፣ “እስከ አሁን አታስተውሉምን?” አላቸው።
ዐይነ ስውር ማየት አገኘ
22ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ፤ ሰዎችም ዐይነ ስውር ወደ እርሱ አመጡ፤ እንዲዳስሰውም ኢየሱስን ለመኑት።
23የዐይነ ስውሩንም እጅ ይዞ ከመንደሩ ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎ እጆቹን ጫነበት፤ “ምን ታያለህ?” ብሎ ጠየቀው።
24እርሱም ቀና ብሎ አየና፣ “ሰዎችን አያለሁ፤ ነገር ግን እንደ ዛፍ ሲመላለሱ ይታዩኛል” አለ።
25ከዚያም ኢየሱስ እንደ ገና እጆቹን በዐይኖቹ ላይ ጫነ፤ እርሱም ትኵር ብሎ አየ፤ ተፈወሰም፤ ሁሉንም ነገር በግልጽ አየ።
26ወደ ቤቱም ሰደደው፤ “ወደ መንደሩ እንኳ አትግባ” አለው።
እኔ ማን ነኝ ትላላችሁ?
27ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄዱ። በመንገድም ላይ፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።
28እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ ይሉሃል፤ ሌሎችም ኤልያስ፤ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ይሉሃል” አሉት።
29እርሱም፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም መልሶ፣ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው።
30ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አበክሮ አዘዛቸው።
የሰው ልጅ መከራ ሊቀበል ግድ ነው
31የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፣ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆችም በጸሐፍትም ተጥሎ ሊገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዳለበት ያስተምራቸው ጀመር። 32ይህንም ነገር በግልጽ ተናገረ። ጴጥሮስም ወደ ጎን ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።
33እርሱ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን አየና ጴጥሮስን ገሠጸው፤ “ሰይጣን ሆይ፣ ከበኋላዬ ሂድ! አንተ የአባታችንን ነገር ሳይሆን የሰውን ነገር ታስባለህና።”
34ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35ነፍሱን ሊያድን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። 36ሰው ዓለሙን ሁሉ አግኝቶ ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? 37ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ሊሰጥ ይችላል? 38በዚህ አመንዝራና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በሚመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።”