አብ ልጁን ይገልጣል
በተራራው ላይ ልብሱ እያንጸባረቀ ነጭ ይሆናል፤ የአባቱ የአብ ድምፅም የተወደደ ልጅ ብሎ ይጠራዋል። ከታች፣ ደቀ መዛሙርቱ ልጁን ሊረዱት ያልቻሉት አንድ አባት አምናለሁ ይላል፤ አለማመኑንም እንዲረዳው ይለምናል። አሥራ ሁለቱ ስለ ታላቅነት ይከራከራሉ፤ ኢየሱስም አንድ ሕፃን በመካከላቸው ያቆማል።
9 1እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከሚቆሙት አንዳንዶች የአባታችን መንግሥት በኀይል ሲመጣ ሳያዩ ሞትን አይቀምሱም።”
2ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ብቻቸውን ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ አወጣቸው፤ በፊታቸውም ተለወጠ። 3ልብሱም እጅግ የሚያብረቀርቅ፣ በምድር ላይ ማንም አጣቢ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ ነጭ ሆነ። 4ኤልያስም ከሙሴ ጋር ተገለጠላቸው፤ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር።
5ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ረቢ ሆይ፤ በዚህ መሆናችን መልካም ነው፤ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፣ አንዱን ለሙሴ፣ አንዱን ለኤልያስ” አለው። 6እጅግ ፈርተው ነበርና ምን ሊል እንደሚገባው አያውቅም ነበር።
7ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም፣ “የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ።
8ወዲያውም ዘወር ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ከእነርሱ ጋር ማንንም አላዩም።
9ከተራራው ሲወርዱ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። 10ስለዚህ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ ከሙታን መነሣት ምን ማለት እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ነበር። 11እነርሱም፣ “ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
12እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “በእርግጥ ኤልያስ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ያቀናል፤ ታዲያ የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበልና ሊናቅ እንደሚገባው የተጻፈው ለምንድን ነው? 13ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቶአል፤ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት።” a a v13 ኢየሱስ በኤልያስ መንፈስና ኀይል ስለ መጣው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እየተናገረ ነው።
የአንድ አባት የተማጽኖ እምነት
14ወደ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው፣ ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ። 15ሕዝቡም ሁሉ ኢየሱስን እንዳዩት ወዲያው ተገረሙ፤ ሊሰላሙትም ወደ እርሱ ሮጡ።
16እርሱም፣ “ከጻፎች ጋር ስለ ምን ትከራከራላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።
17ከሕዝቡም መካከል አንዱ፣ “መምህር ሆይ፤ እንዳይናገር የሚያደርገው መንፈስ ያለበትን ልጄን ወደ አንተ አመጣሁ። 18በያዘውም ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አፉም አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ይደርቃልም። አስወጡልኝ ዘንድ ደቀ መዛሙርትህን ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።”
19እርሱም መልሶ፣ “እናንተ የማታምኑ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት” አለ።
20ልጁንም ወደ እርሱ አመጡት። መንፈሱም ኢየሱስን ባየ ጊዜ ወዲያው አንፈራገጠው፤ መሬት ላይም ወድቆ እየተንፈራገጠ አፉ አረፋ ይደፍቅ ነበር።
21ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ይህ ከመጣበት ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “ከልጅነቱ ጀምሮ ነው” አለ።
22“ሊያጠፋውም ብዙ ጊዜ ወደ እሳትና ወደ ውሃ ጥሎታል። ነገር ግን የምትችለው ነገር ቢኖር፣ አዝነህልን እርዳን።”
23ኢየሱስም፣ “‘ብትችል’ ትላለህን? ለሚያምን ሰው ሁሉ ነገር ይቻለዋል” አለው።
24ወዲያውም የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ።
25ኢየሱስም ሕዝቡ እየሮጠ ሲሰበሰብ ባየ ጊዜ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው፤ “አንተ ዲዳና ደንቆሮ መንፈስ፣ እኔ አዝሃለሁ፤ ከእርሱ ውጣ፤ ከእንግዲህም ዳግመኛ አትግባበት!” አለው።
26ጮኾም አበርትቶ ካንፈራገጠው በኋላ ወጣ። ልጁም እንደ በድን ሆነ፤ ስለዚህ ብዙዎች፣ “ሞተ” አሉ። 27ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ እርሱም ቆመ።
28ኢየሱስም ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
29እርሱም፣ “ይህ ዓይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” አላቸው።
የሰው ልጅ መሞት አለበት
30ከዚያም ወጥተው በገሊላ አለፉ፤ ኢየሱስም የት እንዳሉ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም ነበር፤
31ደቀ መዛሙርቱን ያስተምር ነበርና፤ እንዲህም አላቸው፤ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፤ ይገድሉታልም፤ ከተገደለም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
32እነርሱ ግን ያለውን አልተረዱም፤ ሊጠይቁትም ፈሩ።
ታናሹ ታላቅ ይሆናል
33ወደ ቅፍርናሆምም መጡ። ወደ ቤትም ከገባ በኋላ፣ “በመንገድ ላይ ስለ ምን ትከራከሩ ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው።
34እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ምክንያቱም በመንገድ ላይ ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ተከራክረው ነበር።
35እርሱም ተቀምጦ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፣ “ፊተኛ ሊሆን የሚወድድ ሁሉ የሁሉ ኋለኛና የሁሉ አገልጋይ ይሁን” አላቸው።
36አንድ ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው፤ አቅፎም እንዲህ አላቸው፤
37“ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን እንጂ እኔን አይደለም የሚቀበለው።”
ለእኛ እንጂ በእኛ ላይ አይደለም
38ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ በስምህ አጋንንትን የሚያስወጣ አንድ ሰው አየን፤ እኛን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው።
39ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ በስሜ ተአምር የሚያደርግ ማንም ቶሎ ስለ እኔ ክፉ ሊናገር አይችልምና። 40በእኛ ላይ ያልሆነ ከእኛ ጋር ነውና። 41እውነት እላችኋለሁ፤ የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ አንድ ጽዋ ውሃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ ዋጋው ከቶ አይጠፋበትም።
ታናናሾቹን አታሳስቱ
42በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል ሰው፣ ታላቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። 43እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም፣ ወደማይጠፋው እሳት ከመግባት ይልቅ፣ አካለ ጒዳተኛ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል። b b v43 የጥንቶቹ ቅጂዎች እዚህ ላይ ቍጥር 44 የላቸውም፤ የኋለኞቹ ቅጂዎች ግን፣ “ትላቸው በማይሞትበት እሳቱም በማይጠፋበት” ብለው ይጨምራሉ።
45እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል፣ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል። c c v45 የጥንቶቹ ቅጂዎች እዚህ ላይ ቍጥር 46 የላቸውም፤ የኋለኞቹ ቅጂዎች ግን፣ “ትላቸው በማይሞትበት እሳቱም በማይጠፋበት” ብለው ይጨምራሉ።
47ዐይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል፣ ባንዲት ዐይን ወደ አባታችን መንግሥት መግባት ይሻላል፤ 48በዚያም፣ ‘ትላቸው አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም።’
49ሁሉ በእሳት ይጣፈጣልና። 50ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ቢያጣ፣ እንደ ገና በምን ታጣፍጡታላችሁ? በመካከላችሁ ጨው ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ።”