የቢታንያው አልዓዛር
ኢየሱስ ሁለት ቀን ይቆያል፣ አራት ቀን ዘግይቶ ይደርሳል፣ በወዳጁ መቃብር ላይም ያለቅሳል። ለማርታ ትንሣኤና ሕይወት እርሱ እንደ ሆነ ይነግራታል፣ ስለ ሰማው አብን በድምፅ ያመሰግናል፣ አልዓዛርንም ወደ ውጭ ይጠራዋል። ያን ጊዜ ሸንጎው ሊገድለው ይወስናል።
11 1ከማርያምና ከእኅቷ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የተባለ አንድ ሰው ታሞ ነበር። 2ወንድሟ አልዓዛር የታመመባት ማርያም፣ ጌታን ሽቱ ባለው ዘይት ቀብታ እግሮቹን በጠጒሯ ያበሰች ናት። 3ስለዚህ እኅትማማቾቹ፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትወደው ታሟል” ብለው ወደ እርሱ ላኩ።
4ኢየሱስም ይህን ሰምቶ፣ “ይህ ሕመም በሞት አያልቅም፤ ነገር ግን የአባታችን ልጅ በእርሱ እንዲከብር፣ ለአባታችን ክብር ነው” አለ።
5ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወድ ነበር። 6ስለዚህ አልዓዛር እንደ ታመመ በሰማ ጊዜ፣ ባለበት ስፍራ ሌላ ሁለት ቀን ቈየ።
7ከዚህ በኋላም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው።
8ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ ሆይ፤ አይሁድ ገና አሁን ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ አሁንም ወደዚያ ትመለሳለህን?” አሉት።
9ኢየሱስም መልሶ፣ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት የለምን? በቀን የሚመላለስ ማንም አይሰናከልም፤ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና፤ 10በሌሊት የሚሄድ ቢኖር ግን፣ ብርሃን በእርሱ ውስጥ ስለሌለ ይሰናከላል” አለ። 11ይህንም ተናግሮ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ” አላቸው።
12ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነ ይድናል” አሉት። 13ኢየሱስ የተናገረው ስለ ሞቱ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ ተራ እንቅልፍ የተናገረ መስሏቸው ነበር።
14ስለዚህ ኢየሱስ ግልጥ አድርጎ፣ “አልዓዛር ሞቷል፤ 15እናንተ ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ስላልነበርሁ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ” አለ።
16መንታ የተባለው ቶማስም ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ደግሞ ሄደን ከእርሱ ጋር እንሙት” አላቸው።
17ኢየሱስም በደረሰ ጊዜ፣ አልዓዛር በመቃብር ውስጥ አራት ቀን እንደ ቈየ አገኘ። 18ቢታንያም ከኢየሩሳሌም አጠገብ፣ ሁለት ማይል ያህል ትርቅ ነበር፤ a a v18 ዐሥራ አምስት እስታዲዮን ሁለት ማይል ያህል (ገደማ 3 ኪሎ ሜትር) ነበር። 19ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኗቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። 20ማርታም ኢየሱስ እንደሚመጣ በሰማች ጊዜ፣ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤቱ ውስጥ ተቀምጣ ቀረች። 21ማርታም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። 22አሁንም ቢሆን ከአባታችን የምትለምነውን ሁሉ፣ አባታችን እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለች።
23ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት።
24ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው።
25ኢየሱስም፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ይኖራል፤ 26በሕይወት ኖሮ በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” አላት።
27እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ክርስቶስ፣ የአባታችን ልጅ፣ ወደ ዓለም የሚመጣው እንደ ሆንህ አምናለሁ” አለችው።
28ይህንም ብላ፣ ሄዳ እኅቷን ማርያምን በስውር ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ አንቺንም ይጠራል” አለቻት። 29ማርያምም ይህን በሰማች ጊዜ፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ መጣች። 30ኢየሱስ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር፤ ነገር ግን ማርታ በተገናኘችው ስፍራ ገና ነበር። 31በቤቱ ውስጥ ከእርሷ ጋር የነበሩትና ያጽናኗት የነበሩ አይሁድ፣ ማርያም ፈጥና ተነሥታ ስትወጣ ባዩ ጊዜ፣ በመቃብሩ ዘንድ ልታለቅስ የምትሄድ መስሏቸው ተከተሏት። 32ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ፣ በእግሩ ላይ ወድቃ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው።
33ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ፣ በመንፈሱ እጅግ ተነክቶ ታወከ።
34እርሱም፣ “የት አኖራችሁት?” አለ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት።
35ኢየሱስ አለቀሰ።
36ስለዚህ አይሁድ፣ “እንዴት ይወደው እንደ ነበር እዩ!” አሉ። 37ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዕውሩን ዐይን የከፈተ ይህ ሰው፣ ይህ ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ።
38ስለዚህ ኢየሱስ እንደ ገና በራሱ እጅግ ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ድንጋይ የተገጠመበት ዋሻ ነበር።
39ኢየሱስም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሞተው ሰው እኅት ማርታም፣ “ጌታ ሆይ፤ ሞቶ አራት ቀን ስለ ሆነው አሁን ይሸታል” አለችው።
40ኢየሱስም፣ “ብታምኝ የአባታችንን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት።
41ስለዚህ ድንጋዩን አነሡት። ኢየሱስም ቀና ብሎ አሻቅቦ፣ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። 42አንተ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ፣ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆመው ሕዝብ ይህን ተናገርሁ” አለ። 43ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር ሆይ፤ ወደ ውጭ ውጣ!” ብሎ ጮኸ።
44የሞተውም ሰው እግሮቹና እጆቹ በበፍታ እስፌ ታስረው፣ ፊቱም በጨርቅ ተጠቅልሎ ወጣ። ኢየሱስም፣ “ፍቱት፤ ይሂድም” አላቸው።
ሸንጎው ተሰበሰበ
45ስለዚህ ወደ ማርያም መጥተው ኢየሱስ ያደረገውን ያዩ ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ። 46ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሯቸው። 47ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው፣ “ይህ ሰው ብዙ ምልክቶችን ያደርጋልና ምን እያደረግን ነው? 48እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእርሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ስፍራችንንም ሕዝባችንንም ይወስዳሉ” አሉ።
49ከእነርሱ አንዱ ግን፣ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ፣ “እናንተ ምንም ዐታውቁም። 50ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ፣ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ለእናንተ እንደሚሻላችሁ አታስተውሉም?” አላቸው። 51ይህንም ከራሱ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ስለ ነበር፣ ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ 52ስለ ሕዝቡ ብቻም ሳይሆን፣ የተበተኑትን የአባታችንን ልጆች ወደ አንድነት ለመሰብሰብ ጭምር ነበር። b b v52 ቀያፋ ካወቀው በላይ ተናገረ። ኢየሱስ ስለ አይሁድ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተነውን የአባታችንን ልጅ ሁሉ ወደ አንድ ቤተ ሰብ ለመሰብሰብ ይሞት ነበር። 53ስለዚህ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሊገድሉት ተማከሩ። 54ስለዚህ ኢየሱስ ከእንግዲህ በአይሁድ መካከል በግልጥ አይመላለስም ነበር፤ ነገር ግን ከምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄዶ፣ በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።
55የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር፤ ብዙዎችም ራሳቸውን ለማንጻት ከፋሲካው በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው፣ “ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ ፈጽሞ አይመጣም ይሆን?” ተባባሉ። 57የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሊይዙት ይችሉ ዘንድ፣ ያለበትን የሚያውቅ ማንም ቢኖር እንዲያመለክት አዝዘው ነበር።