በባቢሎን ላይ የተነገረ የአባታችን ትንቢት
ይሁዳን የማረከው ግዛት ራሱ ተፈረደበት፤ ቤል አፈረ፣ ቅጥሮቹ ፈረሱ፣ ምድሩም ለቀበሮዎች ተተወ። በዚያን ጊዜ እስራኤልና ይሁዳ እያለቀሱ ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንና ወደ አባታቸው ወደ አብ የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ፤ በደላቸው ቢፈለግ አይገኝም፤ ታዳጊያቸውም ብርቱ ነው።
50 1ስለ ባቢሎን፣ ስለ ባቢሎናውያን ምድር አባታችን በነቢዩ በኤርምያስ አማካኝነት የተናገረው ቃል ይህ ነው፦
2በሕዝቦች መካከል አውጁ፤ አስታውቁም፤ ሰንደቅ ዓላማ አንሡ፤ አስታውቁ፤ ምንም አትሰውሩ፤ እንዲህ በሉ፦ ባቢሎን ተማረከች፤ ቤል አፈረ፤ ማርዱክ ተሰበረ፤ ምስሎቿ አፈሩ፤ ጣዖቶቿ ተሰባበሩ። a a v2 ቤልና ማርዱክ የባቢሎን ዋነኛ አማልክት ነበሩ። 3ከሰሜን ወገን አንድ ሕዝብ ይመጣባታልና፤ ምድሯንም ባድማ ያደርጋታል፤ የሚኖርባትም የለም፤ ሰውም እንስሳም ሸሽተዋል፤ ሄደዋል።
4በዚያ ወራትና በዚያ ጊዜ፣ ይላል አባታችን፤ የእስራኤል ልጆች ይመጣሉ፤ እነርሱና የይሁዳ ልጆች በአንድነት እያለቀሱ ይሄዳሉ፤ አባታቸውንም ይፈልጋሉ። 5ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ፤ ፊታቸውንም ወደ እርስዋ አዙረው እንዲህ ይላሉ፦ “ኑ፤ ከአባታችን ጋር በዘላለም ኪዳን እንተባበር፤ ይህም ኪዳን ከቶ አይረሳም።” 6ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤ እረኞቻቸው አሳስተዋቸዋል፤ በተራሮችም ላይ ለቀቋቸው፤ ከተራራ ወደ ኰረብታ ተቅበዘበዙ፤ ማረፊያ ቦታቸውንም ረሱ። 7ያገኟቸው ሁሉ በሉአቸው፤ ጠላቶቻቸውም እንዲህ አሉ፦ “እኛ ተጠያቂዎች አይደለንም፤ እነርሱ እውነተኛ መሰማሪያቸው በሆነው በእግዚአብሔር ላይ፣ የአባቶቻቸው ተስፋ በሆነው በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርተዋልና።” 8ከባቢሎን መካከል ሽሹ፤ ከባቢሎናውያን ምድር ውጡ፤ መንጋውን እንደሚመሩ አውራ ፍየሎችም ሁኑ። 9እነሆ፣ ከሰሜን ምድር የታላላቅ ሕዝቦችን ጉባኤ በባቢሎን ላይ አስነሥቼ አመጣባታለሁ፤ በእርስዋም ላይ ይሰለፋሉ፤ ከዚያም ትማረካለች፤ ፍላጾቻቸው ባዶ እጁን ከቶ እንደማይመለስ እንደ ብልኅ ተዋጊ ፍላጻ ናቸው። 10ከለዳ ትበዘበዛለች፤ የሚበዘብዟትም ሁሉ ይጠግባሉ፣ ይላል አባታችን።
11ርስቴን የምትዘርፉ ሆይ፣ ስለ ተደሰታችሁ፣ ስለ ፈነደቃችሁ፣ እህል እንደምትረግጥ ጊደር ስለ ዘለላችሁ፣ እንደ አውራ ፈረሶችም ስለ ጓራችሁ፣ 12እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፤ የወለደቻችሁ ትዋረዳለች፤ እነሆ፣ ከሕዝቦች ሁሉ የመጨረሻ ትሆናለች፤ በረሓ፣ ደረቅ ምድር፣ ምድረ በዳ ትሆናለች። 13ከአባታችን ቍጣ የተነሣ ሰው አይኖርባትም፤ ፈጽማ ባድማ ትሆናለች፤ በባቢሎን በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነግጣል፤ በቍስሏም ሁሉ ላይ ያፏጫል። 14እናንተ ቀስተኞች ሁሉ፣ በባቢሎን ዙሪያ በየአቅጣጫው ተሰለፉ፤ ተኩሱባት፤ ፍላጻ አትቈጥቡ፤ በአባታችን ላይ ኀጢአት ሠርታለችና። 15በየአቅጣጫው በእርስዋ ላይ ጩኹ፤ እጅ ሰጥታለች፤ ማማዎችዋ ወድቀዋል፤ ቅጥሮችዋ ፈርሰዋል፤ ይህ የአባታችን ፍርድ ነውና፣ በእርስዋ ላይ ፍርድ አድርሱ፤ እርስዋ እንዳደረገች አድርጉባት። 16ዘሪውንና አጫጁን ከባቢሎን አጥፉ፤ ከጨቋኙ ሰይፍ የተነሣ እያንዳንዱ ወደ ገዛ ወገኑ ይመለሳል፤ እያንዳንዱም ወደ ገዛ አገሩ ይሸሻል።
17እስራኤል አንበሶች ያባረሩት የተበተነ መንጋ ነው፤ በመጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፤ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ዐጥንቱን አገጠው።
18የሰማይ ሠራዊት አባት፣ የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላል፦ የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ። 19እስራኤልን ወደ ገዛ መሰማሪያው እመልሰዋለሁ፤ በቀርሜሎስና በባሳን ላይ ይሰማራል፤ በኤፍሬምና በገለዓድ ተራሮች ላይ ነፍሱ ትጠግባለች። 20በዚያ ወራትና በዚያ ጊዜ፣ ይላል አባታችን፤ የእስራኤል በደል ይፈለጋል፤ ነገር ግን አይገኝም፤ የይሁዳ ኀጢአቶችም ይፈለጋሉ፤ ነገር ግን አይገኙም፤ በሕይወት የማስቀረውን ቀሪ ይቅር እላለሁና።
21በምራታይም ምድር ላይ ዝመቱ፤ በፋቁድም ነዋሪዎች ላይ ዝመቱ፤ ግደሉ፤ ፈጽማችሁም አጥፉአቸው፤ ይላል አባታችን፤ ያዘዝኋችሁን ሁሉ አድርጉ። 22የጦርነት ድምፅ በምድሪቱ ላይ ነው፤ ታላቅ ጥፋትም አለ። 23የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ተቈረጠ፤ ተሰበረም! ባቢሎን በአሕዛብ መካከል እንዴት ድንጋጤ ሆነች! 24ባቢሎን ሆይ፣ ወጥመድ አጠመድሁብሽ፤ ሳታውቂም ተያዝሽ። ከአባታችን ጋራ ስለ ተከራከርሽ ተገኝተሽ ተያዝሽ።
25አባታችን የጦር መሣሪያ ቤቱን ከፍቶ የቍጣውን የጦር ዕቃዎች አወጣ፤ የሰማይ ሰራዊት አባት በከለዳውያን ምድር የሚሠራው ሥራ አለውና። 26ተነሡባት፤ ከየአቅጣጫው ጐተራዎቿን ክፈቱ፤ እንደ እኽል ክምር አከማቹዋት። ለጥፋት ስጧት፤ ከእርሷ ምንም አይቅር። 27ኮርማዎቿን ሁሉ ግደሉ፤ ወደ ዕርድ ይውረዱ። ቀናቸው፣ የቅጣታቸውም ጊዜ ስለ ደረሰ ወዮላቸው። 28ስሙ፤ ከባቢሎን ምድር የሸሹና የተሰደዱ የአባታችንን ፍርድ፣ ለቤተ መቅደሱ የሚሆነውን ፍርዱን ለማወጅ ወደ ጽዮን ይመጣሉ። 29ቀስተኞችን፣ ቀስት የሚገትሩትን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩ። በዙሪያዋ ክበቧት፤ ማንም አያምልጥ። እንደ ሥራዋ ብድራቷን መልሱላት፤ ያደረገችውን ሁሉ አድርጉባት። በአባታችን ላይ፣ በእስራኤል ቅዱስ ላይ ኵራት አድርጋለችና።
30ስለዚህ ጐበዞቿ በአደባባዮቿ ይወድቃሉ፤ ተዋጊዎቿም ሁሉ በዚያ ቀን ዝም ይላሉ፤ ይላል አባታችን። 31እነሆ፣ አንተ ትዕቢተኛ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ ይላል የሰማይ ሰራዊት አባት፤ ቀንህ፣ የምቀጣህ ጊዜ ደርሷልና። 32ትዕቢተኛው ይሰናከላል፤ ይወድቃልም፤ የሚያነሣውም የለም። በከተሞቹ እሳት አነድዳለሁ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ይበላል። 33የሰማይ ሰራዊት አባት እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ልጆች ተጨቍነዋል፤ ከእነርሱም ጋራ የይሁዳ ልጆች። የማረኳቸው ሁሉ አጥብቀው ይዘዋቸዋል፤ ሊለቋቸውም እምቢ ይላሉ።
34ቤዛቸው ኀያል ነው፤ ስሙ የሰማይ ሰራዊት አባት ነው። ለምድር ዕረፍትን ለማምጣት ነገራቸውን በእርግጥ ይሟገታል፤ በባቢሎን ለሚኖሩ ግን ሁከትን።
35ሰይፍ በከለዳውያን ላይ፣ ይላል አባታችን፤ በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፣ በሹማምቶቿና በጥበበኞቿ ላይ! 36ሰይፍ በሐሰተኞች ነቢያት ላይ፤ ሞኞችም ይሆናሉ! ሰይፍ በተዋጊዎቿ ላይ፤ ይደቈሳሉም! 37ሰይፍ በፈረሶቿና በሠረገሎቿ ላይ፤ በመካከሏ ባሉ መጻተኞች ሰራዊት ሁሉ ላይ፤ እንደ ሴቶችም ይሆናሉ! ሰይፍ በሀብቷ ላይ፤ ይዘረፋልም! 38ድርቅ በውሆቿ ላይ፤ ይደርቃሉም! የጣዖታት ምድር ናትና፤ በሚያስፈሩ ምስሎቻቸውም ያብዳሉ። 39ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊትና ጅቦች በዚያ ይኖራሉ፤ ሰጎኖችም በውስጧ ይቀመጣሉ። ከእንግዲህ ወዲያ ፈጽሞ አይኖርባትም፤ ለልጅ ልጅ ሁሉም አይሰፈርባትም። 40አባታችን ሰዶምንና ገሞራን በአቅራቢያቸውም የነበሩትን ከተሞች እንደ ገለበጠ፣ ይላል አባታችን፤ እንዲሁ ማንም በዚያ አይኖርም፤ ማንም ሰው በውስጧ አይቀመጥም። 41እነሆ፣ ከሰሜን ሰራዊት ይመጣል፤ ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታት ከምድር ዳርቻ ይነሣሉ። 42ቀስትና ጦር ይዘዋል፤ ጨካኞች ናቸው፤ ምሕረትም የላቸውም። ድምፃቸው እንደ ባሕር ይጓዛል፤ በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፣ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፣ ሊዋጉሽ እንደ አንድ ሰው ተሰልፈዋል። 43የባቢሎን ንጉሥ ወሬያቸውን ሰማ፤ እጆቹም ላሉ። ጭንቅ ያዘው፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሥቃይ አገኘው። 44እነሆ፣ ከዮርዳኖስ ቍጥቋጦ ወደ ለም መሰማሪያ እንደሚወጣ አንበሳ፣ በቅጽበት ባቢሎንን ከምድሯ አባርራለሁ፤ የመረጥኩትንም በእርሷ ላይ እሾማለሁ። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ማንስ ሊጠራኝ ይችላል? የትኛውስ እረኛ በፊቴ ሊቆም ይችላል?
45ስለዚህ አባታችን በባቢሎን ላይ ያደረገውን ምክር፣ በባቢሎናውያንም ምድር ላይ የመከረውን ዐሳብ ስሙ፦ በእርግጥ የመንጋቸው ታናናሾች ተጐትተው ይወሰዳሉ፤ በእርግጥ መሰማሪያቸው በዕጣ ፈንታቸው ይደነግጣል። 46ባቢሎን በመያዟ ድምፅ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ጩኸቷም በአሕዛብ መካከል ይሰማል።