ካህናትና ጸሐፍት ሞቱን ያሴራሉ
ይሁዳ በዋጋ ይስማማል። በፋሲካ ማዕድ ላይ ኢየሱስ እንጀራንና ጽዋን ይሰጣል፤ ወዳጆቹም ማን ይበልጣል ብለው ይከራከራሉ። ላቡ እንደ ደም ጠብታ እስኪወርድ ድረስ በጭንቀት ወደ አባቱ ወደ አብ ይጸልያል፤ በመሳም ተላልፎ ይሰጣል፤ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ይክደዋል፤ ከዚያም ዓይኑ ከኢየሱስ ዓይን ጋር ይገጣጠማል።
22 1እርሾ የሌለበት የቂጣ በዓል፣ ፋሲካ የሚባለው፣ ተቃርቦ ነበር። 2የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ሕዝቡን ይፈሩ ስለነበር እንዴት እንደሚገድሉት መንገድ ይፈልጉ ነበር።
3ከዐሥራ ሁለቱም አንዱ በነበረው አስቆሮቱ በተባለው በይሁዳ ሰይጣን ገባበት። 4ሄዶም ከካህናት አለቆችና ከቤተ መቅደሱ ሹማምንት ጋራ እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተማከረ። 5እነርሱም ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ተስማሙ። 6እርሱም ተስማማ፤ ከሕዝቡም ራቅ ባለ ጊዜ አሳልፎ ሊሰጣቸው አመቺ ጊዜ መፈለግ ጀመረ።
የመጨረሻው ፋሲካ ተዘጋጀ
7የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ቀን ደረሰ።
8ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን፣ “ሄዳችሁ የምንበላውን ፋሲካ አዘጋጁልን” ብሎ ላካቸው።
9እነርሱም፣ “የት እንድናዘጋጀው ትፈልጋለህ?” አሉት።
10እርሱም እንዲህ አለ፤ “ወደ ከተማዋ እንደ ገባችሁ ማድጋ ውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ተከትላችሁ ግቡ፤
11የቤቱንም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ ክፍል የት ነው? ይልሃል’ በሉት። 12እርሱም ሰፊ የሆነ የተነጠፈ የላይ ክፍል ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።”
13ሄደውም እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙ፤ ፋሲካንም አዘጋጁ።
14ሰዓቱ በደረሰ ጊዜም እርሱ ከሐዋርያቱ ጋራ በማዕድ ተቀመጠ።
15እንዲህም አላቸው፤ “ከመከራዬ በፊት ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋራ ልበላ እጅግ ናፍቄአለሁ። 16እላችኋለሁና፣ በአባታችን መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ አልበላውም።” 17ጽዋም ተቀብሎ አመስግኖ እንዲህ አለ፤ “ይህን ውሰዱ፤ እርስ በርሳችሁም ተካፈሉት። 18እላችኋለሁና፣ የአባታችን መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከእንግዲህ ከወይን ፍሬ አልጠጣም።”
19እንጀራም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። 20እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። 21ነገር ግን እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ በማዕድ ላይ ከእኔ ጋራ ነው። 22የሰው ልጅ እንደ ተወሰነበት ይሄዳል፤ ነገር ግን አሳልፎ በሚሰጥበት በዚያ ሰው ወዮለት!”
23ከእነርሱም ይህን የሚያደርገው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው መጠያየቅ ጀመሩ።
24ደግሞም ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በመካከላቸው ክርክር ተነሣ።
25እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ነገሥታት ይገዟቸዋል፤ በእነርሱም ላይ ሥልጣን ያላቸው ቸሮች ይባላሉ። 26እናንተ ግን እንደዚህ አትሁኑ፤ ከእናንተ የሚበልጠው እንደ ታናሹ፣ መሪውም እንደሚያገለግለው ይሁን። 27በማዕድ የተቀመጠው ወይስ የሚያገለግለው ማን ይበልጣል? በማዕድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ።
28“በፈተናዬ ከእኔ ጋራ የጸናችሁ እናንተ ናችሁ፤ 29አባቴ ለእኔ መንግሥት እንደ ሰጠኝ፣ እኔም ለእናንተ እሰጣችኋለሁ፤ 30በመንግሥቴ በማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፣ በዙፋኖችም ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ትፈርዱ ዘንድ ነው።”
31“ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፣ ስማ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሁላችሁንም ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ 32እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።”
33ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፣ ከአንተ ጋራ ወደ እስር ቤትም ወደ ሞትም ለመሄድ ተዘጋጅቻለሁ” አለው።
34ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፣ እልሃለሁ፤ ዛሬ ሦስት ጊዜ እንደማታውቀኝ ሳትክድ ዶሮ አይጮኽም” አለው።
35እርሱም፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢት፣ ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ አንዳች አጥታችሁ ነበርን?” አላቸው። እነርሱም፣ “ምንም የለም” አሉ።
36እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆ ያለው ይውሰድ፤ ከረጢትም እንዲሁ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ። 37እላችኋለሁና፣ ‘ከኀጥኣን ጋራ ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በእኔ ሊፈጸም ይገባል፤ ስለ እኔ የተጻፈው እየተፈጸመ ነውና።”
38እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፣ እነሆ፣ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉ። እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።
ወልድ ለአብ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል
39እንደ ልማዱም ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
40ወደ ስፍራውም በደረሰ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው።
41እርሱም ድንጋይ ውርወራ ያህል ከእነርሱ ራቅ ብሎ ተንበርክኮ ጸለየ፤
42እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህን ጽዋ ከእኔ አስወግድ፤ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።”
43ከሰማይም መልአክ እያበረታው ተገለጠለት። a a v43 ቍጥር 43-44 በአንዳንድ ጥንታዊ ቅጆች ውስጥ የሉም። በአብዛኞቹ ዘመናዊ መጻሕፍት ቅዱሳት እንደሚደረገው እዚህ ተካተዋል። 44በጭንቀትም ሆኖ አብልጦ ይጸልይ ነበር፤ ላበቱም ወደ መሬት እንደሚወድቅ እንደ ትልቅ የደም ነጠብጣብ ሆነ።
45ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ ከኀዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸው፤
46እንዲህም አላቸው፤ “ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ።”
በመሳም አሳልፎ ተሰጠ
47ገና ሲናገር ሳለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለው እየመራ ሕዝብ መጣ፤ ኢየሱስንም ሊስመው ቀረበ፤
48ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፣ የሰው ልጅን በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።
49ከእርሱ ጋራ የነበሩትም የሚሆነውን አይተው፣ “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። 50ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ።
51ኢየሱስ ግን መልሶ፣ “ይህ ይብቃ!” አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። 52ኢየሱስም ሊይዙት ወደ እርሱ ለመጡት ለካህናት አለቆችና ለቤተ መቅደሱ ሹማምንት፣ ለሽማግሌዎችም እንዲህ አለ፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በዱላ ልትይዙኝ ወጣችሁን? 53ዕለት ዕለት በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋራ ሳለሁ እጃችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ይህ የእናንተ ሰዓት፣ የጨለማውም ሥልጣን ነው።”
ጴጥሮስ ኢየሱስን ማወቁን ይክዳል
54ይዘውም ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ቤት አገቡት፤ ጴጥሮስም በሩቅ ይከተል ነበር። 55በግቢው መካከልም እሳት አንድደው አብረው ተቀመጡ፤ ጴጥሮስም በመካከላቸው ተቀመጠ። 56አንዲት ገረድ ግን በእሳቱ ብርሃን ፊት ለፊት ተቀምጦ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣ “ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋራ ነበረ” አለች።
57እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፣ አላውቀውም” ብሎ ካደ።
58ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት፣ “አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለ። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፣ አይደለሁም” አለ።
59አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም ሌላው፣ “ይህ ሰው በርግጥ ከእርሱ ጋራ ነበረ፤ ገሊላዊ ነውና” ብሎ አጥብቆ ተናገረ።
60ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፣ የምትለውን አላውቅም” አለ። ወዲያውም ገና ሲናገር ሳለ ዶሮ ጮኸ። 61ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው። ጴጥሮስም ጌታ፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የነገረውን ቃል አስታወሰ። 62ወደ ውጭም ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
63ኢየሱስን የያዙት ሰዎችም እየደበደቡት ያፌዙበት ነበር። 64ዐይኑንም ሸፍነው፣ “ትንቢት ተናገር! የመታህ ማን ነው?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። 65እየሰደቡትም ሌላ ብዙ ነገር በእርሱ ላይ ተናገሩ።
ኢየሱስ በሸንጎው ፊት ቆመ
66በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎች ጉባኤ ማለትም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ወደ ሸንጎአቸውም ወስደው እንዲህ አሉ፤
67“ክርስቶስ ከሆንህ፣ ንገረን።” እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑም፤
68ብጠይቃችሁም አትመልሱም።
69ነገር ግን ከእንግዲህ የሰው ልጅ በአባታችን ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።”
70ሁሉም፣ “እንግዲያውስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉ። እርሱም፣ “እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ” አላቸው።
71እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና” አሉ።