የአባታችን እውነትና ሐሰተኞቹ ነቢያት
አራት መቶ ነቢያት አክዓብን በራሞት ዘገለዓድ ድል እንደሚያደርግ ተስፋ ሰጡት፤ ሚክያስ ብቻ የአባታችንን ሸንጎና በመካከላቸው የተላከውን የሐሰት መንፈስ ተናገረ፤ በእንጀራና በውሃ ላይም ታሰረ። አክዓብ ራሱን ለውጦ ተዋጋ፤ በዘፈቀደ የተወረወረ ፍላጻ አገኘው፤ እንደ ተነገረውም ውሾች ደሙን ላሱ።
22 1በአራምና በእስራኤል መካከል ሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም። 2በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። 3የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን፣ “ራሞት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ከአራም ንጉሥ እጅ ለመውሰድ ምንም ሳናደርግ ዝም ብለን ተቀምጠናል?” አላቸው። 4ኢዮሣፍጥንም፣ “ራሞት ዘገለዓድን ለመውጋት ከእኔ ጋራ ትሄዳለህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው።
5ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “እባክህ አስቀድመህ የአባታችንን ቃል ጠይቅ” አለው።
6የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን፣ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ሰበሰበ፤ “ራሞት ዘገለዓድን ልውጋ ወይስ ልተው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ውጣ፤ ጌታ አባታችን በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጠዋልና” አሉት።
7ኢዮሣፍጥ ግን፣ “የምንጠይቀው የአባታችን ነቢይ ከዚህ ገና የለምን?” አለ።
8የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “አባታችንን በእርሱ በኩል ልንጠይቅ የምንችልበት አንድ ሰው ቀርቷል፤ እኔ ግን እጠላዋለሁ፤ ስለ እኔ መልካም ከቶ አይተነብይም፤ ክፉ ብቻ እንጂ፤ እርሱም የየምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለው። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለ።
9የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ሹም ጠርቶ፣ “የየምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ” አለው።
10የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሳቸውን ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ ባለው አውድማ፣ እያንዳንዳቸው በየዙፋናቸው ተቀመጡ፤ ነቢያቱም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 11የከነዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አራማውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’” አለ። 12ነቢያቱም ሁሉ፣ “ወደ ራሞት ዘገለዓድ ውጣ፤ ድልም ትነሣለህ፤ እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጠዋል” ብለው እንደዚሁ ተነበዩ።
13ሚክያስን ሊጠራ የተላከው መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ነቢያቱ በአንድ ቃል ለንጉሡ ድልን ተናግረዋል፤ ቃልህ ከእነርሱ ቃል ጋራ ይስማማ፤ አንተም ድልን ተናገር” አለው።
14ሚክያስ ግን፣ “አባታችን ሕያው እንደ ሆነ፣ አባታችን የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ” አለ።
15በመጣም ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፣ ራሞት ዘገለዓድን ልንወጋ እንሂድ ወይስ ልንተው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “ውጣ፤ ድልም ትነሣለህ፤ አባታችን በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጠዋል” አለው።
16ንጉሡም፣ “በአባታችን ስም እውነቱን ብቻ እንድትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው።
17እርሱም፣ “እስራኤልን ሁሉ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ አባታችንም፣ ‘እነዚህ ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ’ አለ” አለ።
18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ መልካም እንደማይተነብይ፣ ክፉ ብቻ እንጂ አልነገርኩህምን?” አለው።
19ሚክያስም እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የአባታችንን ቃል ስማ፤ አባታችን በዙፋኑ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በስተ ቀኙና በስተ ግራው በአጠገቡ ቆመው አየሁ።
20አባታችንም፣ ‘አክዓብን ወጥቶ በራሞት ዘገለዓድ እንዲወድቅ የሚያታልለው ማን ነው?’ አለ፤ አንዱም እንዲህ፣ ሌላውም እንዲያ አለ።
21ከዚያም አንድ መንፈስ ወጥቶ በአባታችን ፊት ቆመ፤ ‘እኔ አታልለዋለሁ’ አለ።
22አባታችንም፣ ‘እንዴት?’ አለው። እርሱም፣ ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። አባታችንም፣ ‘ታታልለዋለህ፤ ትሳካለህም፤ ወጥተህ እንዲሁ አድርግ’ አለ።
23አሁንም እነሆ አባታችን በእነዚህ ነቢያትህ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ አባታችንም በአንተ ላይ ክፉ ተናገረ።”
24የከነዓና ልጅ ሴዴቅያስም ቀርቦ ሚክያስን በጒንጩ መታው፤ “የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ ዘንድ አልፎ በየትኛው መንገድ ሊያናግርህ መጣ?” አለው።
25ሚክያስም፣ “ለመደበቅ ወደ ውስጠኛው ክፍል በምትገባበት በዚያ ቀን ታያለህ” አለ።
26የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማው አዛዥ ወደ አሞጽና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ 27እንዲህም በሉ፤ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ በሰላም እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው አስሩት፤ እንጀራና ውሃ ብቻ ስጡት’” አለ።
28ሚክያስም፣ “ፈጽሞ በሰላም ብትመለስ፣ አባታችን በእኔ አልተናገረም” አለ፤ ደግሞም፣ “እናንተ ሕዝቦች ሁሉ፣ ስሙ!” አለ።
አክዓብ አብ እንደ ተናገረው ወደቀ
29የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም ወደ ራሞት ዘገለዓድ ወጡ። 30የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ራሴን ለውጬ ወደ ጦርነት እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ራሱን ለውጦ ወደ ጦርነት ገባ።
31የአራምም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ታናሽም ሆነ ታላቅ ማንንም አትውጉ” ብሎ አዝዞአቸው ነበር።
32የሠረገላ አለቆቹም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “ይህ በርግጥ የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ሊወጉትም ዞሩ፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። 33የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ፣ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 34አንድ ሰውም ሳይተክል ቀስቱን ለቀቀ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ መካከል መታው። ንጉሡም ሠረገላውን ለሚነዳው፣ “ዞር ብለህ ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስዬአለሁና” አለው። 35በዚያም ቀን ጦርነቱ ተፋፋመ፤ ንጉሡም አራማውያንን ትይዩ ሆኖ በሠረገላው ውስጥ ተደግፎ ቆመ። በመሸም ጊዜ ሞተ፤ የቍስሉም ደም ወደ ሠረገላው ታች ፈሰሰ። 36ፀሐይም ስትጠልቅ በሰፈሩ ውስጥ፣ “እያንዳንዱ ወደ ከተማው፣ እያንዳንዱ ወደ አገሩ!” የሚል ጩኸት ተላለፈ።
37ንጉሡም ሞተ፤ ወደ ሰማርያም ተወሰደ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት። 38ሠረገላውንም በሰማርያ ኵሬ አጠቡት፤ ውሾችም ደሙን ላሱ፤ ጋለሞቶችም በዚያ ታጠቡ፤ ይህም አባታችን እንደ ተናገረው ሆነ።
39የአክዓብ ሌላው ሥራ፣ ያደረገው ሁሉ፣ የሠራው የዝሆን ጥርስ ቤተ መንግሥትና ከተሞች ሁሉ፣ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፈው የሉምን? 40አክዓብም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁም አካዝያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
ኢዮሣፍጥ በአብ ፊት ተመላለሰ
41የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በይሁዳ ላይ ነገሠ። 42ኢዮሣፍጥ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም የሽልሒ ልጅ ዓዙባ ትባል ነበር። 43በአባቱ በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በአባታችን ፊት ቅኑን አደረገ። ሆኖም የኮረብታ መስገጃዎች አልፈረሱም ነበር፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረብንና ዕጣን ማጠንን ቀጠሉ። 44ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋራ ሰላም አደረገ።
45የኢዮሣፍጥ ሌላው ሥራ፣ ያሳየው ኀይልና እንዴት እንደ ተዋጋ፣ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ አልተጻፈምን? 46በአባቱ በአሳ ዘመን ቀርተው የነበሩትን የቤተ ጣዖት ወንድ ዘማዊዎች ቀሪዎች ከምድሪቱ አስወገደ። 47በኤዶምም ንጉሥ አልነበረም፤ ምትክ ሆኖ የሚገዛ ነበር። 48ኢዮሣፍጥም ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር ይሄዱ ዘንድ የተርሴስ መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን በዔሲዮን ጋብር ስለ ተሰበሩ አልሄዱም። 49የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን፣ “ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋራ በመርከብ ይሂዱ” አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን እምቢ አለ። 50ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋራ አረፈ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከእነርሱ ጋራ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
አካዝያስ አብን አስቈጣ
51የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በአሥራ ሰባተኛው ዓመት በሰማርያ በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 52በአባታችንም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱ መንገድ፣ በእናቱ መንገድ፣ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በመንገዱ ሄደ። 53በኣልን አገለገለ፤ ሰገደለትም፤ አባቱ እንዳደረገውም አባታችንን፣ የእስራኤልን አምላክ አስቈጣ።