ንጉሥ ፈራ፣ ነቢይም ተጠራ
እስራኤል በአሞራውያን ላይ ባደረገው ነገር የፈራው ሞዓብ እንዲረግማቸው በለዓምን ይቀጥራል። እርሱ ግን አብ የሚነግረውን ብቻ መድገም ይችላል፤ ነጥቡም በአህያ ይገለጣል፤ ዝነኛው ባለ ራእይ ያላየውን በመንገድ ላይ የቆመውን የተመዘዘ ሰይፍ እርሷ ታያለች።
22 1ከዚያም እስራኤላውያን ተነሥተው በዮርዳኖስ ማዶ፣ በኢያሪኮ ትይዩ፣ በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። 2የሲፖር ልጅ ባላቅም እስራኤል በአሞራውያን ያደረገውን ሁሉ አየ። 3ሕዝቡ ብዙዎች ስለ ነበሩ ሞዓብ እጅግ ፈራ፤ ሞዓብም በእስራኤላውያን ተጨነቀ። 4ሞዓብም ለምድያም ሽማግሌዎች፣ “በሬ የሜዳውን ሣር እንደሚልስ፣ ይህ ሕዝብ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይልሳል” አላቸው። በዚያን ጊዜ የሲፖር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበር።
5በወገኖቹም ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በፍቶር ወደሚኖረው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም ሊጠሩት መልእክተኞችን ላከ። እንዲህም አለ፤ “እነሆ፣ አንድ ሕዝብ ከግብፅ ወጥቷል፤ እነሆ፣ የምድሪቱን ፊት ሸፍነዋል፤ በፊቴም ሰፍረዋል። 6አሁንም እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ፤ ከእኔ ይልቅ ብርቱዎች ናቸውና። ምናልባት እመታቸውና ከምድሪቱ አባርራቸው ይሆናል፤ አንተ የባረክኸው የተባረከ፣ የረገምኸውም የተረገመ እንደ ሆነ አውቃለሁና።”
7የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎች የሟርት ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጥተው የባላቅን ቃል ነገሩት።
8እርሱም፣ “በዚህ ሌሊት አድሩ፤ እግዚአብሔር የሚነግረኝንም መልስ አመጣላችኋለሁ” አላቸው። የሞዓብ መኳንንትም ከበለዓም ጋራ አደሩ።
9ከዚያም አባታችን ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋራ ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” አለ።
10በለዓምም ለአባታችን እንዲህ አለ፤ “የሞዓብ ንጉሥ የሲፖር ልጅ ባላቅ ወደ እኔ ልኮ፣ 11እነሆ፣ ከግብፅ የወጣው ሕዝብ የምድሪቱን ፊት ሸፍኗል፤ አሁንም መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባት ተዋግቼ አባርራቸው ይሆናል ብሏል።”
12አባታችን ግን በለዓምን፣ “ከእነርሱ ጋራ አትሂድ፤ ሕዝቡን አትርገም፤ የተባረኩ ናቸውና” አለው።
13በለዓምም በማግስቱ ጥዋት ተነሥቶ የባላቅን መኳንንት፣ “ወደ ምድራችሁ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ እንድሄድ አልፈቀደልኝም” አላቸው።
14የሞዓብ መኳንንትም ተነሥተው ወደ ባላቅ ሄዱ፤ “በለዓም ከእኛ ጋራ ሊመጣ እምቢ አለ” አሉም።
15ባላቅም እንደገና ከፊተኞቹ የበዙና ይበልጥ የተከበሩ መኳንንትን ላከ። 16ወደ በለዓምም መጥተው እንዲህ አሉ፤ “የሲፖር ልጅ ባላቅ እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ከመምጣት ምንም ነገር አይከልክልህ፤ 17እጅግ አከብርሃለሁና፤ የምትለኝንም ሁሉ አደርጋለሁ። እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።”
18በለዓምም ለባላቅ አገልጋዮች መልሶ እንዲህ አለ፤ “ባላቅ ቤቱን የሞላ ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ እንኳ፣ ታናሽ ወይም ታላቅ ነገር ላደርግ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማለፍ አልችልም። 19አሁንም እባካችሁ እናንተም በዚህ ሌሊት አድሩ፤ አባታችን ደግሞ ምን እንደሚለኝ ላውቅ።”
20አባታችንም በሌሊት ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች ሊጠሩህ ስለ መጡ፣ ተነሥተህ ከእነርሱ ጋራ ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ብቻ አድርግ” አለው።
21በለዓምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፤ ከሞዓብ መኳንንትም ጋራ ሄደ።
አባታችን በአህያ በኩል ተናገረ
22እርሱም ስለ ሄደ የአባታችን ቍጣ ነደደ፤ የአባታችንም መልአክ ተቃዋሚው ሆኖ በመንገድ ላይ ቆመ። በለዓም አህያውን ተቀምጦ ነበር፤ ሁለቱም አገልጋዮቹ ከእርሱ ጋራ ነበሩ። 23አህያይቱም የአባታችንን መልአክ ሰይፉን መዝዞ በእጁ ይዞ በመንገድ ላይ ቆሞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ ሜዳ ገባች። በለዓምም አህያይቱን ወደ መንገዱ ይመልሳት ዘንድ መታት። 24የአባታችንም መልአክ በወይን ቦታዎች መካከል፣ በሁለቱም ወገን ቅጥር ባለው ጠባብ መንገድ ቆመ። 25አህያይቱም የአባታችንን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፤ የበለዓምንም እግር በቅጥሩ ላይ አጫጨቀች፤ እርሱም እንደገና መታት።
26የአባታችንም መልአክ ወደ ፊት አልፎ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ለመታጠፍ ስፍራ በሌለበት ጠባብ ቦታ ቆመ። 27አህያይቱም የአባታችንን መልአክ ባየች ጊዜ፣ ከበለዓም በታች ተኛች፤ የበለዓምም ቍጣ ነደደ፤ በበትሩም መታት።
28ከዚያም አባታችን የአህያይቱን አፍ ከፈተ፤ እርሷም በለዓምን፣ “እነዚህን ሦስት ጊዜ የመታኸኝ፣ ምን አደረግሁብህ?” አለችው።
29በለዓምም አህያይቱን፣ “አፌዝሽብኝ! በእጄ ሰይፍ ቢኖረኝ ኖሮ፣ አሁን እገድልሽ ነበር” አላት።
30አህያይቱም በለዓምን፣ “እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የተቀመጥህብኝ አህያህ አይደለሁምን? ከዚህ በፊት እንዲህ አድርጌብህ አውቃለሁን?” አለችው። እርሱም፣ “አላደረግሽም” አለ።
31ከዚያም አባታችን የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የአባታችንንም መልአክ ሰይፉን መዝዞ በእጁ ይዞ በመንገድ ላይ ቆሞ አየ፤ አጐንብሶም በግንባሩ ተደፋ።
32የአባታችንም መልአክ እንዲህ አለው፤ “አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታሃት? መንገድህ በፊቴ የተጣመመ ስለ ሆነ፣ ልቃወምህ ወጥቻለሁ። 33አህያይቱ አይታኝ እነዚህን ሦስት ጊዜ ከእኔ ፈቀቅ አለች፤ ፈቀቅ ባትል ኖሮ፣ አሁን አንተን በገደልሁ፣ እርሷን ግን ባተረፍሁ ነበር።”
34በለዓምም ለአባታችን መልአክ እንዲህ አለ፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ ልትቃወመኝ በመንገድ ላይ እንደ ቆምህ አላወቅሁም ነበር። አሁንም ይህ በዐይንህ ክፉ መስሎ ቢታይ፣ እመለሳለሁ።”
35የአባታችንም መልአክ በለዓምን፣ “ከሰዎቹ ጋራ ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው። በለዓምም ከባላቅ መኳንንት ጋራ ሄደ።
36ባላቅም በለዓም እንደሚመጣ በሰማ ጊዜ፣ በአርኖን ድንበር ላይ ባለችው፣ በድንበሩ ዳር ባለችው በሞዓብ ከተማ ሊቀበለው ወጣ። 37ባላቅም በለዓምን፣ “ልጠራህ አጥብቄ አልላክሁምን? ለምን ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ ላከብርህ አልችልምን?” አለው።
38በለዓምም ባላቅን፣ “እነሆ፣ አሁን ወደ አንተ መጥቻለሁ፤ ነገር ግን ማናቸውንም ነገር መናገር እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያኖረውን ብቻ መናገር እችላለሁ” አለው።
39በለዓምም ከባላቅ ጋራ ሄደ፤ ወደ ቂርያት ሑጾትም መጡ። 40ባላቅም ከብትና በግ ሠዋ፤ ለበለዓምና ከእርሱ ጋራ ላሉት መኳንንትም ድርሻ ላከ። 41በማግስቱ ጥዋት ባላቅ በለዓምን ወስዶ ወደ ባሞተ በኣል አወጣው፤ ከዚያም የሕዝቡን ዳር አየ።