ለተራበው ሕዝብ እንጀራ
አምስት እንጀራ ሺዎችን ይመግባል፣ ሕዝቡም ንጉሥ ሊያደርጉት ይፈልጋሉ። ኢየሱስ በውሃው ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ ይመጣል፤ ከዚያም አብ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ እንደሚሰጥ፣ እርሱም ያ እንጀራ እንደ ሆነ፣ ሥጋውም ለዓለም እንደሚሰጥ ይነግራቸዋል። ብዙ ደቀ መዛሙርት ይተዉታል፤ ጴጥሮስ ግን ወደ ሌላ የሚሄድበት የለውም።
6 1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የጥብርያዶስ ባሕር ተብሎ ወደሚጠራው የገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ። 2በበሽተኞች ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። 3ኢየሱስም ወደ ተራራው ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ተቀመጠ። 4የአይሁድ በዓል የሆነው ፋሲካም ቀርቦ ነበር።
5ኢየሱስም ቀና ብሎ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን፣ “እነዚህ ሰዎች የሚበሉትን እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” አለው።
6ራሱ ሊያደርግ ያለውን አስቀድሞ ያውቅ ነበርና ይህን ያለው ፊልጶስን ሊፈትነው ነበር።
7ፊልጶስም መልሶ፣ “እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲያገኙ የሁለት መቶ ቀን ደመወዝ የሚያወጣ እንጀራ አይበቃቸውም” አለው። a a v7 አንድ ዲናር የአንድ ቀን ደመወዝ ያህል ነበር፤ ሁለት መቶ ዲናር ደግሞ የስምንት ወር ያህል ደመወዝ ነበር።
8ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፤ 9“አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ ያለው አንድ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን ይህ ለእነዚህ ሁሉ ምን ይሆናል?”
10ኢየሱስም፣ “ሰዎቹን አስቀምጧቸው” አለ። በዚያም ብዙ ሣር ነበረ፤ ስለዚህ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ተቀመጡ።
11ከዚያም ኢየሱስ እንጀራውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለተቀመጡትም አከፋፈለ፤ እንዲሁም ከዓሣው እንደ ፈለጉት ያህል ሰጣቸው።
12ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “አንዳች እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰብስቡ” አላቸው።
13ስለዚህ ሰዎቹ ከበሉ በኋላ ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰበሰቡ፤ ዐሥራ ሁለት መሶብም ሞሉ። 14ሰዎቹም ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ፣ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው!” አሉ። 15ኢየሱስም መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ ዳግመኛ ብቻውን ወደ ተራራ ፈቀቅ አለ።
ወደ ማዕበሉ መካከል
16በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ወረዱ፤ 17ወደ ታንኳም ገብተው ባሕሩን ተሻግረው ወደ ቅፍርናሆም አመሩ። አስቀድሞም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር። 18ኀይለኛ ነፋስም ይነፍስ ነበር፤ ባሕሩም ተናወጠ። 19ሦስት ወይም አራት ማይል ያህል ከቀዘፉ በኋላ ኢየሱስ በውሃው ላይ እየተራመደ ወደ ታንኳዪቱ ሲቀርብ አዩና ፈሩ።
20እርሱ ግን፣ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።
21ስለዚህ ወደ ታንኳዪቱ ሊያስገቡት ተደሰቱ፤ ታንኳዪቱም ወዲያውኑ ወደሚሄዱበት ዳርቻ ደረሰች።
22በማግስቱ በባሕሩ ማዶ ቀርቶ የነበረው ሕዝብ በዚያ ከአንዲት ታንኳ በቀር ሌላ አለመኖሩን፣ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በታንኳዪቱ አለመሳፈሩን፣ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን መሄዳቸውን አየ። 23ጌታ ካመሰገነ በኋላ እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አቅራቢያ ከጥብርያዶስ ሌሎች ታንኳዎች መጡ። 24ስለዚህ ሕዝቡ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን ባየ ጊዜ፣ ወደ ታንኳዎች ገብተው ኢየሱስን ለመፈለግ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። 25በባሕሩም ማዶ ባገኙት ጊዜ፣ “ረቢ፣ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት።
26ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የምትፈልጉኝ ምልክቶችን ስላያችሁ ሳይሆን እንጀራውን በልታችሁ ስለ ጠገባችሁ ነው። 27ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ይህንም የሰው ልጅ ይሰጣችኋል። አባታችን ማኅተሙን ያተመበት እርሱ ነውና።”
28ከዚያም እርሱን፣ “የአባታችንን ሥራ ለመሥራት ምን እናድርግ?” አሉት።
29ኢየሱስም መልሶ፣ “የአባታችን ሥራ ይህ ነው፤ በላከው ሰው እንድታምኑ ነው” አላቸው።
30ስለዚህ እርሱን እንዲህ አሉት፤ “ታዲያ አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ታሳያለህ? ምን ሥራ ትሠራለህ? 31አባቶቻችን ‘ከሰማይ እንጀራ እንዲበሉ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ በምድረ በዳ መና በሉ።”
32ኢየሱስም፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ የሆነውን እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ ከሰማይ የሆነውን እውነተኛ እንጀራ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው። 33የአባታችን እንጀራ ከሰማይ የሚወርደውና ለዓለም ሕይወትን የሚሰጠው እርሱ ነውና።”
34ስለዚህ እርሱን፣ “ጌታ ሆይ፣ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን” አሉት።
35ኢየሱስም፣ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምን ከቶ አይጠማም። 36ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኛል፤ ይሁን እንጂ አታምኑም። 37አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ አላወጣውም። 38የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። 39የላከኝም ፈቃድ ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንዱን እንኳ ሳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው ነው። 40የአባቴ ፈቃድ ይህ ነውና፤ ወደ ወልድ የሚመለከትና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”
41ስለዚህ አይሁድ፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” ስላለ ስለ እርሱ አጕረመረሙ።
42እነርሱም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቀው የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን፣ ‘ከሰማይ ወርጃለሁ’ እንዴት ሊል ይችላል?” አሉ።
43ኢየሱስም መልሶ፣ “እርስ በርሳችሁ ማጕረምረማችሁን ተዉ።
44“የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። b b v44 ወደ ኢየሱስ መምጣት የአባታችን አነሣሽነት ነው፤ እርሱ ልጆቹን ወደ ወልድ የሚስበው በሚያስገድድ ኀይል ሳይሆን በሚከታተል ፍቅር ነው። 45በነቢያት መጽሐፍ፣ ‘ሁሉም ከአባታችን ይማራሉ’ ተብሎ ተጽፏል። ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46ከአብ ዘንድ ከመጣው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ እርሱ አብን አይቷል። 47እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። 48የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። 49አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ነገር ግን ሞቱ። 50ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ የሚወርደው እንጀራ ይህ ነው። 51ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ። ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል። የምሰጠውም እንጀራ ለዓለም ሕይወት የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”
52ከዚያም አይሁድ፣ “ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ተከራከሩ።
53ኢየሱስም፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 55ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። 56ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ስለ አብ ሕያው እንደ ሆንሁ፣ እንዲሁ እኔን የሚበላ ስለ እኔ ሕያው ይሆናል። 58ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው። አባቶቻችሁ እንደ በሉትና እንደ ሞቱት እንጀራ አይደለም። ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል።”
59ይህንም በቅፍርናሆም ምኵራብ ሲያስተምር ተናገረ። 60ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ የሚከብድ ትምህርት ነው፤ ሊቀበለው ማን ይችላል?” አሉ።
ብዙዎች ወደ ኋላ ሲመለሱ
61ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደሚያጕረመርሙ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ያሰናክላችኋልን?
62“ታዲያ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል? 63ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ለምንም አይጠቅምም። የነገርኋችሁ ቃሎች መንፈስና ሕይወት ናቸው። 64ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።” ኢየሱስ ከጥንቱ የማያምኑ እነማን እንደ ሆኑ፣ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና። 65ደግሞም፣ “አብ ካልሰጠው በቀር ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም ያልኋችሁ ስለዚህ ነው” አለ።
66ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያ ወዲያም ከእርሱ ጋር አልተመላለሱም።
67ስለዚህ ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን፣ “እናንተም ደግሞ ልትሄዱ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው።
68ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፣ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ። 69አንተ የአባታችን ቅዱሱ እንደ ሆንህ እኛ አምነናል፤ ዐውቀናልም።”
70ኢየሱስም መልሶ፣ “እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ሰይጣን ነው” አላቸው።
71ይህንም ያለው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረውን፣ አሳልፎ ሊሰጠው ያለውን የስምዖን አስቆሮቱን ልጅ ይሁዳን ነበር።