አባታችን ናታንን ወደ ዳዊት ላከ
ናታን አንድ ባለጠጋ የድሀውን የቤት በግ ስለ መስረቁ ታሪክ ይነግረዋል፤ ዳዊትም አንተ ነህ ያ ሰው የሚለውን ሳይሰማ ራሱን ይፈርዳል። ሰይፍ ከቤቱ ፈጽሞ አይለይም። ለሚሞተው ሕፃን ይጾማል፤ ከዚያም ተነሥቶ ይሰግዳል። ሰሎሞን ይወለዳል፤ አብም ይወደዋል።
12 1አባታችን ናታንን ወደ ዳዊት ላከ። እርሱም መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንዲት ከተማ ውስጥ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ ባለጸጋ፣ ሌላው ድኻ ነበር። 2ባለጸጋው እጅግ ብዙ በጎችና ከብቶች ነበሩት፤ 3ድኻው ግን የገዛት አንዲት ትንሽ ሴት ጠቦት ብቻ ነበረችው። አሳደጋት፤ ከእርሱና ከልጆቹ ጋራ አደገች። ከሳሕኑ በላች፣ ከጽዋው ጠጣች፣ በዕቅፉ ተኛች፤ ለእርሱም እንደ ሴት ልጅ ነበረች። 4ወደ ባለጸጋው አንድ መንገደኛ መጣ፤ ነገር ግን ለመጣው እንግዳ ምግብ ለማዘጋጀት ከራሱ በጎች ወይም ከብቶች ሊወስድ አልፈለገም። ስለዚህ የድኻውን ሴት ጠቦት ወስዶ ወደ እርሱ ለመጣው ሰው አዘጋጀ።”
5ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ናታንንም እንዲህ አለው፤ “አባታችን ሕያው እንደ ሆነ፣ ይህን ያደረገ ሰው ፈጽሞ ሊሞት ይገባዋል! 6ይህን ስላደረገና ስላልራራ፣ ለጠቦቷ አራት እጥፍ አድርጎ ይክፈል።”
7ከዚያም ናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ! አባታችን የእስራኤል አምላክ እንዲህ ይላል፤ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ።
8“የጌታህን ቤትና ሚስቶቹን በዕቅፍህ ሰጠሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳንም ቤት ሰጠሁህ። ይህም ያነሰ ቢሆን ኖሮ፣ ከዚህ እጅግ የበለጠ እሰጥህ ነበር። 9ታዲያ በፊቴ ክፉ ነገር በማድረግ የእኔን ቃል ለምን ናቅህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታኸው፤ ሚስቱንም ለራስህ ወሰድህ፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። 10ስለዚህ ናቅኸኝና የኬጢያዊውን ኦርዮን ሚስት ለራስህ ስለ ወሰድህ፣ ከእንግዲህ ሰይፍ ከቤትህ ከቶ አይለይም።
11አባታችን እንዲህ ይላል፤ እነሆ፣ ከገዛ ቤትህ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ። በዓይንህ ፊት ሚስቶችህን ወስጄ ለባልንጀራህ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በግልጥ ቀን ከእነርሱ ጋራ ይተኛል። 12አንተ ይህን በስውር አደረግህ፤ እኔ ግን ይህን ነገር በመላው እስራኤል ፊት፣ በግልጥ ቀን አደርገዋለሁ።”
13ዳዊትም ናታንን፣ “አባታችንን በድያለሁ” አለው። ናታንም መልሶ፣ “አባታችን ደግሞ ኀጢአትህን አስወግዶልሃል፤ አትሞትም” አለው።
14ነገር ግን በዚህ ድርጊትህ አባታችንን እጅግ ስለ ናቅህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል። 15ከዚያም ናታን ወደ ቤቱ ሄደ። የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ልጅ አባታችን መታው፤ እርሱም ጽኑ ደዌ ታመመ። 16ዳዊትም ስለ ልጁ አባታችንን ለመነ። ጾመም፤ ወደ ውስጥ ገብቶ፣ ሌሊቱን ሁሉ በምድር ላይ ተኝቶ አደረ። 17የቤቱም ሽማግሌዎች ከምድር ሊያነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ ከእነርሱም ጋራ ምግብ አልበላም። 18በሰባተኛውም ቀን ልጁ ሞተ። የዳዊትም አገልጋዮች ልጁ እንደ ሞተ ሊነግሩት ፈሩ፤ እንዲህ ይሉ ነበርና፤ “ልጁ በሕይወት ሳለ ተናገርነው፤ እርሱ ግን አልሰማንም። ታዲያ ልጁ ሞተ ብለን እንዴት እንናገራለን? ራሱን ይጎዳ ይሆናል።”
19ዳዊትም አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አየ፤ ልጁም እንደ ሞተ አወቀ። ስለዚህ፣ “ልጁ ሞቷልን?” ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፣ “ሞቷል” አሉት።
20ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፤ ዘይት ተቀባ፤ ልብሱንም ለወጠ። ወደ አባታችን ቤትም ገብቶ ሰገደ፤ ከዚያም ወደ ቤቱ ሄደ፤ ባዘዘውም መሠረት ምግብ አቀረቡለት፤ በላም። 21አገልጋዮቹም፣ “ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? ልጁ በሕይወት ሳለ ጾምህ፣ አለቀስህ፤ አሁን ግን ከሞተ በኋላ ተነሥተህ ትበላለህ” አሉት።
22እርሱም እንዲህ አለ፤ “ልጁ በሕይወት ሳለ፣ ‘ማን ያውቃል? አባታችን ይራራልኝ ይሆናል፤ ልጁም በሕይወት ይኖር ይሆናል’ ብዬ ሳስብ ጾምሁ፣ አለቀስሁ። 23አሁን ግን ሞቷል። ታዲያ ለምን እጦማለሁ? መልሼ ላስመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ፤ እርሱ ግን ወደ እኔ አይመለስም።”
24ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ ከእርሷ ጋራ ተኛ፤ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። አባታችንም ወደደው፤ 25በነቢዩ በናታን በኩልም ቃል ላከ፤ እርሱም ስለ አባታችን ሲል ይዲድያ ብሎ ጠራው። a a v25 ይዲድያ ማለት “የአባታችን ተወዳጅ” ማለት ነው፤ ይህ ስም አባታችን ገና በልጁ ላይ ያሳደረውን ፍቅር ያስተጋባል።
ዳዊት ረባትን ያዘ
26በዚህ ጊዜ ኢዮአብ የአሞናውያንን ረባት ተዋጋ፤ የንጉሡንም ከተማ ያዘ። 27ኢዮአብም ወደ ዳዊት መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አለ፤ “ረባትን ተዋግቼ የውሃ መገኛዋን ያዝሁ። 28አሁንም የቀረውን ሰራዊት ሰብስበህ ከተማዪቱን ክበብ፤ ያዛትም። ያለዚያ እኔ እይዛታለሁ፤ በስሜም ትጠራለች።”
29ዳዊትም መላውን ሰራዊት ሰብስቦ ወደ ረባት ዘመተ፤ ተዋጋትም፤ ያዛትም። 30የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ዘውዱም ክቡር ድንጋይ የተቀረጸበት፣ ሰባ አምስት ፓውንድ ያህል የሚመዝን ወርቅ ነበር፤ በዳዊትም ራስ ላይ ተደረገ። ከከተማዪቱም እጅግ ብዙ ምርኮ ዘረፈ። 31በዚያም የነበሩትን ሰዎች አስወጥቶ በመጋዝ፣ በብረት ዶማና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ በጡብ ማቃጠያ ቦታም አሠራቸው። ለአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሰራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።