በርናባስና ሳኦል ተለዩ
በአንጾኪያ የሚጾሙ መሪዎች በርናባስንና ሳውልን ይልካሉ። በቆጵሮስ አገረ ገዥውን ከአብ ቃል የሚከለክል ጠንቋይ ይታወራል። በጲስድያዋ አንጾኪያ ጳውሎስ የእስራኤልን ታሪክ እስከ ትንሣኤ ድረስ ይዘረዝራል፤ ከተማዪቱ ተጨናንቃ ትሰበሰባለች፤ ቅናት ይፈነዳል፤ ሁለቱም ወደ አሕዛብ ይዞራሉ።
13 1በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና አስተማሪዎች ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ (ከአራተኛው ክፍል ገዥ ከሄሮድስ ጋራ አብሮ ያደገው) ማናኤንና ሳኦል ነበሩ።
2ጌታችንን ኢየሱስን እያመለኩና እየጦሙ ሳሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “ለጠራኋቸው ሥራ በርናባስንና ሳኦልን ለዩልኝ” አለ።
3ከዚያም ከጦሙና ከጸለዩ በኋላ፣ እጆቻቸውን ጫኑባቸውና ሰደዷቸው።
የአባታችን ቃል ቆጵሮስ ደረሰ
4በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። 5ሰላሚስ በደረሱ ጊዜ፣ የአባታችንን ቃል በአይሁድ ምኵራቦች ሰበኩ። ዮሐንስም ረዳታቸው ሆኖ ነበር። 6ደሴቲቱን ሁሉ አልፈው እስከ ጳፉስ በደረሱ ጊዜ፣ በርያሱስ የተባለ አይሁዳዊ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ አገኙ፤ 7እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ከአገረ ገዡ ከሴርግዮስ ጳውሎስ ጋራ ነበር። አገረ ገዡም የአባታችንን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳኦልን አስጠራ። 8ጠንቋዩ ኤልማስ — የስሙ ትርጓሜ ይህ ነውና — አገረ ገዡን ከእምነት ለማዘንበል እየሞከረ ተቃወማቸው። 9ጳውሎስ የተባለው ሳኦል ግን መንፈስ ቅዱስ ሞልቶበት ትኵር ብሎ ተመለከተውና 10እንዲህ አለው፤ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ በተንኰልና በክፋት ሁሉ የተሞላህ፣ የአባታችንን ቅን መንገዶች ከማጣመም ከቶ አትቦዝንምን? 11አሁንም እነሆ፣ የአባታችን እጅ በአንተ ላይ ናት። ዕውር ትሆናለህ፤ ለጊዜውም ፀሐይን ማየት አትችልም።” ወዲያውም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጅ የሚመራውን ሰው እየፈለገ ይዳክር ጀመር።
12አገረ ገዡም የሆነውን አይቶ አመነ፤ በጌታችን በኢየሱስ ትምህርትም ተደነቀ።
የአባታችን ታሪክ በአንጾኪያ ተሰበከ
13ጳውሎስና ባልንጀሮቹ ከጳፉስ በመርከብ ተነሥተው ወደ ጵንፍልያዋ ጴርጌ መጡ፤ ዮሐንስ ግን ተዋቸውና ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 14ከጴርጌም አልፈው ወደ ጲስድያዋ አንጾኪያ ሄዱ። በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። 15ከሕግና ከነቢያት ንባብ በኋላ፣ የምኵራቡ አለቆች፣ “ወንድሞች ሆይ፣ ለሕዝቡ የምትናገሩት የማበረታቻ ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ላኩባቸው።
16ጳውሎስም ተነሥቶ በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች፣ አባታችንንም የምትፈሩ ሆይ፣ ስሙ። 17የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አባት የሆነው አባታችን አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብፅ ምድር ተቀምጠው ሳሉ አበዛቸው፤ በተዘረጋ ክንድም አወጣቸው። 18አርባ ዓመትም ያህል በምድረ በዳ ታገሣቸው። 19በከነዓን ምድር ሰባት ሕዝቦችን ካጠፋ በኋላ፣ ምድራቸውን ርስት አድርጎ ሰጣቸው። 20ይህም አራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያህል ፈጀ። ከዚያም እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንት ሰጣቸው። 21ከዚያም ንጉሥ ለመኑ፤ አባታችንም የብንያምን ነገድ ሰው የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት ሰጣቸው። 22እርሱንም ካስወገደ በኋላ፣ ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ አስነሣላቸው፤ ስለ እርሱም፣ ‘የእሴይን ልጅ ዳዊትን እንደ ልቤ የሆነ ሰው፣ ፈቃዴን ሁሉ የሚፈጽም ሰው አገኘሁ’ ሲል መሰከረ። 23አባታችንም እንደ ተስፋው ከዚህ ሰው ዘር አዳኝን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ። 24እርሱ ከመምጣቱም በፊት፣ ዮሐንስ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። 25ዮሐንስም ሩጫውን እየጨረሰ ሳለ፣ ‘እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይመስላችኋል? እኔ እርሱ አይደለሁም። ነገር ግን እነሆ፣ ከእኔ በኋላ የሚመጣ አለ፤ የእግሩን ጫማ መፍታት እንኳ አይገባኝም’ አለ።
26“ወንድሞች ሆይ፣ የአብርሃም ትውልድ ልጆች፣ ከእናንተም መካከል አባታችንን የምትፈሩ ሆይ፣ ይህ የድነት መልእክት ለእኛ ተልኮአል። 27የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱን አላወቁትም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት ቃሎች አልተረዱም፤ እርሱን በመኰነን ይህንኑ ቃል ፈጸሙ። 28የሚያስገድለውን ምክንያት ባያገኙበትም፣ እንዲገደል ጲላጦስን ለመኑ። 29ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ ከዕንጨቱ አውርደው በመቃብር አኖሩት። 30አባታችን ግን ከሙታን አስነሣው፤ 31ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም አብረውት ለወጡትም ብዙ ቀን ታየ፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው። 32እኛም አባታችን ለአባቶቻችን የሰጠውን ተስፋ የምስራች እናበስራችኋለን፤
33ኢየሱስን በማስነሣት ይህን ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታልና፤ በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፣ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ’ ተብሎ እንደ ተጻፈ።
34ከሙታንም እንዳስነሣው፣ ከእንግዲህም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ፣ ‘ለዳዊት የተሰጠውን ቅዱስና የተረጋገጠ በረከት እሰጥሃለሁ’ አለ። 35ስለዚህም በሌላ መዝሙር፣ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትተውም’ ይላል። 36ዳዊት በራሱ ትውልድ የአባታችንን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋራ ተቀበረ፤ መበስበስንም አየ፤ 37አባታችን ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። 38እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እወቁ፤ በዚህ ሰው በኩል የኀጢአት ይቅርታ ይሰበክላችኋል፤ 39በእርሱም የሚያምን ሁሉ የሙሴ ሕግ ነጻ ሊያወጣችሁ ካልቻለው ነገር ሁሉ ነጻ ይወጣል። 40እንግዲህ በነቢያት የተነገረው በእናንተ ላይ እንዳይደርስ ተጠንቀቁ፤ 41‘እናንተ ተሳላቂዎች ሆይ፣ እዩ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ እኔ በዘመናችሁ ሥራ እሠራለሁና፤ ማንም ቢነግራችሁ እንኳ ከቶ የማታምኑትን ሥራ።’”
42ጳውሎስና በርናባስም ሲወጡ፣ ሕዝቡ በሚቀጥለው ሰንበት ስለ እነዚህ ነገሮች ደግመው እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። 43የምኵራቡም ስብሰባ በተፈታ ጊዜ፣ ብዙ አይሁድና ወደ አይሁድ እምነት የገቡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉ፤ እነርሱም አነጋገሯቸውና በአባታችን ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አበረታቷቸው።
44በሚቀጥለው ሰንበትም የጌታችንን የኢየሱስን ቃል ለመስማት መላው ከተማ ማለት ይቻላል ተሰበሰበ። 45አይሁድ ግን ሕዝቡን ባዩ ጊዜ ቅናት ሞላባቸው፤ እየተሳደቡም የጳውሎስን ቃል ተቃወሙ።
46ጳውሎስና በርናባስ በድፍረት እንዲህ አሉ፤ “የአባታችን ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ ሊነገር ይገባ ነበር። እናንተ ግን ስለ ናቃችሁት፣ ራሳችሁን ለዘላለም ሕይወት የማይገባ አድርጋችሁ ስለ ፈረዳችሁ፣ እነሆ ወደ አሕዛብ እንዞራለን።”
47አባታችን እንዲህ ብሎ አዝዞናልና፤ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ድነትን ታደርስ ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ።”
48አሕዛብም ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ የጌታችንንም የኢየሱስን ቃል አከበሩ፤ ለዘላለም ሕይወትም የተመደቡ ሁሉ አመኑ። 49የጌታችንም የኢየሱስ ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። 50አይሁድ ግን ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን የተከበሩ ሴቶችንና የከተማዋን ታላላቅ ሰዎች አነሣሡ፤ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሡ፤ ከአገራቸውም አስወጧቸው። 51እነርሱም የእግራቸውን ትቢያ አራገፉባቸውና ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። 52ደቀ መዛሙርቱም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞሉባቸው።