ሄሮድስ ቤተ ክርስቲያንን አጠቃ
ሄሮድስ ያዕቆብን ይገድላል፤ ጴጥሮስንም ያስራል። የአብ መልአክ በሌሊት ሰንሰለቱን ይፈታል፤ በሮችም በራሳቸው ይከፈታሉ፤ ጴጥሮስ ሕልም የሚያይ ይመስለዋል። በጸሎቱ ስብሰባ አንዲት ሠራተኛ ልጃገረድ አብደሻል ትባላለች። እንደ አምላክ የተወደሰው ሄሮድስ ይሞታል።
12 1በዚያን ጊዜ ገደማ ንጉሡ ሄሮድስ ሊጐዳቸው አስቦ ከቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን ለማሳደድ እጁን ዘረጋባቸው። 2የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። 3ይህም አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ፣ በቂጣ በዓል ወራት ጴጥሮስንም ጭምር ለመያዝ ቀጠለ። 4ይዞም ወደ እስር ቤት አስገባው፤ ከፋሲካ በኋላ ወደ ሕዝቡ ሊያወጣው አስቦ፣ አራት አራት ወታደሮች ላሏቸው ለአራት የጥበቃ ክፍሎች እንዲጠብቁት አሳልፎ ሰጠው።
5ጴጥሮስም በእስር ቤት ይጠበቅ ነበር፤ ቤተ ክርስቲያን ግን ስለ እርሱ ወደ አባታችን አጥብቃ ትጸልይ ነበር። 6ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበበት በዚያች ሌሊት፣ ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው እስር ቤቱን ይጠብቁ ነበር። 7ድንገትም የአባታችን መልአክ በአጠገቡ ቆመ፤ በእስር ቤቱም ውስጥ ብርሃን ሞላ። የጴጥሮስን ጎን መትቶ ቀሰቀሰውና፣ “ፈጥነህ ተነሥ” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ወደቁ። 8መልአኩም፣ “ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ” አለው። ጴጥሮስም እንዲሁ አደረገ። ከዚያም፣ “ልብስህን ደርበህ ተከተለኝ” አለው። 9ጴጥሮስም ወጥቶ ተከተለው፤ መልአኩ ያደረገው ነገር እውን መሆኑን ግን አላወቀም፤ ራእይ ያየ መስሎት ነበር። 10የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ጠባቂ አልፈው ወደ ከተማዋ ወደሚወስደው የብረት በር ደረሱ፤ በሩም በራሱ ተከፈተላቸው። ወጥተውም አንድ መንገድ ተጓዙ፤ ድንገትም መልአኩ ተለየው።
11ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፣ “አባታችን መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅ፣ የአይሁድ ሕዝብ ከጠበቁትም ሁሉ እንዳዳነኝ አሁን በርግጥ አወቅሁ” አለ። 12ይህንም አውቆ፣ ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ በዚያም ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ይጸልዩ ነበር። 13ጴጥሮስም የደጁን በር ባንኳኳ ጊዜ፣ ሮዳ የተባለች አገልጋይ ልጃገረድ ልትከፍት መጣች። 14የጴጥሮስንም ድምፅ አውቃ ከደስታዋ የተነሣ በሩን ሳትከፍት ወደ ውስጥ ሮጣ ገባች፤ ጴጥሮስም በደጁ ፊት እንደ ቆመ ተናገረች።
15እነርሱም፣ “አብደሻል” አሏት። እርሷ ግን እውነት መሆኑን አጥብቃ ተናገረች። እነርሱም፣ “መልአኩ ነው” አሉ። 16ጴጥሮስ ግን ያንኳኳ ነበር፤ በሩንም ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ። 17በእጁም ዝም እንዲሉ ጠቅሶ፣ አባታችን ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው ነገራቸው። “ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞችና ለእኅቶች ንገሩ” ብሎም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።
18በነጋም ጊዜ፣ ጴጥሮስ ምን እንደ ሆነ በወታደሮቹ መካከል ቀላል ያልሆነ ሁከት ተነሣ። 19ሄሮድስም ፈልጎ ባጣው ጊዜ፣ ጠባቂዎቹን መርምሮ እንዲገደሉ አዘዘ። ከዚያም ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
አባታችን ሄሮድስን ቀሠፈው
20ሄሮድስም በጢሮስና በሲዶና ሰዎች እጅግ ተቈጥቶ ነበር። እነርሱም በአንድነት ወደ እርሱ መጡ፤ የንጉሡን የግቢ አዛዥ ብላስጦስን አግባብተው ዕርቅን ለመኑ፤ ምክንያቱም አገራቸው ለምግብ በንጉሡ አገር ላይ ትመካ ነበርና። 21በተወሰነውም ቀን ሄሮድስ የመንግሥት ልብስ ለብሶ በዙፋኑ ተቀመጠ፤ ንግግርም አደረገላቸው። 22ሕዝቡም፣ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ይጮኽ ነበር። 23ክብርን ለአባታችን ስላልሰጠ፣ በዚያን ጊዜ የአባታችን መልአክ መታው፤ ትልም በልቶት ሞተ።
24የአባታችን ቃል ግን እያደገና እየተስፋፋ ሄደ። 25በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ፣ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ይዘው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ።