ጢሞቴዎስ ከተልእኮው ጋራ ተቀላቀለ
አብ ከመቄዶንያ በመጣ ሰው ራእይ ይጠራቸዋል። ልድያ ቤቷን ትከፍታለች፤ ጠንቋይ የሆነች ባሪያ ልጅ መንፈሷን ታጣለች፣ ጌቶቿም ገቢያቸውን ያጣሉ። ተደብድበውና በሰንሰለት ታስረው ጳውሎስና ሲላስ በእኩለ ሌሊት ይዘምራሉ፤ የምድር መናወጥ በሮቹን ይከፍታል፤ የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ይጠመቃል።
16 1ጳውሎስ ወደ ደርቤና ወደ ልስጥራ ሄደ። በዚያም ጢሞቴዎስ የተባለ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ አማኝ የሆነች የአይሁዳዊት ሴት ልጅ ነበር፤ አባቱ ግን ግሪካዊ ነበረ። 2በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክር ነበረው። 3ጳውሎስ ከእርሱ ጋራ አብሮ እንዲጓዝ ፈለገ፤ ስለዚህ በእነዚያ ስፍራ ስለ ነበሩት አይሁድ ወስዶ ገረዘው፤ አባቱ ግሪካዊ እንደ ነበረ ሁሉም ያውቁ ነበርና። 4በከተሞቹ ውስጥ እያለፉ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያሳለፉትን ውሳኔ እንዲጠብቁ ሰጧቸው። 5ስለዚህ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት ይጸኑ ነበር፤ ዕለት ዕለትም በቍጥር ይጨምሩ ነበር።
አባታችን ወደ መቄዶንያ ጠራቸው
6መንፈስ ቅዱስ በእስያ ቃሉን እንዳይናገሩ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ። 7ወደ ሚስያ በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ለመግባት ሞከሩ፤ የኢየሱስ መንፈስ ግን አልፈቀደላቸውም። 8ስለዚህ ሚስያን አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። 9ጳውሎስ በሌሊት ራእይ አየ፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” እያለ ይለምነው ነበር። 10ራእዩን ካየ በኋላ ወዲያውኑ ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ሞከርን፤ ምሥራቹን እንድንነግራቸው አባታችን እንደ ጠራን ተረድተን ነበርና።
ልድያ በፊልጵስዩስ ልቧን ከፈተች
11ስለዚህ ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ፣ በማግስቱም ወደ ናጶሊስ ተጓዝን፤ 12ከዚያም በመቄዶንያ የዚያ አውራጃ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው፣ የሮም ቅኝ ግዛት ወደ ሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ሄድን። በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጥን።
13በሰንበት ቀን የጸሎት ስፍራ ያለ መስሎን ከበሩ ውጭ ወደ ወንዝ ዳር ወጣን። ተቀምጠንም በዚያ ከተሰበሰቡት ሴቶች ጋራ ተነጋገርን። 14ከትያጥራ የመጣች፣ ሐምራዊ ጨርቅ የምትሸጥ፣ አባታችንን የምታመልክ ልድያ የተባለች ሴት ትሰማ ነበር። ጌታም ጳውሎስ የተናገረውን እንድታዳምጥ ልቧን ከፈተ። 15እርሷና ቤተ ሰቧ ከተጠመቁ በኋላ፣ “ለጌታ ታማኝ እንደ ሆንሁ ከቈጠራችሁኝ፣ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ተቀመጡ” ብላ ለመነችን። አሳመነችንም።
ስለ ወንጌል ታሰሩ
16ወደ ጸሎቱ ስፍራ ስንሄድ፣ የምዋርት መንፈስ ያደረባት አንዲት ባሪያ ልጃገረድ አገኘን፤ እርሷም በምዋርት ለጌቶቿ ብዙ ትርፍ ታስገኝ ነበር። 17እርሷም ጳውሎስንና እኛን ተከትላ፣ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር ባሪያዎች ናቸው፤ የድነትን መንገድ ይነግሯችኋል” እያለች ትጮኽ ነበር። 18ይህንም ብዙ ቀን አደረገች። ጳውሎስም እጅግ ተቸግሮ ዘወር ብሎ መንፈሱን፣ “ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው። በዚያም ቅጽበት ወጣ።
19ጌቶቿም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ጠፋ ባዩ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያው ወደ ገዦቹ ፊት ጎተቷቸው። 20ወደ ዳኞቹም አቅርበው፣ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን ያውካሉ፤ 21እኛ ሮማውያን እንድንቀበለውና እንድናደርገው ያልተፈቀደልንን ልማድ ያስተምራሉ” አሉ።
22ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፤ ዳኞቹም የጳውሎስንና የሲላስን ልብስ ገፈው በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። 23እጅግ ከደበደቧቸውም በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሏቸው፤ ወኅኒ ጠባቂውንም በጥብቅ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። 24እንዲህ ያለ ትእዛዝ ስለ ተቀበለ፣ በውስጠኛው ክፍል አስገብቶ ቈለፋቸው፤ እግሮቻቸውንም በግንድ አጠበቀ።
25እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ ይጸልዩ ነበር፤ ለአባታችንም መዝሙር ይዘምሩ ነበር፤ እስረኞቹም ያዳምጧቸው ነበር። 26ድንገትም ብርቱ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የወኅኒውም መሠረት ተናወጠ፤ ወዲያውኑ በሮቹ ሁሉ ተከፈቱ፤ የሁሉም ሰንሰለት ተፈታ። 27ወኅኒ ጠባቂውም ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒውን በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ። 28ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፣ “ሁላችንም እዚህ ነንና ራስህን አትጕዳ” ብሎ ጮኸ።
29ወኅኒ ጠባቂውም መብራት አስመጥቶ ወደ ውስጥ ሮጦ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ ፊት ወደቀ። 30ከዚያም ወደ ውጭ አውጥቶ፣ “ጌቶች ሆይ፣ እድን ዘንድ ምን ማድረግ አለብኝ?” አለ።
31እነርሱም፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰብህ ትድናላችሁ” አሉት። 32የጌታንም ቃል ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሁሉ ነገሩ። 33በዚያም የሌሊት ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበ፤ ወዲያውኑም እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ ተጠመቁ። 34ወደ ቤቱም አውጥቶ ምግብ አቀረበላቸው፤ በአባታችንም በማመኑ እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ እጅግ ደስ አላቸው።
35በነጋም ጊዜ ዳኞቹ ሎሌዎችን ልከው፣ “እነዚያን ሰዎች ፍታቸው” አሉ።
36ወኅኒ ጠባቂውም ጳውሎስን፣ “ዳኞቹ እንዲፈቷችሁ ትእዛዝ ልከዋል፤ አሁንም ውጡና በሰላም ሂዱ” አለው።
37ጳውሎስ ግን፣ “እኛ ሮማውያን ዜጎች ሆነን ሳለን ሳይፈርዱብን በሰው ፊት ደበደቡን፤ ወደ ወኅኒም ጣሉን። አሁንስ በስውር ሊያስወጡን ይፈልጋሉን? አይሆንም! እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን” አላቸው።
38ሎሌዎቹም ይህን ቃል ለዳኞቹ ነገሯቸው፤ እነርሱም ሮማውያን ዜጎች እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ። 39መጥተውም ይቅርታ ጠየቋቸው፤ አውጥተውም ከተማይቱን ለቀው እንዲሄዱ ለመኗቸው። 40ከወኅኒም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፤ በዚያም ወንድሞችን አይተው አበረታቷቸው፤ ከዚያም ሄዱ።