መሪዎች ኢየሱስን ለመግደል አሴሩ
አንዲት ሴት ውድ ሽቱ ታፈስሳለች፤ ስለዚህም ትወቀሳለች፤ ይሁዳ በሠላሳ ብር ይሸጠዋል። በጌቴሴማኒ ኢየሱስ ጽዋውን እንዲያርቅለት አብን ይለምናል፤ ወዳጆቹ ግን ደጋግመው ያንቀላፋሉ። ሲያዝ አይቃወምም። ጴጥሮስ ሰውየውን ፈጽሞ እንደማያውቀው ይምላል።
26 1ኢየሱስም ይህን ሁሉ ቃል ከተናገረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤
2“ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚመጣ ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል አሳልፎ ይሰጣል።”
3በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው ሊቀ ካህናት ግቢ ውስጥ ተሰበሰቡ፤ 4ኢየሱስንም በስውር ይዘው ሊገድሉት ተማከሩ። 5ነገር ግን፣ “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓሉ ጊዜ አይሁን” አሉ።
ለቀብር ኢየሱስን ቀባችው
6ኢየሱስም በቢታንያ፣ ለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣ 7አንዲት ሴት እጅግ ውድ የሆነ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ መጣች፤ በማዕድ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 8ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡ፤ “ይህ ብክነት ለምን ሆነ? 9ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድኆች ሊሰጥ ይችል ነበርና።”
10ኢየሱስም ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እርሷ መልካም ነገር አድርጋልኛለችና። 11ድኆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። 12ይህችን ሽቱ በሰውነቴ ላይ ባፈሰሰች ጊዜ፣ ለቀብር ልታዘጋጀኝ አደረገችው። 13እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት ስፍራ ሁሉ፣ እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያዋ ይነገራል።”
ይሁዳ ወልድን በብር አሳልፎ ሰጠ
14በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው፣ ወደ ካህናት አለቆች ሄደ፤ 15“አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ልትሰጡኝ ትፈልጋላችሁ?” አለ። እነርሱም ሠላሳ ብር ቈጥረው ሰጡት። 16ከዚያን ጊዜ ጀምሮም አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
ለፋሲካ መዘጋጀት
17በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።
18እርሱም እንዲህ አለ፤ “ወደ ከተማ ወደ እገሌ ሰው ሂዱና፣ ‘መምህሩ፣ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ፋሲካን ከደቀ መዛሙርቴ ጋር በቤትህ አከብራለሁ ይላል’ በሉት።”
19ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካንም አዘጋጁ።
20በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።
21ሲበሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ።
22እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው፣ “ጌታ ሆይ፣ በእርግጥ እኔ አይደለሁም?” አሉት።
23እርሱም መልሶ፣ “ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፣ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። 24የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ባይወለድ ኖሮ ለእርሱ ይሻለው ነበር።”
25አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም፣ “ረቢ ሆይ፣ በእርግጥ እኔ አይደለሁም?” አለ። እርሱም፣ “አንተ ራስህ ተናግረኻል” አለው።
26ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፣ “እንካችሁ፤ ብሉ፤ ይህ ሰውነቴ ነው” አለ። 27ጽዋም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸውና እንዲህ አለ፤ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ 28ይህ ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ነውና። 29እላችኋለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲሱን እስከምጠጣበት ቀን ድረስ፣ ይህን የወይን ፍሬ ከእንግዲህ አልጠጣም።”
30መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
ኢየሱስ የጴጥሮስን መካድ አስቀድሞ ተናገረ
31በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “በዚህች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ምክንያት ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና። 32ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ከእናንተ ቀድሜ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”
33ጴጥሮስም፣ “ሁሉም በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ፣ እኔ ከቶ አልሰናከልም” አለው።
34ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።
35ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ ቢያስፈልገኝ፣ ከቶ አልክድህም” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንዲሁ አሉ።
ወልድ ራሱን ለአብ አሳልፎ ሰጠ
36ከዚያም ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ መጣና ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደዚያ ሄጄ ስጸልይ፣ እናንተ በዚህ ተቀመጡ” አላቸው።
37ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ከእርሱ ጋር ይዞ ሄደ፤ እጅግም ማዘንና መጨነቅ ጀመረ።
38በዚያን ጊዜም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ በኀዘን ተውጣለች፤ በዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው።
39ጥቂትም ወደ ፊት አልፎ በፊቱ ተደፋ፤ ሲጸልይም፣ “አባቴ ሆይ፣ ቢቻልስ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልግ ሳይሆን አንተ እንደምትፈልግ ይሁን” አለ።
40ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጥቶ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም፣ “እንዲህ ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? 41ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስስ ይፈቅዳል፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”
42ዳግመኛም ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ፣ ይህ ጽዋ ካልጠጣሁት በቀር ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፣ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ።
43ዳግመኛም መጥቶ ተኝተው አገኛቸው፤ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። 44ትቶአቸውም እንደ ገና ሄደ፤ ያንኑ ቃል ደግሞ እየተናገረ ለሦስተኛ ጊዜ ጸለየ።
45ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እስካሁን ተኝታችሁ ታርፋላችሁን? እነሆ፣ ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ አሳልፎ ይሰጣል። 46ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”
ኢየሱስ አሳልፎ ተሰጠ ተያዘም
47እርሱም ገና ሲናገር፣ እነሆ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ፣ ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች ተልከው ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሕዝብ አስከትሎ ድንገት መጣ። 48አሳልፎ የሚሰጠውም፣ “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 49ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ረቢ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” አለና ሳመው።
50ኢየሱስም፣ “ወዳጄ ሆይ፣ የመጣህበትን አድርግ” አለው። ከዚያም ቀርበው ኢየሱስን ይዘው ያዙት።
51እነሆም፣ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘ፤ የሊቀ ካህናቱንም አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠ።
52በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፤ “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። 53አባቴን መለመን እንደማልችል ይመስልሃልን? እርሱም ወዲያው ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበልጡ መላእክትን ይልክልኝ ነበር። 54ነገር ግን እንዲህ ሊሆን እንደሚገባ የሚናገረው መጽሐፍ እንዴት ይፈጸማል?”
55በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ወንበዴ ለመያዝ እንደምትወጡ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር አልያዛችሁኝም። 56ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው።” በዚያን ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።
ኢየሱስ በከሳሾቹ ፊት
57ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። 58ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ ወደ ውስጥም ገብቶ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ለማየት ከጠባቂዎቹ ጋር ተቀመጠ።
59የካህናት አለቆችና ሸንጎው ሁሉ ኢየሱስን ለመግደል በእርሱ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ 60ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም አላገኙም። በመጨረሻም ሁለት ሰዎች ቀረቡና፣ 61“ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ መሥራት እችላለሁ’ ብሎ ተናገረ” አሉ።
62ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ፣ “ምንም መልስ የለህምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድር ነው?” አለው። 63ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ ንገረን” አለው።
64ኢየሱስም፣ “አንተ ራስህ ተናግረኻል። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለው።
65ያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀደደና፣ “ተሳድቦአል! ከእንግዲህ ምስክሮች ለምን ያስፈልጉናል? እነሆ፣ ስድቡን አሁን ሰማችሁ። 66ፍርዳችሁ ምንድር ነው?” አለ። እነርሱም መልሰው፣ “ሞት ይገባዋል” አሉ።
67ከዚያም በፊቱ ላይ እንትፍ አሉ፤ በጡጫም መቱት፤ አንዳንዶችም በጥፊ መትተው፣ 68“አንተ ክርስቶስ፣ የመታህ ማን እንደ ሆነ ትንቢት ተናገርልን!” አሉ።
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደማያውቅ ካደ
69ጴጥሮስም በውጭ በግቢው ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።
70እርሱ ግን በሁሉም ፊት፣ “የምትዪውን አላውቅም” ብሎ ካደ።
71ወደ በሩም ሲወጣ ሌላ ገረድ አየችውና በዚያ ላሉት፣ “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች።
72እርሱም ዳግመኛ፣ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ በመሐላ ካደ።
73ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው፣ “አነጋገርህ ይገልጥሃልና፣ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት።
74ያን ጊዜም ራሱን እየረገመ፣ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ መማል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።
75ጴጥሮስም ኢየሱስ፣ “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የተናገረውን ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።