ንጉሥ ስግደትን ጠየቀ
ዘጠና ጫማ ቁመት ያለው የወርቅ ምስልና የሙዚቃ ጓድ አምልኮን ግዴታ ያደርጋሉ። ሦስት የይሁዳ ሰዎች እምቢ ብለው ለንጉሡ እጅግ ዋጋ የሚያስከፍለውን መልስ ይሰጣሉ፤ አብ ሊያድነን ይችላል፤ ባያድነን እንኳ ግን አንሰግድም። አራተኛ ሰው ከእነርሱ ጋር በእሳቱ ውስጥ ይመላለሳል።
3 1ናቡከደነፆር የተባለው ንጉሥ የወርቅ ምስል ሠራ፤ ቁመቱ ዘጠና ጫማ ያህል፣ ስፋቱም ዘጠኝ ጫማ ነበር፤ በባቢሎን አውራጃ በዱራ ሜዳ ላይ አቆመው። 2ንጉሡ ናቡከደነፆር መሳፍንቱን፣ ሹማምቱን፣ አገረ ገዦቹን፣ አማካሪዎቹን፣ ግምጃ ቤት ጠባቂዎቹን፣ ዳኞቹን፣ ፈራጆቹንና የአውራጃውን ባለሥልጣናት ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ እንዲመጡ ላከ። 3ከዚያም መሳፍንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹ፣ አማካሪዎቹ፣ ግምጃ ቤት ጠባቂዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ፈራጆቹና የአውራጃው ባለሥልጣናት ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ያቆመውን ምስል ለመመረቅ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆር ባቆመውም ምስል ፊት ቆሙ።
4ከዚያም አዋጅ ነጋሪው በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ዐወጀ፤ “ወገኖች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ሆይ፤ የታዘዛችሁት ይህ ነው፦ 5የቀንደ መለከቱን፣ የእምቢልታውን፣ የበገናውን፣ የመሰንቆውን፣ የክራሩን፣ የዋሽንቱንና የሁሉንም ሙዚቃ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ስገዱ። 6ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ወዲያውኑ በሚነድደው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”
7ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ የቀንደ መለከቱን፣ የእምቢልታውን፣ የበገናውን፣ የመሰንቆውን፣ የክራሩንና የሁሉንም ዓይነት ሙዚቃ ድምፅ እንደ ሰሙ፣ ወገኖች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ሁሉ ተደፍተው ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ።
8በዚያን ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቆጣሪዎች ቀርበው አይሁድን በክፋት ከሰሱ። 9ንጉሡንም ናቡከደነፆርን እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ኑር! 10ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ዐወጅክ፦ የቀንደ መለከቱን፣ የእምቢልታውን፣ የበገናውን፣ የመሰንቆውን፣ የክራሩን፣ የዋሽንቱንና ማንኛውንም ሙዚቃ ድምፅ የሚሰማ ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፤ 11ተደፍቶ የማይሰግድም ሁሉ በሚነድደው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣል። 12አንተ በባቢሎን አውራጃ ላይ የሾምሃቸው አንዳንድ አይሁድ፣ ይኸውም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፣ ንጉሥ ሆይ፤ አንተን ቸል ብለውሃል። አማልክትህን አያገለግሉም፤ ላቆምኸው የወርቅ ምስልም አይሰግዱም።”
13ናቡከደነፆርም እጅግ ተቈጥቶ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እንዲመጡ አዘዘ፤ እነርሱም በንጉሡ ፊት ቀረቡ። 14ናቡከደነፆርም እንዲህ አለ፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጎ፤ አማልክቴን የማታገለግሉ፣ ላቆምሁትም የወርቅ ምስል የማትሰግዱ መሆናችሁ እውነት ነውን? 15አሁንም ዝግጁ ከሆናችሁ፦ የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የበገና፣ የመሰንቆ፣ የክራር፣ የዋሽንትና የሁሉም ዓይነት ሙዚቃ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ እኔ ለሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው። ባትሰግዱ ግን ወዲያውኑ በሚነድደው የእሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ። ከእጄስ የሚያድናችሁ የትኛው አምላክ ነው?”
16ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም ለንጉሡ መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ ስለዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አያስፈልገንም። 17የምናገለግለው አባታችን ሊያድነን ቢችል፣ ንጉሥ ሆይ፤ ከሚነድደው እቶንና ከእጅህ ያድነናል። 18ባይሆንም እንኳ፣ ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዕወቅ፦ አማልክትህን አናገለግልም፤ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል አንሰግድም።”
19ከዚያም ናቡከደነፆር እጅግ ተቈጥቶ በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ ላይ የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ እቶኑም ከወትሮው ይልቅ ሰባት ዕጥፍ እንዲጋል አዘዘ። 20ከጭፍሮቹም እጅግ ኀይለኛ የሆኑ አንዳንዶቹ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው በሚነድደው እቶን ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ። 21ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ቀሚስ፣ ሱሪ፣ ጥምጥምና ሌላ ልብስ ለብሰው ታስረው በሚነድደው የእሳት እቶን ውስጥ ተጣሉ። 22የንጉሡ ትእዛዝ ጥብቅ፣ የእቶኑም ትኩሳት ያይል ስለ ነበር፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ያነሡትን ሰዎች የእሳቱ ነበልባል ገደላቸው። 23እነዚህም ሦስት ሰዎች፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፣ እንደ ታሰሩ በሚነድደው እቶን ውስጥ ወደቁ።
24ከዚያም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደንቆ ፈጥኖ ተነሣ። አማካሪዎቹንም፣ “በእሳቱ ውስጥ የጣልናቸው የታሰሩ ሦስት ሰዎች አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም ለንጉሡ፣ “እውነት ነው ንጉሥ ሆይ” ብለው መለሱ።
25እርሱም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ሳይታሰሩ በእሳቱ መካከል ሲመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አልተነኩም፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል።” a a v25 ንጉሡ በነበልባሉ ውስጥ አራተኛ አካል አየ፤ ይህም አገልጋዮቹን በእሳቱ ውስጥ ብቻቸውን ያልተወ የአባታችን አዳኝ መገኘት ነበር።
26ናቡከደነፆርም ወደሚነድደው እቶን በር ቀርቦ፣ “የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፤ ወደዚህ ውጡ!” አለ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም ከእሳቱ ወጡ።
27መሳፍንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚህ ሰዎች ሰውነት ላይ ኀይል እንዳልነበረው አዩ፤ የራሳቸው ጠጕር አልተለበለበም፤ ልብሳቸውም አልተነካም፤ የእሳት ሽታም አልነበረባቸውም።
28ናቡከደነፆርም እንዲህ አለ፤ “የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ! መልአኩን ልኮ በእርሱ የታመኑትን አገልጋዮቹን አዳነ። የንጉሡን ትእዛዝ ተላልፈዋል፤ ከራሳቸው አምላክ በቀር ሌላ አምላክ ከማገልገል ወይም ከመስገድ ሞትን መርጠዋል። 29እኔም እንዲህ ብዬ ዐወጅኩ፦ የሲድራቅን፣ የሚሳቅንና የአብደናጎን አምላክ የሚሳደብ ማንኛውም ወገን፣ ሕዝብ ወይም ቋንቋ ቍራጭ ቍራጭ ይደረጋል፤ ቤቶቻቸውም ፍርስራሽ ይሆናሉ፤ እንደዚህ ሊያድን የሚችል ሌላ አምላክ የለምና።”
30ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።