ሰላም ያጣ ንጉሥ
ናቡከደነፆር ጠቢባኑ ትርጉሙን ብቻ ሳይሆን ሕልሙን ራሱ እንዲነግሩት ይጠይቃል፤ ሊነግሩት ባልቻሉ ጊዜም ሁሉንም ሞት ይፈርድባቸዋል። ዳንኤል ጊዜ ይለምናል፤ ወዳጆቹም ከአብ ምሕረትን እንዲለምኑ ይማጸናቸዋል፤ ከአራት ዓይነት ብረቶች የተሠራ ምስል በእጅ ባልተፈነቀለ ድንጋይ ሲደቅቅም ይገልጻል።
2 1ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፤ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። 2ንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ጠንቋዮች፣ አስማተኞች፣ መተተኞችና ኮከብ ቆጣሪዎች እንዲጠሩ አዘዘ። እነርሱም መጥተው በንጉሡ ፊት ቆሙ። 3ንጉሡም እንዲህ አላቸው፤ “ሕልም አልሜአለሁ፤ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኳል።”
4ኮከብ ቆጣሪዎቹም በአራማይክ ቋንቋ ለንጉሡ እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ሕልሙን ለባሪያዎችህ ንገረን፤ እኛም ትርጓሜውን እንገልጣለን።”
5ንጉሡም ኮከብ ቆጣሪዎቹን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ትእዛዜ ጸንቷል፤ ሕልሙንና ትርጓሜውን ባትነግሩኝ ቍራጭ ቍራጭ ትሆናላችሁ፤ ቤቶቻችሁም ፍርስራሽ ይሆናሉ። 6ሕልሙንና ትርጓሜውን ብትነግሩኝ ግን ከእኔ ዘንድ ስጦታ፣ ዋጋና ታላቅ ክብር ትቀበላላችሁ። ስለዚህ ሕልሙንና ትርጓሜውን ንገሩኝ።”
7ዳግመኛም መልሰው፤ “ንጉሡ ሕልሙን ለባሪያዎቹ ይንገር፤ እኛም ትርጓሜውን እንሰጣለን” አሉ።
8ንጉሡም መልሶ እንዲህ አለ፤ “ትእዛዜ እንደ ጸና ስለምታዩ፣ ጊዜ ልታራዝሙ እንደምትፈልጉ በርግጥ ዐውቃለሁ፤ 9ሕልሙን ባትነግሩኝ ለእናንተ ፍርዱ አንድ ብቻ ነው። ጊዜው እስኪለወጥ ድረስ በፊቴ ሐሰተኛና የበሰበሰ ቃል ለመናገር ተስማምታችኋል። ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ያን ጊዜም ትርጓሜውን ልትገልጡ እንደምትችሉ ዐውቃለሁ።”
10ኮከብ ቆጣሪዎቹም ንጉሡን መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሡ የሚጠይቀውን ሊያደርግ የሚችል በምድር ላይ ማንም የለም። እንዲህ ያለውን ነገር ከማንኛውም ጠንቋይ፣ አስማተኛ ወይም ከለዳዊ የጠየቀ ታላቅና ኃያል ንጉሥ ከቶ የለም።
11ንጉሡ የጠየቀው ነገር እጅግ ከባድ ነው፤ በሟች ሰዎች መካከል የማይኖሩ አማልክት ብቻ ለንጉሡ ሊገልጡለት ይችላሉ።”
12በዚህም ንጉሡ ተቆጣ፤ እጅግም ተበሳጨ፤ የባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ እንዲጠፉ አዘዘ። 13ትእዛዙም ጠቢባኑን ለመግደል ወጣ፤ ዳንኤልንና ጓደኞቹንም ይገድሏቸው ዘንድ ፈለጓቸው።
14ያን ጊዜ የባቢሎንን ጠቢባን ለመግደል ለወጣው ለንጉሡ የዘበኞች አለቃ ለአርዮክ ዳንኤል በጥበብና በማስተዋል መለሰለት። 15የንጉሡን ሹም አርዮክን፤ “ይህ ጭካኔ የተሞላበት ትእዛዝ ከንጉሡ ለምን ወጣ?” ብሎ ጠየቀው። አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል ገለጠለት። 16ስለዚህ ዳንኤል ገብቶ ትርጓሜውን ለንጉሡ ይገልጥ ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ለመነ።
17ከዚያም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄዶ ነገሩን ለጓደኞቹ ለሐናንያ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገራቸው፤ 18ዳንኤልና ጓደኞቹ ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋራ እንዳይጠፉ፣ ስለዚህ ምስጢር በሰማይ ካለው አባታችን ዘንድ ምሕረትን እንዲለምኑ አሳሰባቸው። 19ያን ጊዜ ምስጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፤ ዳንኤልም በሰማይ ያለውን አባታችን ባረከ። 20ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ “የአባታችን ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን፤ ጥበብና ኃይል የእርሱ ናቸውና። 21እርሱ ዘመናትንና ወቅቶችን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያስወግዳል፤ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ለጠቢባን ጥበብን፣ ለአስተዋዮችም ዕውቀትን ይሰጣል። 22እርሱ ጥልቅና ድብቅ የሆነውን ነገር ይገልጣል፤ በጨለማ ውስጥ ያለውን ያውቃል፤ ብርሃንም ከእርሱ ጋራ ይኖራል።
23የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ ጥበብንና ኃይልን ሰጥተኸኛልና አመሰግንሃለሁ፤ አከብርሃለሁም፤ አሁንም የለመንንህን ነገር ገልጠህልኛል፤ የንጉሡንም ነገር ገልጠህልናል።”
ዳንኤል መልሱን አመጣ
24ስለዚህ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲያጠፋ ንጉሡ ወደ ሾመው ወደ አርዮክ ሄዶ እንዲህ አለው፤ “የባቢሎንን ጠቢባን አታጥፋ። ወደ ንጉሡ አግባኝ፤ እኔም ትርጓሜውን እነግረዋለሁ።”
25አርዮክም ዳንኤልን ፈጥኖ ወደ ንጉሡ ፊት አገባና፤ “ለንጉሡ ትርጓሜውን ሊነግር የሚችል ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አገኘሁ” አለ።
26ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን፤ “ያየሁትን ሕልምና ትርጓሜውን ልትነግረኝ ትችላለህን?” ብሎ ጠየቀው።
27ዳንኤልም ንጉሡን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ንጉሡ የሚጠይቀውን ምስጢር ሊገልጡ የሚችሉ ጠቢባን፣ አስማተኞች፣ ጠንቋዮች ወይም ኮከብ ቆጣሪዎች የሉም።
28በሰማይ ያለው አባታችን ግን ምስጢርን ይገልጣል፤ በኋለኛው ዘመንም የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቋል። በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ያየኸው ሕልምና በልቡናህ የታዩህ ራእዮች እነዚህ ናቸው፤ a a v28 “የኋለኛው ዘመን” ማለት እግዚአብሔር የዘላለም መንግሥቱን ከማቋቋሙ በፊት ያለውን የታሪክ የመጨረሻ ዘመን ያመለክታል።
29“ንጉሥ ሆይ፤ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ሐሳብህ ወደ ፊት ስለሚመጣው ነገር ዞረ፤ ምስጢርን የሚገልጠውም የሚሆነውን አሳየህ።
30ይህ ምስጢር የተገለጠልኝ ከሕያዋን ሁሉ የበለጠ ጥበብ ስላለኝ ሳይሆን፤ ንጉሡ ትርጓሜውን እንዲያውቅ፣ አንተም የልብህን ሐሳብ እንድታስተውል ነው።
31“ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ተመለከትህ፤ ታላቅ ምስልም አየህ። ይህ ምስል ታላቅና በጣም የሚያበራ ሆኖ በፊትህ ቆመ፤ መልኩም የሚያስፈራ ነበር።
32የምስሉ ራስ ጥሩ ወርቅ ነበር፤ ደረቱና ክንዶቹ ብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ናስ ነበሩ፤ 33ባቶቹ ብረት ነበሩ፤ እግሮቹ በከፊል ብረት፣ በከፊልም ሸክላ ነበሩ።
34ስትመለከትም፤ ያለ እጅ የተቈረጠ ድንጋይ የምስሉን የብረትና የሸክላ እግሮች መታ፤ ቀጠቀጣቸውም። b b v34 በሰው እጅ ሳይሆን የተቈረጠው ድንጋይ ምድርን ሁሉ የሚሞላ ተራራ ይሆናል — ይህም አባታችን በኢየሱስ በኩል የሚያቋቁመው፣ ከቶ የማይጠፋና ለሌላ ሰው ከቶ የማይተላለፍ መንግሥት ነው።
35ያን ጊዜም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ በአንድነት ተሰባበሩ፤ በበጋ አውድማ ላይ እንዳለ ገለባም ሆኑ። ነፋስም ወስዶ አንዳች ዱካ ሳያስቀር አወጣቸው። ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ የሚሞላ ታላቅ ተራራ ሆነ።
36“ሕልሙ ይህ ነበር። አሁንም ለንጉሡ ትርጓሜውን እንነግራለን።
37ንጉሥ ሆይ፤ አንተ በሰማይ ያለው አባታችን መንግሥትን፣ ሥልጣንን፣ ኃይልንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ ነህ።
38ሰዎችን ሁሉ፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ በእጅህ ሰጥቷል፤ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል። አንተ የወርቁ ራስ ነህ።
39“ከአንተ በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ የናስ ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል።
40አራተኛው መንግሥት እንደ ብረት ብርቱ ይሆናል፤ ብረት ሁሉን ነገር ይሰብራል፤ ያደቅቃልም፤ ብረትም ይህን ሁሉ እንደሚቀጠቅጥ፣ እርሱ ይሰብራቸዋል፤ ይቀጠቅጣቸዋልም።
41እግሮቹንና ጣቶቹን በከፊል የሸክላ ሠሪ ሸክላ፣ በከፊልም ብረት ሆነው እንዳየሃቸው፤ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረት ከለስላሳ ሸክላ ጋራ ተደባልቆ እንዳየኸው፣ ከብረቱ ጥንካሬ የተወሰነ ይኖረዋል።
42ጣቶቹ በከፊል ብረት፣ በከፊልም ሸክላ እንደ ነበሩ፣ መንግሥቱም በከፊል ብርቱ፣ በከፊልም ተሰባሪ ይሆናል።
43ብረት ከለስላሳ ሸክላ ጋራ ተደባልቆ እንዳየኸው፣ ሕዝቡ በጋብቻ ይደባለቃሉ፤ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋራ እንደማይደባለቅ፣ አይተሳሰሩም።
44“በእነዚያ ነገሥታት ዘመን በሰማይ ያለው አባታችን ከቶ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል፤ ግዛቱም ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። ይህን ሁሉ መንግሥት ይቀጠቅጣል፤ ያጠፋቸዋልም፤ እርሱ ግን ለዘላለም ይኖራል።
45ራእዩ ያመለከተው ይህ ነው፤ በሰው እጅ ሳይሆን ከተራራ የተቈረጠው ድንጋይ ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ሰባበረ። ታላቁ አባታችን ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል። ሕልሙ የተረጋገጠ፣ ትርጓሜውም የታመነ ነው።”
በአባታችን ፊት የተዋረደ ንጉሥ
46ያን ጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደ፤ መባና ዕጣንም እንዲቀርብለት አዘዘ።
47ንጉሡም ዳንኤልን እንዲህ አለው፤ “ይህን ምስጢር ልትገልጥ ስለ ቻልህ፣ በርግጥ አምላክህ የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ጌታና ምስጢርን ገላጭ ነው።”
48ከዚያም ንጉሡ ዳንኤልን ወደ ከፍተኛ ክብር ከፍ አደረገው፤ ብዙ ታላላቅ ስጦታዎችንም ሰጠው፤ የባቢሎንም ሁሉ አውራጃ ገዥ፣ በጠቢባኑም ሁሉ ላይ ዋና አለቃ አደረገው። 49ዳንኤልም ንጉሡን ለመነ፤ ንጉሡም ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ጒዳዮች ላይ ሾመ፤ ዳንኤል ግን በንጉሡ ቤተ መንግሥት ቀረ።