ፍላጎቱ ለእኔ ነው
ሰውየው ጫማ ካጠለቁት እግሮቿ እስከ ጠጕሯ ድረስ ያመሰግናታል፤ በእርሷ በግልጽ ይደሰታል። እርሷ ይህን አትገፋውም። ፍቅሩ የጋራና የራሷም እንደ ሆነ ትናገራለች፤ ከዚያም ለእርሱ ፍሬ ወዳስቀመጠችበት ወደ ወይን ቦታዎችና ወደ መንደሮች ይዛው ትወጣለች።
7 1በጫማ ውስጥ ያሉ እግሮችሽ እንዴት ውብ ናቸው፤ የመኳንንት ልጅ ሆይ! የጭኖችሽ ውበት እንደ ጌጥ፣ የተዋጣለት ባለሙያ እጅ ሥራ ነው። 2እምብርትሽ የተቀላቀለ ወይን የማይታጣበት ክብ ጽዋ ነው። ሆድሽ በአበቦች የተከበበ የስንዴ ክምር ነው። 3ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለት ግልገሎች፣ እንደ ዋላ መንታዎች ናቸው። 4አንገትሽ ከዝሆን ጥርስ እንደ ተሠራ ግንብ ነው። ዓይኖችሽ በባትረቢም በር አጠገብ ያሉ በሔሽቦን ኩሬዎች ናቸው። አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው። 5ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ዘውድ ሆኖሻል፤ የተንዠረገገ ጠጕርሽ እንደ ሐምራዊ ነው፤ ንጉሥ በዘለላው ተማርኳል። 6ፍቅሬ ሆይ፣ በደስታሽ ሁሉ እንዴት ውብ፣ እንዴትስ ደስ የምታሰኝ ነሽ! 7ቁመትሽ እንደ ዘንባባ ዛፍ ነው፣ ጡቶችሽም እንደ ዘለላዎቹ ናቸው። 8እንዲህ አልሁ፤ “ዘንባባውን ዛፍ እወጣለሁ፣ ፍሬውንም እይዛለሁ።” ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላዎች ይሁኑ፣ የትንፋሽሽም መዓዛ እንደ ፖም ይሁን፣ 9አፍሽም እንደ ምርጥ ወይን ይሁን። ለውዴ ለስለስ ብሎ ይፈስሳል፣ በከንፈርና በጥርስ ላይ ረጋ ብሎ ይንሸራተታል።
10እኔ የውዴ ነኝ፣ ፍላጎቱም ለእኔ ነው። 11ውዴ ሆይ፣ ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ፣ በመንደሮችም እናድር። 12ማለዳ ወደ ወይኑ ተክል እንሂድ፤ የወይኑ ተክል ማቆጥቆጡን፣ አበቦቹ መፍካታቸውን፣ ሮማኖቹም ማበባቸውን እንይ። በዚያ ፍቅሬን እሰጥሃለሁ። 13ዱዳኢሞች መዓዛቸውን ይሰጣሉ፤ በበሮቻችን ላይም ውዴ ሆይ፣ ለአንተ ያከማቸኋቸው አዲሱና አሮጌው ምርጥ ፍሬዎች ሁሉ አሉ። a a v13 ዱዳኢሞች በጥንቱ ዓለም የፍቅር ፍላጎትን እንደሚቀሰቅሱና የመውለድ ኀይልን እንደሚያበረታቱ በሰፊው ይታመንባቸው የነበሩ መዓዛ ያላቸው ተክሎች ነበሩ።