እኔ የውዴ ነኝ
የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት እንዲፈልጉት ሊረዷት ይቀርባሉ፤ እርሷም ወዴት እንደ ሄደ እንደምታውቅ ትመልሳለች። ሰውየው ያመሰግናታል፤ ስድሳ ንግሥታትና ቍጥር የሌላቸው ሴቶች አሉ፤ እርሷ ግን አሁንም አንዲት ብቻ ናት። ከዚያም ተመልካቾች ሱላማጢስን ያዩአት ዘንድ ተመለሺ ብለው ይጠሯታል።
6 1ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ ውብ የሆንሽ ሆይ፣ ውድሽ ወዴት ሄደ? ከአንቺ ጋራ እንድንፈልገው ውድሽ በየትኛው መንገድ ሄደ?
2ውዴ ወደ አትክልቱ ስፍራ፣ ወደ ሽቱ ዕፅዋት መደብ ወርዷል፤ በአትክልት ስፍራዎች መካከል ሊሰማራ፣ ሱፍ አበቦችንም ሊለቅም ሄዷል።
3እኔ የውዴ ነኝ፤ ውዴም የእኔ ነው፤ እርሱ በሱፍ አበቦች መካከል ይሰማራል።
4ውዳጄ ሆይ፣ እንደ ቲርሳ ውብ ነሽ፤ እንደ ኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነሽ፤ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ያዘ ሰራዊት የምታስፈሪ ነሽ። a a v4 ቲርሳ በውበትዋ የተመሰገነች ጥንታዊት የንጉሥ ከተማ ነበረች፤ እዚህም ከከተሞች ሁሉ እጅግ ተወዳጅ እንደ ሆነች ከኢየሩሳሌም ጋራ ተጣምራለች።
5ዐይኖችሽን ከእኔ መልሺ፤ ያሸንፉኛልና። ጠጕርሽ ከገለዓድ ተራራ እንደ ወረደ የፍየሎች መንጋ ነው። 6ጥርሶችሽ ከመታጠቢያ እንደ ወጡ የበጎች መንጋ ናቸው፤ ሁሉም መንታ የወለዱ ናቸው፤ ከእነርሱም መካከል ልጁን ያጣ አንድም የለም። 7ጕንጮችሽ ከመሸፈኛሽ በስተ ኋላ እንደ ተሰነጠቀ የሮማን ፍሬ ናቸው።
8ስድሳ ንግሥታትና ሰማንያ ቁባቶች አሉ፤ ቍጥር የሌላቸው ወጣት ሴቶችም አሉ፤ 9ርግቤ፣ ፍጽምቴ ግን ብቸኛዪቱ ናት፤ የእናትዋ አንዲት ልጅ፣ ለወለደቻት ተወዳጅ ናት። ወጣት ሴቶች አይተዋት ብፅዕት አሏት፤ ንግሥታትና ቁባቶችም አመሰገኗት።
10ይህች እንደ ጎህ የምትወጣ፣ እንደ ጨረቃ ውብ የሆነች፣ እንደ ፀሐይ የምታበራ፣ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ያዘ ሰራዊት የምታስፈራ ማን ናት?
11የሸለቆውን አበቦች ለማየት፣ ወይኑ ማቈጥቈጡንና ሮማኑም ማበቡን ለማየት ወደ ለውዝ አትክልት ወረድሁ።
12ሳላውቀው ምኞቴ በተከበረው ሕዝቤ ሰረገላዎች መካከል አኖረኝ።
13ተመለሺ፣ ተመለሺ፣ ሱላማዊት ሆይ፤ እንድንመለከትሽ ተመለሺ፣ ተመለሺ። ሱላማዊትን እንደ ሁለቱ ሰፈሮች ጭፈራ ለምን ትመለከታላችሁ? b b v13 ‹የሁለቱ ሰፈሮች ጭፈራ› የተባለው በሁለት ትይዩ ተመልካቾች ረድፎች መካከል የሚከናወን ውብ ሰልፍን ያሳያል።