ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት
ሙሴና አሮን ፈርዖንን በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርጉ ይጠይቃሉ፤ እርሱም ይህን እግዚአብሔር እንደማያውቅ ይነግራቸዋል። ገለባ ይከለከላል የጡቡ ቁጥር ግን ይጠበቃል፤ አለቆች ይደበደባሉ፤ እስራኤልም ሙሴን ይወቅሳሉ። ሙሴ ተመልሶ አብን ለምን እንደ ላከው ይጠይቃል።
5 1ከዚያም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው፣ “የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ በምድረ በዳ በዓል ያከብሩልኝ ዘንድ ልቀቃቸው” አሉት።
2ፈርዖንም፣ “ድምፁን ሰምቼ እስራኤልን እንድለቅ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቀውም፤ እስራኤልንም አልለቅም” አለ።
3እነርሱም፣ “የዕብራውያን አባታችን ተገናኝቶናል፤ ለአባታችን መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሂድ፤ አለዚያ በመቅሠፍት ወይም በሰይፍ ይመታናል” አሉ።
4የግብፅ ንጉሥ ግን፣ “ሙሴና አሮን፣ ሕዝቡን ከሥራቸው ለምን ትጐትታላችሁ? ወደ ሥራችሁ ተመለሱ!” አላቸው። 5ፈርዖንም፣ “እነሆ፣ የምድሪቱ ሕዝብ አሁን በዝተዋል፤ እናንተም ከሥራ ልታሳርፏቸው ትፈልጋላችሁ!” አለ።
6ፈርዖንም በዚያኑ ዕለት የባሪያ ሹማምቱንና በሕዝቡ ላይ የተሾሙትን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዘ፤ 7“እንደ ቀድሞው ሕዝቡ ለጡብ ገለባ አትስጧቸው፤ ሄደው ራሳቸው ገለባ ይሰብስቡ።
8እንደ ቀድሞው ያንኑ የጡብ ልክ ጣሉባቸው፤ አታሳንሱትም። ሰነፎች ናቸው፤ ስለዚህ ነው፣ ‘ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት እናቅርብ’ ብለው የሚጮኹት። 9በሰዎቹ ላይ ሥራውን አክብዱባቸው፤ እንዲሠሩበትና ለውሸት ቃል ትኵረት እንዳይሰጡ።”
10የባሪያ ሹማምቱና አለቆቹም ወጥተው ሕዝቡን፣ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፤ ‘ከእንግዲህ ገለባ አልሰጣችሁም። 11ሄዳችሁ ባገኛችሁበት ስፍራ ሁሉ ለራሳችሁ ገለባ ፈልጉ፤ ሆኖም ሥራችሁ ከቶ አይቀነስም’” አሏቸው። 12ስለዚህ ሕዝቡ ለገለባ ፍሳሽ ለመሰብሰብ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። 13የባሪያ ሹማምቱም፣ “ገለባ በነበራችሁ ጊዜ እንዳደረጋችሁት፣ የየዕለቱን ልካችሁን ጨርሱ” እያሉ ይወተውቷቸው ነበር። 14የፈርዖን የባሪያ ሹማምት የሾሙአቸው የእስራኤል አለቆችም ተደበደቡ፤ “ለምን እንደ ቀድሞው ትናንትም ሆነ ዛሬ የጡብ ልካችሁን አልጨረሳችሁም?” ተባሉ።
15ከዚያም የእስራኤል አለቆች መጥተው ወደ ፈርዖን እንዲህ ሲሉ ጮኹ፤ “አገልጋዮችህን ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? 16ለአገልጋዮችህ ገለባ አይሰጥም፤ ይሁን እንጂ፣ ‘ጡብ ሥሩ!’ ይሉናል። እነሆ፣ አገልጋዮችህ ይደበደባሉ፤ በደሉ ግን የገዛ ሕዝብህ ነው” አሉ።
17ፈርዖንም፣ “ሰነፎች! ሰነፎች ናችሁ! ስለዚህ ነው፣ ‘ሄደን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እናቅርብ’ የምትሉት። 18አሁን ሂዱ፣ ሥሩ። ገለባ አይሰጣችሁም፤ ይሁን እንጂ ሙሉ የጡብ ልካችሁን ማስረከብ አለባችሁ” አለ።
19የእስራኤል አለቆችም፣ “የየዕለቱን የጡብ ልካችሁን አታሳንሱ” በተባሉ ጊዜ፣ በመከራ ውስጥ መሆናቸውን ተገነዘቡ። 20ከፈርዖን ዘንድ በወጡ ጊዜ፣ ሊገናኟቸው ሲጠብቁ የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አገኟቸው፤ 21እንዲህም አሏቸው፤ “እኛን ሊገድሉን ሰይፍ በእጃቸው በማስያዝ፣ በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት የተጠላን እንድንሆን አድርጋችሁናልና አባታችን ይመልከታችሁ፤ ይፍረድባችሁም።”
22ከዚያም ሙሴ ወደ አባታችን ተመልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ አባት ሆይ፣ በዚህ ሕዝብ ላይ ለምን መከራ አመጣህ? እኔንስ ለምን ላክኸኝ?
23በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከሄድሁ ጀምሮ፣ በዚህ ሕዝብ ላይ ክፉ አድርጓል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንህም።”