የሙሴ ፍርሃት
ሙሴ ይከራከራል፦ አያምኑኝም፤ አንደበቴ ኮልታፋ ነው፤ ሌላ ሰው ላክ። እባብ የሚሆን በትር፣ ለምጽ የሚይዝና የሚነጻ እጅ፣ በመጨረሻም አፉ እንዲሆን አሮን ይሰጠዋል። እስራኤል የአብ በኩር ልጅ ነው፤ ፈርዖንም ሊለቀው ይገባል።
4 1ሙሴም መልሶ፣ “ነገር ግን አያምኑኝም፤ ድምፄንም አይሰሙም፤ ‘አባታችን አልተገለጠልህም’ ይላሉና” አለ።
2አባታችንም፣ “በእጅህ ያለው ይህ ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፣ “በትር ነው” አለ።
3እርሱም፣ “ወደ ምድር ጣለው” አለ። ወደ ምድርም ጣለው፤ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከፊቱ ሸሸ።
4አባታችን ግን ሙሴን፣ “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዝ” አለው፤ እጁንም ዘርግቶ ያዘው፤ በእጁም በትር ሆነ። 5“ይህም የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው አባትህ እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው።”
6አባታችንም፣ “እጅህን በመጎናጸፊያህ ውስጥ አግባ” አለው። እርሱም እንዳለው አደረገ፤ ባወጣትም ጊዜ እጁ የቈዳ በሽታ ይዟት እንደ በረዶ ነጭ ሆና ነበር።
7እርሱም፣ “እጅህን መልሰህ በመጎናጸፊያህ ውስጥ አግባ” አለው። እርሱም አደረገ፤ ባወጣትም ጊዜ እንደ ሌላው ሥጋው ተመልሳ ዳነች።
8“ባያምኑህና የፊተኛውን ምልክት ድምፅ ባይሰሙ፣ የኋለኛውን ምልክት ያምናሉ። 9እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑና ድምፅህን ባይሰሙ፣ ከዓባይ ወንዝ ውሃ ወስደህ በደረቁ ምድር ላይ አፍስስ፤ ከዓባይ የወሰድኸው ውሃ በደረቁ ምድር ላይ ደም ይሆናል።”
10ሙሴ ግን አባታችንን፣ “ጌታዬ አባት ሆይ፣ እባክህ፤ ባሪያህን ከመናገርህ በፊትም ሆነ ከተናገርህ ወዲህ ከቶ በንግግር የተካንሁ ሰው አልሆንሁም፤ በመናገር የቸገርሁ፣ አንደበቴም ኰልታፋ ነውና” አለ።
11አባታችንም፣ “ለሰው አፍ የሰጠው ማን ነው? ድዳ ወይም ደንቆሮ፣ የሚያይ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማን ነው? አባትህ እኔ አይደለሁምን? 12አሁንም ሂድ፤ እኔም ከአፍህ ጋራ እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው።
13እርሱ ግን፣ “ጌታዬ አባት ሆይ፣ እባክህ፤ ሌላ ሰው ላክ” አለ።
14የአባታችንም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ እንዲህም አለ፤ “ወንድምህ ሌዋዊው አሮን አይደለምን? እርሱ በሚገባ እንደሚናገር ዐውቃለሁ። እነሆ፣ እርሱ ራሱ ሊቀበልህ እየወጣ ነው፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። 15ተናገረው፤ ቃሉንም በአፉ አኑር፤ እኔም ከአፍህና ከአፉ ጋራ እሆናለሁ፤ የምታደርጉትንም ሁለታችሁን አስተምራችኋለሁ። 16እርሱ ስለ አንተ ለሕዝቡ ይናገራል፤ አፍህ ይሆንልሃል፤ አንተም ለእርሱ እንደ አምላክ ትሆነዋለህ። 17ይህችንም በትር በእጅህ ያዝ፤ በእርስዋም ምልክቶቹን ታደርጋለህ” አለው።
ሙሴና ዮቶር ተለያዩ
18ሙሴም ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ፣ “እባክህ፣ በግብፅ ወዳሉት ወንድሞቼ ልመለስና በሕይወት መኖራቸውን ልይ” አለው። ዮቶርም፣ “በሰላም ሂድ” አለው።
19አባታችንም በምድያም ሳለ ሙሴን፣ “ነፍስህን ይፈልጉ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ወደ ግብፅ ተመለስ” አለው።
20ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወስዶ በአህያ ላይ አስቀመጣቸው፤ ወደ ግብፅ ምድርም ተመለሰ። ሙሴም የአባታችንን በትር በእጁ ያዘ።
21አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ግብፅ በተመለስህ ጊዜ፣ እንድታደርግ ኀይል የሰጠሁህን ተኣምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት አድርግ። እኔ ግን ልቡን አደነድነዋለሁ፤ ሕዝቡንም አይለቅም። 22ለፈርዖንም እንዲህ ትለዋለህ፤ ‘አባታችን እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ a a v22 እስራኤል ሕዝብ ከመሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ አባታችን ይህን ሕዝብ የበኵር ልጁ ብሎ ጠራው፤ ይህም ወደ ራሱ የሚሰበስበው ቤተ ሰብ የመጀመሪያው ጥቆማ ነው፤ እውነተኛው በኵር ኢየሱስ ለልጆቹ ሁሉ ወደ ቤት የሚመለሱበትን መንገድ ሲከፍት ተፈጸመ። 23አንተንም እንዲህ እልሃለሁ፤ ያገለግለኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ፤ ልትለቀው ባትፈቅድ፣ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ’” አለው።
24በመንገድ ላይ ባለው ማደሪያ፣ አባታችን ተገናኘው፤ ሊገድለውም ፈለገ። b b v24 ይህ አጭርና ምስጢራዊ ትእይንት፣ ሙሴ ለልጁ ቸል ባለው የኪዳን ምልክት በሆነው በግርዛት ላይ ያጠነጥናል። የሲጶራ ፈጣን ተግባር፣ ሙሴ የአባታችንን ሕዝብ ከመምራቱ በፊት ቤተ ሰቡን ወደ ኪዳኑ ይመልሳል። 25ሲጶራም ስለታም ድንጋይ ወስዳ የልጅዋን ሸለፈት ቈረጠች፤ በሙሴም እግር ላይ አስነካችው፤ “አንተ ለእኔ በእርግጥ የደም ሙሽራ ነህ” አለች።
26አባታችንም ሙሴን ተወው። በዚያን ጊዜም እርስዋ ስለ ግርዛቱ፣ “የደም ሙሽራ” አለች።
27አባታችንም አሮንን፣ “በምድረ በዳ ሙሴን ልትቀበለው ሂድ” አለው። እርሱም ሄደ፤ በአባታችን ተራራ ላይ ተገናኘው፤ ሳመውም።
28ሙሴም አባታችን እንዲያደርስ የሰጠውን ቃል ሁሉ፣ እንዲያደርግም ያዘዘውን ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው። 29ሙሴና አሮንም ሄደው የእስራኤልን ሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። 30አሮንም አባታችን ለሙሴ የተናገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፤ በሕዝቡም ፊት ምልክቶቹን አደረገ። 31ሕዝቡም አመነ። አባታችን የእስራኤልን ሕዝብ ሊረዳ እንደ መጣ፣ መከራቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፣ ራሳቸውን አዘንብለው ሰገዱ።