ኢየሱስ በተራራ ላይ ያስተምራል
ኢየሱስ በተራራ ላይ ተቀምጦ የሚያዝኑትን፣ የዋሆችንና የሚሰደዱትን ብፁዓን ይላቸዋል፤ ከዚያም ትእዛዛቱን ወደ ውስጥ ይገፋቸዋል፦ ከመግደል አልፎ ወደ ቁጣ፣ ከምንዝር አልፎ ወደ ማየት፣ ከመሐላ አልፎ ወደ ግልጽ ንግግር። ልጆችን አባታቸውን አብን እንዲመስሉ የሚያደርጋቸው ጠላቶችን መውደድ ነው።
5 1ኢየሱስም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ መጡ። 2አፉንም ከፍቶ እንዲህ ሲል ያስተምራቸው ጀመር፦ a a v2 በተራራው ስብከት ሁሉ ላይ፣ ኢየሱስ ተከታዮቹን እርሱ ራሱ ወደሚያውቀው ከአብ ጋራ ወዳለው ቅርበት ይስባቸዋል፤ ደጋግሞም “በሰማይ ያለው አባታችሁ” እያለ ይናገራል።
3“በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ የአባታችን መንግሥት የእነርሱ ናትና። 4የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና። 5የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። 6ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና። 7መሐሪዎች ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና። 8ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ አባታችንን ያዩታልና። 9የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፤ የአባታችን ልጆች ይባላሉና። 10ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ የአባታችን መንግሥት የእነርሱ ናትና።
11“ሰዎች ስለ እኔ ብለው በሚሰድቧችሁ፣ በሚያሳድዷችሁና በእናንተ ላይ ክፉውን ሁሉ በሐሰት በሚናገሩባችሁ ጊዜ ብፁዓን ናችሁ። 12ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
እናንተ ጨውና ብርሃን ናችሁ
13“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ። ጨው ጣዕሙን ቢያጣ ግን እንደ ገና በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰዎች ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
14“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ የተቀመጠች ከተማ ልትሰወር አትችልም። 15ማንም መብራት አብርቶ ከዕንቅብ በታች አያስቀምጥም፤ ነገር ግን በቤት ውስጥ ላሉ ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 16እንዲሁ ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ፣ ብርሃናችሁ በፊታቸው ይብራ።
ወልድ ሕግን ይፈጽማል
17“ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። 18እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፉ ድረስ፣ ሁሉም እስኪፈጸም ድረስ፣ ከሕግ አንዲት ፊደል ቢሆን አንዲት ነጥብ አታልፍም። 19ስለዚህ ከእነዚህ ከታናናሾቹ ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽርና ሌሎችን እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ቢሆን በአባታችን መንግሥት ታናሽ ይባላል፤ የሚጠብቃቸውና የሚያስተምራቸው ግን በአባታችን መንግሥት ታላቅ ይባላል። 20እላችኋለሁና፤ ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ በቀር፣ ወደ አባታችን መንግሥት ከቶ አትገቡም።
አስቀድመህ ከወንድምህ ጋራ ታረቅ
21“ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የሚገድል ሁሉ ለፍርድ ይጋለጣል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 22እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ለፍርድ ይጋለጣል። ወንድሙን የሚሰድብ ለሸንጎ ይጋለጣል፤ ‘አንተ ሞኝ!’ የሚል ደግሞ ለእሳት ገሃነም ይጋለጣል።
23“ስለዚህ ስጦታህን በመሠዊያው ላይ ስታቀርብ፣ ወንድምህ በአንተ ላይ የያዘው ነገር እንዳለ በዚያ ብታስታውስ፣ 24ስጦታህን በዚያ በመሠዊያው ፊት ተወው፤ አስቀድመህ ሄደህ ከወንድምህ ጋራ ታረቅ፤ ከዚያም መጥተህ ስጦታህን አቅርብ። 25ከከሳሽህ ጋራ በመንገድ ላይ ሳለህ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ለዳኛው አሳልፎ ይሰጥህ ይሆናል፤ ዳኛውም ለሎሌው፣ አንተም ወደ ወኅኒ ትጣል ይሆናል። 26እውነት እልሃለሁ፤ የመጨረሻውን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።
ንጽሕና ከልብ ይጀምራል
27“‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 28እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት በፍትወት የሚመለከት ሁሉ፣ በልቡ አስቀድሞ ከእርሷ ጋራ አመንዝሯል። 29ቀኝ ዐይንህ የሚያሰናክልህ ከሆነ፣ አውጥተህ ከአንተ ጣለው፤ ሰውነትህ ሁሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካልህ አንዱ ቢጠፋ ይሻልሃልና። 30ቀኝ እጅህ ኀጢአት እንድትሠራ የሚያደርግህ ከሆነ፣ ቈርጠህ ከአንተ ጣለው፤ ሰውነትህ ሁሉ ወደ ገሃነም ከሚገባ ይልቅ ከአንተ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና።
31“ደግሞም፣ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍች ጽሑፍ ይስጣት’ ተብሏል። 32እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ስለ ዝሙት ካልሆነ በቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።
አዎ ያልኸው አዎ ይሁን
33“ደግሞም ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘መሐላህን አታፍርስ፤ ለአባታችን ፈጽመው’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 34እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሁን፤ የአባታችን ዙፋን ነውና፤ 35በምድርም አይሁን፤ የእግሩ መረገጫ ነውና፤ በኢየሩሳሌምም አይሁን፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና። 36በራስህም አትማል፤ አንዲትን ጠጉር እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። 37‘አዎ’ ያላችሁት ‘አዎ’፣ ‘አይሆንም’ ያላችሁትም ‘አይሆንም’ ይሁን፤ ከዚህ የሚበልጠው ከክፉው ነው።
ከዐይን ስለ ዐይን አልፋችሁ ሂዱ
38“‘ዐይን ስለ ዐይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 39እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉ ሰውን አትቃወሙ። ቀኝ ጕንጭህን በጥፊ የሚመታህ ቢኖር፣ ሌላውንም ጕንጭህን አዙርለት። 40ሊከስህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ የሚፈልግ ቢኖር፣ ካባህንም ተውለት። 41ማንም አንድ ምዕራፍ ሂድ ብሎ ቢያስገድድህ፣ ከእርሱ ጋራ ሁለት ሂድ። 42የሚለምንህን ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚፈልገውን አትከልክል።
እርሱ እንደሚወድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ
43“‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህንም ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 44እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፤ 45በሰማይ ያለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ፀሐዩን በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ያወጣልና፤ ዝናቡንም በጻድቃንና በዐመፀኞች ላይ ያዘንባልና። 46የሚወዷችሁን ብትወዱ፣ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮች እንኳ እንዲሁ አያደርጉምን? 47ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ፣ ከሌሎች ይልቅ ምን ትበልጣላችሁ? አሕዛብ እንኳ እንዲሁ አያደርጉምን? 48ስለዚህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ፣ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።”