አባታችን ድምፁን ይልካል
ዮሐንስ በምድረ በዳ ይሰብካል፤ ሰዎችም በእውነት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ደጋግመው ይጠይቁታል፦ ልብስን አካፍሉ፣ ከተወሰነው በላይ አትውሰዱ፣ አትቀሙ። የሄሮድስን ኃጢአት በስሙ ይጠራል፤ በዚህም ይታሰራል። ኢየሱስ ከሌሎቹ ሁሉ ጋር ይጠመቃል፤ አብም የሚወደው ልጁ ብሎ ይጠራዋል።
3 1በጢባርዮስ ቄሳር በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ ጶንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ በነበረ ጊዜ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛ ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያና የጥራኮኒዶስ አገር ገዥ፣ ልሳንዮስም የሳብለኔ ገዥ በነበሩ ጊዜ፣ 2ሐናና ቀያፋ ሊቀ ካህናት በነበሩበት ዘመን፣ የአባታችን ቃል በምድረ በዳ ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ መጣ። 3ለኀጢአትም ይቅርታ የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ፣ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ ተዘዋወረ፤ 4በነቢዩ በኢሳይያስ የቃላት መጽሐፍ ተጽፎ እንዳለ፦ “በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጎዳናውንም አቅኑ። 5ሸለቆ ሁሉ ይሞላል፤ ተራራና ኮረብታም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው መንገድ ይቀናል፤ ሻካራውም መንገድ ይስተካከላል፤ 6ሥጋ ለባሽም ሁሉ የአባታችንን ማዳን ያያል።”
7ዮሐንስም በእርሱ ሊጠመቁ ወደ እርሱ ለሚመጣው ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አስጠነቀቃችሁ? 8እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ‘አብርሃም አባታችን ነው’ ማለትን በልባችሁ አትጀምሩ፤ አባታችን ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣ እንደሚችል እነግራችኋለሁና። 9አሁንም ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል።”
10ሕዝቡም፣ “እንግዲህ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።
11እርሱም መልሶ፣ “ሁለት ሸሚዝ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንደዚሁ ያድርግ” አላቸው።
12ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፣ ምን እናድርግ?” አሉት።
13እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ አትሰብስቡ” አላቸው።
14ወታደሮችም፣ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ማንንም በኀይል አትበዝብዙ፤ በሐሰትም አትክሰሱ፤ በደመወዛችሁ ረኩ” አላቸው።
15ሕዝቡም በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፤ ሁሉም ምናልባት ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ ይሆንን በልባቸው ያስቡ ነበር። 16ዮሐንስ ለሁሉም መልሶ እንዲህ አለ፦ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ የጫማውን ማሰሪያ ልፈታ አይገባኝም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። 17መንሹ በእጁ ነው፤ አውድማውን ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥላል።”
18ዮሐንስም በሌሎች በብዙ የምክር ቃላት ለሕዝቡ ወንጌልን ሰበከ። 19አራተኛው ክፍል ገዥ የነበረው ሄሮድስ ግን ስለ ወንድሙ ሚስት ስለ ሄሮድያዳ፣ ስላደረገውም ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ገሠጸው፤ 20ሄሮድስም ከሁሉ በላይ ይህን ጨመረ፤ ዮሐንስን በወኅኒ አስሮ ዘጋው።
አባታችን ልጁን የተወደደ ይለዋል
21ሕዝቡ ሁሉ በተጠመቁ ጊዜ፣ ኢየሱስም ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፤
22መንፈስ ቅዱስም እንደ ርግብ በአካል መልክ በእርሱ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም ድምፅ መጥቶ፦ “አንተ የተወደድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” አለ።
23ኢየሱስም አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ነበር፤ እንደሚመስለውም የዮሴፍ ልጅ ነበር፤ ዮሴፍም የኤሊ ልጅ፣ 24የማጣት ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣ የሜልኪ ልጅ፣ የያናይ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ 25የማታትዮስ ልጅ፣ የአሞጽ ልጅ፣ የናሆም ልጅ፣ የኤስሊ ልጅ፣ የናጌ ልጅ፣ 26የማአት ልጅ፣ የማታትዮስ ልጅ፣ የሰሜይን ልጅ፣ የዮሴክ ልጅ፣ የዮዳ ልጅ፣ 27የዮሐና ልጅ፣ የሬሳ ልጅ፣ የዘሩባቤል ልጅ፣ የሰላትያል ልጅ፣ የኔሪ ልጅ፣ 28የሜልኪ ልጅ፣ የአዲ ልጅ፣ የቆሳም ልጅ፣ የኤልማዳም ልጅ፣ የዔር ልጅ፣ 29የኢያሱ ልጅ፣ የኤሊዔዘር ልጅ፣ የዮሪም ልጅ፣ የማጣት ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣ 30የስምዖን ልጅ፣ የይሁዳ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ የዮናም ልጅ፣ የኤልያቄም ልጅ፣ 31የሜልያ ልጅ፣ የሜና ልጅ፣ የማታታ ልጅ፣ የናታን ልጅ፣ የዳዊት ልጅ፣ 32የእሴይ ልጅ፣ የእዮቤድ ልጅ፣ የቦዔዝ ልጅ፣ የሰልሞን ልጅ፣ የነአሶን ልጅ፣ 33የአሚናዳብ ልጅ፣ የአድሚን ልጅ፣ የአርኒ ልጅ፣ የኤስሮን ልጅ፣ የፋሬስ ልጅ፣ የይሁዳ ልጅ፣ 34የያዕቆብ ልጅ፣ የይስሐቅ ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ፣ የታራ ልጅ፣ የናኮር ልጅ፣ 35የሴሮሕ ልጅ፣ የራግው ልጅ፣ የፋሌቅ ልጅ፣ የዔቦር ልጅ፣ የሳላ ልጅ፣ 36የቃይናን ልጅ፣ የአርፋክስድ ልጅ፣ የሴም ልጅ፣ የኖኅ ልጅ፣ የላሜሕ ልጅ፣ 37የማቱሳላ ልጅ፣ የሄኖክ ልጅ፣ የያሬድ ልጅ፣ የመላልኤል ልጅ፣ የቃይናን ልጅ፣ 38የሄኖስ ልጅ፣ የሴት ልጅ፣ የአዳም ልጅ፣ የአባታችን ልጅ።