ወልድ በምድረ በዳ ተፈተነ
ኢየሱስ ከአርባ ቀን በኋላ ተርቦ ሳለ ለዲያብሎስ ከመጽሐፍ ይመልሳል፦ አብን ብቻ አምልክ። በአገሩ ምኵራብ ኢሳይያስን ያነብባል፤ ዛሬ ተፈጸመ ይላል፤ ያው ሕዝብም ከገደል ሊወረውረው ይሞክራል። በሌላ ስፍራ አጋንንት ስሙን ይጠራሉ፤ እርሱም ዝም ያሰኛቸዋል፤ ድውያንም ይፈወሳሉ።
4 1ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ ሞልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በመንፈስም እየተመራ በምድረ በዳ ሄደ። 2አርባ ቀንም በዲያብሎስ ሲፈተን ቈየ፤ በእነዚያ ቀናትም ምንም አልበላም፤ ባለቁም ጊዜ ተራበ።
3ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ ይህ ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ” አለው።
4ኢየሱስም መልሶ፣ “‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው።
5ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ላይ ወሰደውና በቅጽበት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ አሳየው። 6አለውም፣ “ይህን ሥልጣን ሁሉና ክብራቸውን እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥቶአልና ለምፈልገውም እሰጠዋለሁ። 7እንግዲህ አንተ ብትሰግድልኝ ሁሉም ያንተ ይሆናል።”
8ኢየሱስም መልሶ፣ “‘ለአባትህ ትሰግዳለህ፤ እርሱንም ብቻ ታመልካለህ’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው።
9ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደውና በቤተ መቅደሱ ጫፍ ላይ አቁሞ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ ከዚህ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ 10‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል፤ ይጠብቁህም ዘንድ’ ተብሎ ተጽፎአልና፤ 11ደግሞም ‘በእጆቻቸውም ያነሡሃል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል’ ተብሎአል።”
12ኢየሱስም መልሶ፣ “‘አባትህን አትፈታተን’ ተብሎአል” አለው።
13ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ እስከ አመቺ ጊዜ ድረስ ከእርሱ ተለየ።
የአብ ልጅ በኀይል ተመለሰ
14ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ሁሉ ተሰማ። 15በምኵራቦቻቸውም አስተማረ፤ ሁሉም አከበሩት።
16ወዳደገባትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባና ሊያነብ ቆመ። 17የነቢዩም የኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም ዘርግቶ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፦
18“የአባታችን መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኆች ወንጌልን እንድሰብክ ቀብቶኛልና። ለተማረኩት መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እንዳውጅ፣ የተገፉትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤ 19የአባታችንን የሞገስ ዓመት እንዳውጅ።” a a v19 ዕዳ የሚሰረዝበትን፣ ምርኮኞች ነጻ የሚወጡበትን፣ መሬትም የሚመለስበትን የኢዮቤልዩ ዓመት ያመለክታል።
20ጥቅልሉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ። በምኵራብ የነበሩ ሁሉ ዐይኖቻቸውን ትኵር አድርገው ተመለከቱት።
21እርሱም እንዲህ ሊላቸው ጀመረ፤ “ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ።”
22ሁሉም መሰከሩለት፤ ከአፉም በሚወጣው በጸጋ ቃል ተደነቁ፤ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” አሉም።
23እርሱም፣ “በርግጥ፣ ‘ሐኪም ሆይ፣ ራስህን ፈውስ’ የሚለውን ምሳሌ ትጠቅሱልኛላችሁ፤ በቅፍርናሆም ተደረገ ብለን የሰማነውን እዚህም በትውልድ አገርህ አድርግ ትሉኛላችሁ” አላቸው። 24ደግሞም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት የለውም። 25ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማዩ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በተዘጋ ጊዜ፣ በምድሪቱም ሁሉ ታላቅ ራብ በወደቀ ጊዜ፣ በኤልያስ ዘመን በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ 26ኤልያስ ግን ከእነርሱ ወደ አንዱም እንኳ አልተላከም፤ በሲዶና ዘረፋት ወደምትኖር መበለት እንጂ። 27በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመን በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ማንም አልነጻም።”
28በምኵራብ የነበሩ ሁሉ ይህን ሲሰሙ እጅግ ተቈጡ። 29ተነሥተውም ከከተማ አስወጡት፤ ገደል ሊጥሉትም ከተማቸው ወደ ተሠራችበት ተራራ ዳር ወሰዱት። 30እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስን ዝም አሰኘ
31ወደ ገሊላ ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር። 32ቃሉ ሥልጣን ስለ ነበረው በትምህርቱ ተደነቁ። 33በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያለበት ሰው ነበር፤ በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ 34ወዮ! የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፣ ከአንተ ጋራ ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ነህ።
35ኢየሱስም፣ “ዝም በልና ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በሁሉ ፊት ጥሎት ምንም ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ።
36ሁሉም ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፣ “ይህ ምን ዐይነት ቃል ነው? ርኩሳን መናፍስትን በሥልጣንና በኀይል ያዝዛል፤ እነርሱም ይወጣሉ!” ተባባሉ። 37ዝናውም በአካባቢው ባለው ስፍራ ሁሉ ተሰማ።
አባታችን በልጁ በኩል ይፈውሳል
38ተነሥቶም ከምኵራብ ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖን አማት በጽኑ ትኵሳት ታማ ነበር፤ ስለ እርሷም ለመኑት። 39በእርሷም ላይ ቆሞ ትኵሳቱን ገሠጸው፤ ለቀቃትም፤ ወዲያውም ተነሥታ ታገለግላቸው ጀመር። 40ፀሐይም ስትጠልቅ፣ በተለያየ ደዌ የታመሙ ያሏቸው ሁሉ ወደ እርሱ አመጧቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። 41ከብዙዎችም አጋንንት፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ እየጮኹ ወጡ። እርሱም ክርስቶስ መሆኑን ያውቁ ስለ ነበር ዝም አሰኛቸው፤ እንዳይናገሩም ከለከላቸው።
42ሲነጋም ወጥቶ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ሄደ። ሕዝቡም ፈለጉት፤ ወደ እርሱም መጥተው ከእነርሱ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ሞከሩ።
43እርሱ ግን፣ “ለሌሎች ከተሞችም የአባታችንን መንግሥት ወንጌል ማወጅ ይገባኛል፤ የተላክሁት ለዚህ ነውና” አላቸው።
44በይሁዳም ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።