ስለ ማሰናከያና ስለ ይቅርታ
በቀን ሰባት ጊዜ ይቅር በሉ። የዘር ቅንጣት የምታህል እምነት በቂ ናት። ግዴታቸውን የሚፈጽሙ አገልጋዮች ምስጋና አይጠይቁም። ዐሥር ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ከእነርሱም አንዱ ሳምራዊው አብን እያመሰገነ ይመለሳል። መንግሥቱ «እዚህ ናት» ተብሎ የሚጠቆም አይደለችም፤ እርሷ አሁንም በመካከላቸው ናት።
17 1ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርም፤ ነገር ግን በእርሱ በኩል ለሚመጣው ሰው ወዮለት! 2ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ፣ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣልበት ይሻለዋል።
3“ራሳችሁን ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድል ገሥጸው፤ ንስሐ ቢገባም ይቅር በለው። 4በቀን ውስጥ ሰባት ጊዜ ቢበድልህ፣ ሰባት ጊዜም ተመልሶ ‘ንስሐ ገብቻለሁ’ ቢልህ፣ ይቅር በለው።”
5ሐዋርያትም ጌታን፣ “እምነታችንን ጨምርልን!” አሉት።
6ጌታም እንዲህ አለ፤ “እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን የሾላ ዛፍ ‘ተነቅለህ በባሕር ተተከል’ ብትሉት፣ ይታዘዛችሁ ነበር። 7ከእናንተ መካከል የሚያርስ ወይም በጎች የሚጠብቅ ባሪያ ያለው ማን ነው፣ ከዕርሻ ሲገባ ‘ፈጥነህ መጥተህ በማዕድ ተቀመጥ’ የሚለው? 8ከዚህ ይልቅ ‘እራቴን አሰናዳ፤ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ ከዚያም አንተ ትበላለህ፤ ትጠጣለህ’ አይለውም?
9“ባሪያው የታዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? 10እናንተም እንደዚሁ የታዘዛችሁትን ሁሉ ካደረጋችሁ በኋላ፣ ‘የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፤ የሚገባንን ብቻ ነው ያደረግነው’ በሉ።”
አባታችን ዐሥር ለምጻሞችን ፈወሰ
11ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ፣ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ። 12ወደ አንድ መንደር ሲገባ፣ ለምጽ ያለባቸው ዐሥር ሰዎች ተገናኙት። ርቀውም ቆሙ፤
13ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፣ “ኢየሱስ ጌታ ሆይ፣ ማረን!” ብለው ጮኹ።
14ባያቸውም ጊዜ፣ “ሄዳችሁ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። ሲሄዱም ነጹ።
15ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ፣ ድምፁን ከፍ አድርጎ አባታችንን እያመሰገነ ተመለሰ፤ 16በኢየሱስም እግር ሥር በግንባሩ ተደፋ፤ አመሰገነውም። እርሱም ሳምራዊ ነበር።
17ኢየሱስም፣ “ዐሥሩ አልነጹምን? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ? 18ከዚህ መጻተኛ በቀር፣ ተመልሶ ለአባታችን ክብር የሚሰጥ ማንም አልተገኘምን?” 19እርሱንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
መንግሥቱ አስቀድሞ በመካከላችሁ ነው
20ፈሪሳውያን የአባታችን መንግሥት መቼ እንደምትመጣ በጠየቁት ጊዜ፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “የአባታችን መንግሥት በምትታይ ምልክት አትመጣም፤ 21‘እነሆ፣ እዚህ ናት!’ ወይም ‘እዚያ ናት!’ ተብሎም አይባልም፤ የአባታችን መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።”
22ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “የሰው ልጅ ከሚገለጥባቸው ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ዘመን ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩትም። 23‘እነሆ፣ እዚያ ነው!’ ወይም ‘እነሆ፣ እዚህ ነው!’ ይሏችኋል፤ አትሂዱ፤ አትከተሏቸውም። 24መብረቅ ብልጭ ብሎ ከሰማይ ዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በቀኑ እንዲሁ ይሆናል። 25ነገር ግን አስቀድሞ ብዙ መከራ ሊቀበል፣ በዚህም ትውልድ ሊጣል ያስፈልገዋል። 26በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንዲሁ ይሆናል። 27ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋት ውሃም መጥቶ ሁሉንም አጠፋ። 28በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይገዙ፣ ይሸጡ፣ ይተክሉ፣ ይሠሩ ነበር፤ 29ነገር ግን ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን፣ እሳትና ዲን ከሰማይ ዘነበ፤ ሁሉንም አጠፋ፤ 30የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል። 31በዚያ ቀን፣ በሰገነት ላይ ያለ ሰው ዕቃው በቤት ውስጥ ቢሆንም ሊወስደው አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ያለ ሰው ወደ ኋላ አይመለስ። 32የሎጥን ሚስት አስቡ። 33ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ነፍሱን የሚያጠፋ ግን ጠብቆ ያኖራታል። 34እላችኋለሁ፣ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ላይ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፣ ሌላው ይቀራል። 35ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች።” a a v35 የጥንቶቹ ቅጂዎች እዚህ ላይ ቍጥር 36 የላቸውም፤ የኋለኞቹ ቅጂዎች ግን፣ “ሁለት ሰዎች በዕርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፣ ሌላው ይቀራል” የሚለውን ይጨምራሉ።
37እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፣ የት?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “በድን ባለበት ሁሉ፣ አሞራዎች በዚያ ይሰበሰባሉ” አለ።