ዕውር ሆኖ የተወለደው ሰው
ከተወለደ ጀምሮ ዕውር የነበረ ሰው በጭቃ ይቀባል፣ ይታጠባል፣ ያያልም፤ በዚህም የአብ ሥራዎች በእርሱ ይገለጣሉ። ሁለት ጊዜ ሲጠየቅ ከቃሉ ፈቀቅ አይልም፤ ዕውር ነበርሁ፣ አሁን አያለሁ። ምኩራብ ያወጣዋል፣ ኢየሱስ ያገኘዋል፣ ማየታቸውን እርግጠኛ የሆኑትም ዕውሮች ናቸው።
9 1ኢየሱስ ሲያልፍ፣ ከተወለደ ጀምሮ ዕውር የነበረን ሰው አየ። 2ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፣ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው፤ እርሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት።
3“ይህ ሰውም ቢሆን ወላጆቹም ኀጢአት አልሠሩም፤” ሲል ኢየሱስ መለሰ፤ “ነገር ግን የአባታችን ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ይህ ሆነ። a a v3 ኢየሱስ የሰውየውን ዕውርነት የኀጢአት ቅጣት አድርጎ ለማየት እምቢ አለ። ይልቁንም ዓለም ውድቀትን ብቻ ወዳየበት ስፍራ የማዳን ሥራው ወደሚገለጥበት ወደ አባታችን ይጠቁማል። 4ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ልንሠራ ይገባናል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። 5በዓለም ሳለሁ፣ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”
6ይህን ብሎ መሬት ላይ እንትፍ አለ፤ ከምራቁም ጭቃ አበጀ፤ ጭቃውንም በሰውየው ዓይኖች ላይ ቀባ።
7እርሱም፣ “ሂድ፤ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው (ትርጓሜውም የተላከ ማለት ነው)። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመለሰ።
8ጎረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ተቀምጦ ይለምን የነበረው ይህ አይደለምን?” አሉ። 9አንዳንዶች፣ “እርሱ ነው” አሉ። ሌሎች፣ “አይደለም፤ እርሱን ይመስላል እንጂ” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” ይል ነበር።
10ስለዚህ፣ “ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ብለው ጠየቁት።
11እርሱም መልሶ፣ “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ አበጀ፤ በዓይኖቼ ላይ ቀባ፤ ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ። እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ማየትም ቻልኩ” አለ።
12“እርሱ የት ነው?” አሉት። እርሱም፣ “አላውቅም” አለ።
13ቀድሞ ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14ኢየሱስ ጭቃውን ያበጀበትና ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። 15ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት ማየት እንደ ቻለ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም፣ “በዓይኖቼ ላይ ጭቃ አደረገ፤ እኔም ታጠብኩ፤ አሁንም አያለሁ” አላቸው።
16ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ ሰው እንዲህ ያለ ታምራት እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም መለያየት ሆነ።
17እንደ ገና ዕውሩን፣ “ዓይኖችህን ስለ ከፈተልህ፣ ስለ እርሱ አንተ ምን ትላለህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ነቢይ ነው” አለ።
18አይሁድ ማየት የቻለውን ሰው ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ፣ ዕውር እንደ ነበረና ማየት እንደ ቻለ አላመኑም ነበር። 19ወላጆቹንም፣ “ዕውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቋቸው።
20ወላጆቹም መልሰው፣ “ይህ ልጃችን እንደ ሆነና ዕውር ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን። 21ነገር ግን አሁን እንዴት እንደሚያይ አናውቅም፤ ዓይኖቹንም ማን እንደ ከፈተ አናውቅም። እርሱን ጠይቁት፤ ለአካለ መጠን የደረሰ ነውና ራሱ ይናገራል” አሉ። 22ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ስለ ፈሩ ነበር፤ ምክንያቱም ማንም ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ ቢመሰክር ከምኵራብ እንዲባረር አይሁድ ቀድሞውኑ ተስማምተው ነበር። b b v22 ከምኵራብ መባረር ከአይሁድ ማኅበረ ሰብ ፍጹም ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ መገለልን ያመለክት ነበር። 23ስለዚህ ነበር ወላጆቹ፣ “ለአካለ መጠን ደርሷል፤ እርሱን ጠይቁት” ያሉት።
24ስለዚህ ቀድሞ ዕውር የነበረውን ሰው እንደ ገና ጠርተው፣ “ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን” አሉት።
25እርሱም መልሶ፣ “ኀጢአተኛ ይሁን አይሁን አላውቅም፤ አንድ ነገር ግን አውቃለሁ፤ ዕውር ነበርኩ፤ አሁን ግን አያለሁ” አለ።
26“ምን አደረገልህ? ዓይኖችህንስ እንዴት ከፈተ?” አሉት።
27መልሶም፣ “አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም። ደግሞ ለምን መስማት ትፈልጋላችሁ? እናንተም ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው።
28እነርሱም ተሳድበው፣ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። 29እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረ እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ መጣ አናውቅም” አሉ።
30ሰውየውም መልሶ፣ “የሚያስደንቀው ነገር ይህ ነው፤ እርሱ ከወዴት እንደ መጣ አታውቁም፤ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። 31እግዚአብሔር ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ነገር ግን ማንም እግዚአብሔርን የሚፈራና ፈቃዱን የሚያደርግ ቢሆን፣ እግዚአብሔር ይሰማዋል። 32ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዓይኖች የከፈተ ሰው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ከቶ ተሰምቶ አያውቅም። 33ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ፣ ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር” አለ።
34እነርሱም መልሰው፣ “አንተ ሁለንተናህ በኀጢአት ተወለድክ፤ አሁንስ ታስተምረናለህን?” አሉት፤ አባረሩትም።
ታምናለህን?
35ኢየሱስም እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው።
36እርሱም መልሶ፣ “ጌታ ሆይ፣ በእርሱ አምን ዘንድ እርሱ ማን ነው?” አለ።
37ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ ከአንተ ጋራ የሚነጋገረውም እርሱ ነው” አለው።
38እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፣ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም።
39ኢየሱስም፣ “የማያዩ እንዲያዩ፣ የሚያዩም ዕውር እንዲሆኑ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጣሁ” አለ።
40ከእርሱ ጋራ የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያን ይህን ሰምተው፣ “እኛም ዕውሮች ነንን?” አሉ።
41ኢየሱስም፣ “ዕውሮች ብትሆኑ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን፣ ‘እናያለን’ ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ ይኖራል” አላቸው።