ለሰው ተስፋ አለውን?
የተቈረጠ ዛፍ የውኃ ሽታ ሲያገኝ እንደ ገና ያቈጠቍጣል፤ ሰው ግን ይተኛል፤ አይነሣምም። ኢዮብ ሙታን በሕይወት ይኖሩ እንደ ሆነ ያስባል። ቍጣው እስኪያልፍ ድረስ ተሰውሮ ከዚያም ተመልሶ እንደሚጠራ ያስባል። እግዚአብሔርም ውኃ ድንጋይን እንደሚሸረሽር ተስፋን ይሸረሽራል ይላል።
14 1“ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ ዐጭር፣ መከራውም የበዛ ነው። 2እንደ አበባ ይበቅልና ይረግፋል፤ እንደ ጥላ ይሸሻል፣ አይጸናም። 3እንደዚህ ባለ ሰው ላይ ዐይንህን ትተክላለህን? ከአንተ ጋራስ ወደ ፍርድ ታመጣኛለህን? 4ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ የሚችል ማን ነው? ማንም የለም። 5ዘመኑ የተወሰነ ስለሆነ፣ የወራቱም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፤ ሊያልፈው የማይችለውን ዳርቻ ወስነህለታል፤ 6ያርፍ ዘንድ ዐይንህን ከእርሱ ላይ መልስ፤ ቀኑን እንደ ቅጥር ሠራተኛ እስኪፈጽም ድረስ።
7“ለዛፍ ተስፋ አለው፦ ቢቈረጥ እንደ ገና ያቈጠቍጣል፤ ቡቃያውም አያቋርጥም። 8ሥሩ በመሬት ውስጥ ቢያረጅ፣ ጕቶውም በዐፈር ውስጥ ቢሞት፣ 9በውሃ ሽታ ያቈጠቍጣል፤ እንደ አዲስ ተክልም ቅርንጫፎችን ያወጣል። 10ሰው ግን ይሞታል፣ ይወድቃልም፤ ሰው የመጨረሻ ትንፋሱን ይተነፍሳል፣ ከዚያስ የት አለ? 11ውሃ ከሐይቅ እንደሚጠፋ፣ ወንዝም እንደሚመነምንና እንደሚደርቅ፣ 12እንዲሁ ሰው ይተኛል፣ አይነሣምም፤ ሰማያት እስኪያልፉ ድረስ፣ አይነቃም፣ ከእንቅልፉም አይቀሰቀስም።
13“ምነው በመቃብር ውስጥ በሰወርኸኝ፤ ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ፤ የተወሰነ ጊዜ በወሰንክልኝ፤ ባሰብኸኝም! 14ሰው ቢሞት፣ እንደ ገና በሕይወት ይኖራልን? የድካሜን ዘመን ሁሉ እጠባበቅ ነበር፤ መታደሴ እስኪመጣ ድረስ። 15ትጠራ ነበር፤ እኔም እመልስልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቅ ነበር። 16ያን ጊዜ አረማመዴን ትቈጥር ነበር፤ ኀጢአቴንም አትከታተልም ነበር። 17ዐመፄ በከረጢት ውስጥ ይታተም ነበር፤ ኀጢአቴንም ትሸፍን ነበር።
18“ነገር ግን ተራራ ወድቆ እንደሚፈራርስ፣ ዐለትም ከስፍራው እንደሚነቀል፣ 19ውሃ ድንጋዮችን እንደሚሸረሽር፣ ጐርፉም የመሬትን ዐፈር ጠርጎ እንደሚወስድ፣ እንዲሁ የሰውን ተስፋ ታጠፋለህ። 20ለዘላለም ታሸንፈዋለህ፣ እርሱም ያልፋል፤ ፊቱንም ታበላሸዋለህ፣ ታባርረዋለህም። 21ልጆቹ ቢከብሩ፣ እርሱ አያውቅም፤ ቢዋረዱም፣ አያስተውልም። 22የገዛ ሥጋውን ሕመም ብቻ ይሰማዋል፤ ለራሱም ብቻ ያለቅሳል።”