ኢዮብ ለወዳጆቹ መለሰ
ኢዮብ ወዳጆቹን በሐሰት የሚለስኑ የማይረቡ ባለ መድኃኒቶች ይላቸዋል። በሐሰት ለእርሱ በመወገናቸው እግዚአብሔር እንደማያመሰግናቸውም ያስጠነቅቃቸዋል። ጉዳዩን ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ሊሟገት ይፈልጋል፤ ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ ይላል። ከዚያም፣ ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? ብሎ ይጠይቃል።
13 1እነሆ፣ ዐይኔ ይህን ሁሉ አይቷል፤ ጆሮዬም ሰምቶ ተረድቶታል። 2እናንተ የምታውቁትን እኔም ደግሞ ዐውቃለሁ፤ ከእናንተ አላንስም። 3እኔ ግን ሁሉን ቻዩን ማነጋገር እወዳለሁ፤ ነገሬንም ከእግዚአብሔር ጋር ለመከራከር እናፍቃለሁ። 4እናንተ ግን በውሸት ትለቀልቃላችሁ፤ ሁላችሁም የማይጠቅሙ ሐኪሞች ናችሁ። 5ፈጽማችሁ ዝም ብትሉ ኖሮ፣ ያ ጥበባችሁ በሆነ ነበር! 6አሁን ነገሬን ስሙ፤ የከንፈሬንም ልመና አድምጡ። 7ስለ እግዚአብሔር በውሸት ትናገራላችሁን? ስለ እርሱስ በተንኰል ትናገራላችሁን? 8ለእርሱ ታደላላችሁን? ስለ እግዚአብሔር ትከራከራላችሁን? 9እርሱ በሚመረምራችሁ ጊዜ ይበጃችኋልን? ወይስ ሰውን እንደምታታሉ እርሱን ታታሉታላችሁን? 10በስውር ብታደሉ፣ እርሱ በእርግጥ ይገሥጻችኋል። 11ግርማው አያስፈራችሁምን? ፍርሃቱስ በእናንተ ላይ አይወድቅምን? 12አባባሎቻችሁ የዐመድ ምሳሌዎች ናቸው፤ መከላከያዎቻችሁም ከሸክላ የተሠሩ ናቸው።
13በፊቴ ዝም በሉ፤ እኔም ልናገር፤ የሚመጣውም ሁሉ ይድረስብኝ። 14ሥጋዬን ለምን ለአደጋ አጋልጣለሁ? ሕይወቴንስ በእጄ ለምን እይዛለሁ? 15ቢገድለኝ እንኳ በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ እከራከራለሁ። a a v15 በተቃውሞው ውስጥ እንኳ የኢዮብ እምነት ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል። ፍጹም የሆነው የግንኙነት መሻገር ኋላ ይመጣል — ኢዮብ በመጽሐፉ መጨረሻ አባታችንን ፊት ለፊት ያየዋል። 16ይህም ደግሞ መዳኛዬ ይሆናል፤ አምላክ የለሽ ሰው በፊቱ ለመቅረብ አይደፍርምና። 17ቃሌን አድምጣችሁ ስሙ፤ ንግግሬም ወደ ጆሮአችሁ ይድረስ። 18እነሆ፣ ነገሬን አዘጋጅቻለሁ፤ ጻድቅ ሆኜ እንደምገኝ ዐውቃለሁ። 19ከእኔ ጋር የሚከራከር ማን ነው? ያን ጊዜ ዝም ብዬ እሞታለሁና።
20ሁለት ነገሮችን ብቻ ስጠኝ፤ ያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፦ 21እጅህን ከእኔ አርቅ፤ ፍርሃትህም አያስደንግጠኝ። 22ጥራኝ፣ እኔም እመልሳለሁ፤ ወይም እኔ ልናገር፣ አንተም መልስልኝ። 23በደሎቼና ኀጢአቶቼ ስንት ናቸው? ዐመፄንና ኀጢአቴን አሳየኝ። 24ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? እንደ ጠላትህስ ለምን ትቈጥረኛለህ? 25በነፋስ የሚገፋውን ቅጠል ታስፈራዋለህን? የደረቀውንስ ገለባ ታሳድደዋለህን? 26በእኔ ላይ መራራ ነገር ትጽፋለህና የወጣትነቴንም ኀጢአት ታወርሰኛለህ። 27እግሮቼን በእንጨት ማሰሪያ ታስራለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ትጠብቃለህ፤ ለእግሮቼ ጫማ ድንበር ታበጃለህ።
28ስለዚህ ሰው እንደሚበሰብስ እንጨት ያልቃል፤ ብል እንደ በላው ልብስ።