የነፍስ ምሬት
ኢዮብ በቀጥታ ለእግዚአብሔር ሲናገር ክሱ ምን እንደሆነ ይጠይቃል። እንደ ወተት ያፈሰሱት፣ ቆዳንም ያለበሱት እጆች አሁን እንደ አንበሳ ያድኑታል። ወደ ጨለማ ምድር ከመሄዱ በፊት ለጥቂት ጊዜ ብቻውን እንዲተው ብቻ ይለምናል።
10 1“የገዛ ሕይወቴ ሰለቸኝ፤ ሮሮዬን እለቅቃለሁ፤ ከነፍሴ ምሬት የተነሣ እናገራለሁ። 2እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፤ አትኰንነኝ፤ ለምን እንደምትከራከረኝ አስታውቀኝ። 3መጨቈን፣ የእጆችህን ሥራ መናቅ፣ በክፉዎች ተንኰል ፈገግ እያልህ ደስ ይለሃልን? 4የሥጋ ዐይኖች አሉህን? ሟች ሰው እንደሚያይ ታያለህን? 5ዘመንህ እንደ ሟች ሰው ዘመን፣ ዓመታትህስ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን፣ 6በደሌን እስክትመረምር፣ ኀጢአቴንም እስክታሳድድ ድረስ? 7በደለኛ አለመሆኔን እያወቅህ፤ ከእጅህም ሊያድነኝ የሚችል የለም።
8“እጆችህ ቀረጹኝ፤ መላ አካሌንም ሠሩ፤ አሁን ግን ተመልሰህ ታጠፋኛለህ። 9እንደ ሸክላ እንደ ቀረጽኸኝ አስብ፤ አሁንስ ወደ ትቢያ ትመልሰኛለህን? 10እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን፤ እንደ አይብስ አላጋገርኸኝምን፣ 11ቍርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፤ በአጥንትና በጅማትም ሸመንኸኝ? 12ሕይወትንና የኪዳን ፍቅርን ሰጠኸኝ፤ እንክብካቤህም መንፈሴን ጠብቆአል።
13“ነገር ግን ይህን በልብህ ሰወርህ፤ ይህም ዐሳብህ እንደ ነበረ ዐውቃለሁ፦ 14ኀጢአት ብሠራ ትከታተለኝ ነበር፤ ከበደሌም ነጻ አታወጣኝም ነበር። 15በደለኛ ብሆን፣ ወዮልኝ! ንጹሕም ብሆን እንኳ ራሴን ቀና ማድረግ አልችልም፤ በኀፍረት ተሞልቻለሁ፤ በመከራዬም ተዘፍቄአለሁ። 16ራሴን ቀና ባደርግ፣ እንደ አንበሳ ታደነኛለህ፤ እንደ ገናም በእኔ ላይ ድንቅ ሥራህን ታሳያለህ። 17አዲስ ምስክሮችን በእኔ ላይ ታመጣለህ፤ ቍጣህንም በእኔ ላይ አብዝተህ ታፈስሳለህ፤ መከራም እንደ ተከታታይ ማዕበል ያጠቃኛል።
18“ታዲያ ከማኅፀን ለምን አወጣኸኝ? ማንም ዐይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ ኖሮ። 19ከቶ እንዳልነበርሁ በሆንሁ ነበር፤ ከማኅፀን ቀጥታ ወደ መቃብር በተወሰድሁ ነበር። 20ዘመኔ ጥቂት አይደለምን? ከእኔ ዘወር በል፤ ተወኝ፤ ጥቂት እፎይታ አገኝ ዘንድ፣ 21ወደማይመለሱበት ስፍራ ሳልሄድ፣ ወደ ጨለማውና ወደ ድቅድቅ ጥላ ምድር፣ 22እንደ ድቅድቅ ሌሊት ወደ ጨለማማ ምድር፣ ወደ ድቅድቅ ጥላና ሁከት፣ ብርሃን እንኳ እንደ ጨለማ ወደ ሆነበት።”