ሶፋር መለሰ
ሶፋር ከሁሉም ይበልጥ ጨካኝ ነው፤ ኢዮብ ብዙ ይናገራል፤ እግዚአብሔርም ከበደሉ ያነሰ ቀጥቶታል ይላል። ኀጢአትን ከድንኳኖችህ አርቅ፤ ሕይወትህም ከቀትር ይልቅ ታበራለች ይለዋል። እርሱ ፍጹም እርግጠኛ ነው፤ ይህንንም የሚናገረው ለንጹሕ ሰው ነው።
11 1ነዓማቴዊው ሶፋር እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2“ይህ የቃላት ጎርፍ ያለ መልስ ይቀራልን? እንዲህ በንግግር የተሞላ ሰው ጻድቅ ይባላልን? 3ከንቱ ንግግርህ ሌሎችን ዝም ያሰኛልን? የሚያሳፍርህ ሳይኖር ትዘባበታለህን? 4አንተ፦ ‘ትምህርቴ ንጹሕ ነው፤ በፊትህም ነውር የሌለብኝ ነኝ’ ትላለህና። 5ነገር ግን እግዚአብሔር ምነው በተናገረ፤ ከንፈሩንም በአንተ ላይ በከፈተ፤ 6የጥበብንም ምስጢር በገለጠልህ፤ እውነተኛ ጥበብ ሁለት ገጽታ አለውና። እግዚአብሔር ከበደልህ ይገባ ከነበረው ያነሰ እንደ ጠየቀህ እንግዲህ ዕወቅ። 7የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? የሁሉን ቻዩን ወሰን ልታገኝ ትችላለህን? 8ከሰማያት ከፍ ያሉ ናቸው፤ አንተ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦል ጠለቅ ያሉ ናቸው፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ? 9መጠናቸው ከምድር ይረዝማል፤ ከባሕርም ይሰፋል። 10እርሱ አልፎ ቢያስር፤ ወደ ፍርድም ቢጠራ፣ ማን ሊመልሰው ይችላል? 11እርሱ ከንቱ ሰዎችን ያውቃልና፤ ክፋትን ባየ ጊዜ አያስተውለውምን? 12ባዶ ጭንቅላት ያለው ሰው ግን ጥበበኛ የሚሆነው የሜዳ አህያ ውርንጫ ሰው ሆኖ ሲወለድ ነው። 13አንተ ልብህን ብታዘጋጅ፤ እጆችህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፤ 14በእጅህ ኀጢአት ቢኖር፣ አስወግደው፤ በድንኳኖችህም ዐመፅ አይኑር፤ 15በእርግጥ ያለ ኀፍረት ፊትህን ታነሣለህ፤ ጸንተህም ትቆማለህ፤ አትፈራም። 16መከራህን ትረሳለህ፤ እንዳለፈ ውሃም ታስታውሰዋለህ። 17ሕይወትህ ከቀትር ይልቅ ይበራል፤ ጨለማውም እንደ ንጋት ይሆናል። 18ተስፋ ስላለ፣ በእርግጠኝነት ትኖራለህ፤ ዘውር ብለህም በሰላም ትተኛለህ። 19የሚያስፈራህ ሳይኖር ትተኛለህ፤ ብዙዎችም ሞገስህን ይሻሉ። 20የክፉዎች ዐይኖች ግን ይደክማሉ፤ መሸሻቸውም ሁሉ ይጠፋባቸዋል፤ ተስፋቸውም የመጨረሻ ትንፋሻቸውን መተንፈስ ብቻ ነው።”