ወደ ዐለቱ ተመልከቱ
በጣም ጥቂት እንዳይሆኑ ለሚፈሩ ሰዎች አብ ወደ አንድ ወንድና አንዲት ሴት፣ ወደ አብርሃምና ሣራ መልሶ ያመለክታቸዋል። ሰማይና ምድር ያረጃሉ፤ የእርሱ ማዳን ግን አያረጅም። ኢየሩሳሌም የሚያንገዳግደውን ጽዋውን ጠጥታ ጨርሳለች፤ የሚደግፋትም ልጅ አልቀረላትም። እርሱ ጽዋውን ይወስደዋል።
51 1“እኔን ስሙ፤ ጽድቅን የምትከታተሉ፣ አባታችንን የምትሹ ሆይ፤ ከእርሱ ወደ ተፈለጣችሁበት ዐለት፣ ከእርሱም ወደ ተቈፈራችሁበት ጒድጓድ ተመልከቱ። 2ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ እርሱ አንድ ብቻ ሳለ ጠራሁት፤ ባረክሁትም አበዛሁትም። 3አባታችን ጽዮንን ያጽናናልና፤ ፍርስራሿንም ሁሉ ያጽናናል። ምድረ በዳዋን እንደ ኤደን፣ በረሓዋንም እንደ አባታችን ገነት ያደርጋል። ደስታና ተድላ፣ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በእርሷ ውስጥ ይገኛሉ።
4“ሕዝቤ ሆይ፣ እኔን ስሙ፤ ወገኔ ሆይ፣ አድምጡኝ፤ ትምህርት ከእኔ ዘንድ ይወጣልና፤ ፍርዴንም ለአሕዛብ ብርሃን አደርጋለሁ። 5ጽድቄ ቀርቧል፣ ማዳኔ ወጥቷል፤ ክንዶቼም ለአሕዛብ ፍርድ ያደርጋሉ፤ ደሴቶች ይጠብቁኛል፣ በክንዴም ተስፋ ያደርጋሉ። 6ዓይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሡ፣ ከታች ያለችውንም ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ ይተናሉ፣ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፣ በእርሷም የሚኖሩ እንደ ትንኝ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፣ ጽድቄም ከቶ አይሻርም። 7ጽድቅን የምታውቁ፣ ትምህርቴን በልባችሁ የያዛችሁ ሕዝብ ሆይ፣ እኔን ስሙ፤ የሰውን ነቀፋ አትፍሩ፤ በስድባቸውም አትደንግጡ። 8ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋልና፣ ትልም እንደ ጸምር ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም ይኖራል፣ ማዳኔም ለልጅ ልጅ ሁሉ ይኖራል።”
9ንቃ፣ ንቃ፤ የአባታችን ክንድ ሆይ፣ ኀይልን ልበስ! በቀደመው ዘመን፣ በጥንት ትውልዶች እንደ ሆነው ንቃ። የባሕሩን ጭራቅ ራሃብን ቈራርጠህ የጣልህ፣ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን? a a v9 በኢሳይያስ ራእይ፣ የተዘረጋው የአባታችን ክንድ ከፍጥረት ጀምሮ ከግብፅ መውጣትን አልፎ ገና እስኪመጣው ቤዛነት ድረስ በታሪክ ሁሉ ላይ ያለው የማዳን ኀይሉ ነው። 10ባሕሩን፣ የታላቁን ጥልቅ ውሃ ያደረቅህ፣ የባሕሩንም ጥልቅ የተቤዡት የሚሻገሩበት መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን? 11እንግዲህ በአባታችን የተቤዡት ይመለሳሉ፣ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ ራሳቸውን ያጎናጽፋል። ተድላና ደስታ ይደርስባቸዋል፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።
12“እኔ፣ እኔ የማጽናናህ ነኝ። የሚሞተውን ሰው፣ እንደ ሣር የሚያልፈውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ፤ 13ሰማያትን የዘረጋ፣ የምድርንም መሠረት የጣለ ፈጣሪህን እኔን ረሳህ። ለማጥፋት በተነሣው በጨቋኙ ቍጣ የተነሣ ቀኑን ሙሉ ዘወትር በፍርሃት ትኖራለህ። የጨቋኙ ቍጣ ግን ወዴት አለ? 14የተጐበጠው ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል፤ ሞቶ ወደ ጒድጓድ አይወርድም፤ እንጀራውም አያጣም። 15ባሕሩን አናውጦ ማዕበሉ የሚያገሳ አባትህ እኔ ነኝና፤ የሰማይ ሠራዊት አባት ስሙ ነው። 16ቃሌንም በአፍህ አኖርሁ፣ በእጄም ጥላ ሸፈንሁህ፤ ሰማያትን ለመትከል፣ የምድርንም መሠረት ለመጣል፣ ጽዮንንም፣ ‘አንተ ሕዝቤ ነህ’ ለማለት ነው።”
17ንቂ፣ ንቂ! ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ተነሺ፤ ከአባታችን እጅ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ፣ ዋንጫውንም እስከ አተላው ድረስ የጨለጥሽ፣ የሚያንገዳግድሽንም ጽዋ ጠጥተሻል። 18ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፤ ካሳደገቻቸው ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም። 19እነዚህ ሁለት ነገሮች ደረሱብሽ፤ ማን ያለቅስልሻል? ጥፋትና ውድመት፣ ራብና ሰይፍ። የሚያጽናናሽ ማን ነው? 20ልጆችሽ ዝለዋል፤ በመረብ እንደ ተያዘ ሚዳቋ በየመንገዱ ማዕዘን ተኝተዋል፤ የአባታችን ቍጣ፣ የአባትሽም ዘለፋ ሞልቶባቸዋል።
21ስለዚህ የተቸገርሽ፣ በወይን ጠጅ ሳይሆን የሰከርሽ ሆይ፣ ይህን ስሚ፤
22የሕዝቡን ጕዳይ የሚከራከር ጌታ አባትሽ እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፣ የሚያንገዳግድሽን ጽዋ፣ የቍጣዬን ዋንጫ ከእጅሽ ወሰድሁ፤ ዳግመኛ አትጠጪውም።’ 23በሚያሠቃዩሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ እነርሱም፣ ‘ዝቅ በዪ፤ በላይሽም እናልፋለን’ አሉሽ፤ ጀርባሽንም እንደ መሬት፣ ለሚያልፉም እንደ መንገድ አደረግሽ።