ዲና
ዲና በአካባቢው ልዑል ተይዛ ተደፈረች፤ እርሱም ከዚያ በኋላ ሊያገባት ፈለገ። ወንድሞቿ በሐሰተኛ ሰላም መለሱ፤ እንዲገረዙ ጠየቁ፣ ከዚያም በሕመም ላይ ሳሉ በከተማይቱ ያለውን ወንድ ሁሉ ገደሉ። የያዕቆብ ብቸኛ ቅሬታ በራሱ ላይ የመጣው አደጋ ነበር።
34 1ልያ ለያዕቆብ የወለደቻት ልጅ ዲና፣ የአገሩን ቈነጃጅት ልታይ ወጣች። 2የአገሩ አለቃ የሆነው የኤዊው የሐሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ይዞም ከእርሷ ጋራ ተኛ፤ አዋረዳትም። 3ልቡም በያዕቆብ ልጅ በዲና ተጣበቀ፤ ብላቴናዪቱንም ወደደ፤ ልቧንም በሚነካ ተናገራት። 4ሴኬምም አባቱን ሐሞርን፣ “ይህችን ብላቴና ሚስት እንድትሆነኝ አጋባኝ” አለው።
5ያዕቆብም ሴኬም ልጁን ዲናን እንዳረከሳት ሰማ፤ ልጆቹ ግን ከብቶቹ ጋራ በሜዳ ነበሩ፤ ስለዚህ ያዕቆብ እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። 6የሴኬምም አባት ሐሞር ከያዕቆብ ጋራ ሊነጋገር ወደ እርሱ ወጣ። 7የያዕቆብም ልጆች ከሜዳ መጡ፤ በሰሙም ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ተቈጡም፤ ሴኬም የያዕቆብን ልጅ ዳስሶ በእስራኤል ላይ የሚያስነውር ነገር፣ ሊደረግ የማይገባውን ነገር አድርጎ ነበርና። 8ሐሞርም እንዲህ ብሎ ተነጋገራቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን እጅግ ይናፍቃል፤ እባካችሁ ሚስት ትሆነው ዘንድ ስጡት። 9ከእኛም ጋራ ተጋቡ፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፤ ሴቶች ልጆቻችንንም ለእናንተ ውሰዱ። 10ከእኛም ጋራ ኑሩ፤ አገሪቱ በፊታችሁ ክፍት ናት፤ በውስጧ ተቀመጡ፤ ነግዱ፤ ርስትም አግኙባት።”
11ሴኬምም አባቷንና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፤ “በፊታችሁ ሞገስ ላግኝ፤ የምትሉኝንም ሁሉ እሰጣለሁ። 12ጥሎሽና ስጦታ ብትጠይቁኝ፣ ምንም ያህል ትልቅ ቢሆን እከፍላለሁ፤ ብላቴናዪቱን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ስጡኝ ብቻ።”
13የያዕቆብም ልጆች ሴኬም እኅታቸውን ዲናን አርክሶ ነበርና ሴኬምንና አባቱን ሐሞርን በተንኰል መለሱላቸው። 14እንዲህም አሏቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው መስጠት፣ ይህን ነገር ማድረግ አንችልም፤ ይህ ለእኛ ነውር ነውና። 15በዚህ ብቻ እንስማማለን፤ ወንዶቻችሁ ሁሉ ተገርዘው እንደ እኛ ብትሆኑ፣ 16ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ለእኛ እንወስዳለን፤ ከእናንተም ጋራ ኖረን አንድ ሕዝብ እንሆናለን። 17ባትሰሙንና ባትገረዙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።”
18ቃላቸውም ሐሞርንና ልጁን ሴኬምን ደስ አሰኛቸው። 19ጐበዝም በያዕቆብ ልጅ ሐሴት አድርጎ ነበርና ነገሩን ለማድረግ አልዘገየም፤ እርሱም በአባቱ ቤት ሁሉ ከሁሉ ይበልጥ የተከበረ ነበር። 20ሐሞርና ልጁ ሴኬም ወደ ከተማቸው በር መጡ፤ የከተማቸውንም ሰዎች እንዲህ ብለው አነጋገሩ፤ 21“እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋራ ሰላማውያን ናቸው፤ በአገሩ ይኑሩ፤ በውስጡም ይነግዱ፤ አገሪቱ ለእነርሱ የሰፋች ናትና። ሴቶች ልጆቻቸውን ሚስት አድርገን እንወስዳለን፤ የእኛንም እንሰጣቸዋለን። 22ነገር ግን እነርሱ እንደ ተገረዙ ከእኛ ያሉ ወንዶች ሁሉ ቢገረዙ ብቻ፣ ሰዎቹ ከእኛ ጋራ አንድ ሕዝብ ሆነው ሊኖሩ ይስማማሉ። 23ከብቶቻቸውና ንብረታቸው እንስሶቻቸውም ሁሉ የእኛ አይሆኑምን? ከእነርሱ ጋራ እንስማማ ብቻ፤ ከእኛም ጋራ ይኖራሉ።”
24በከተማውም በር የሚወጡ ሁሉ ሐሞርንና ልጁን ሴኬምን ሰሙ፤ በከተማው በር የሚወጡ ወንዶችም ሁሉ ተገረዙ። 25በሦስተኛውም ቀን ገና በሕማም ሳሉ የያዕቆብ ልጆች ከሆኑት ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ፣ እያንዳንዳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳያስቡት በከተማዪቱ ላይ መጡ፤ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ። 26ሐሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፤ ዲናንም ከሴኬም ቤት ወስደው ሄዱ። 27የያዕቆብ ልጆች የከተማዋ ሰዎች እኅታቸውን አርክሰው ነበርና ወደ ተገደሉት መጥተው ከተማዪቱን ዘረፉ። 28በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን አህዮቻቸውንም፣ በከተማውና በሜዳ ያለውንም ሁሉ ወሰዱ። 29ሀብታቸውን ሁሉ፣ ልጆቻቸውንም ሁሉ ሚስቶቻቸውንም ማርከው ወሰዱ፤ በቤቶች ውስጥ ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። 30ያዕቆብም ስምዖንንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በዚህ በሚኖሩት በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ዘንድ አስጠልታችሁኛል፤ መከራም አምጥታችሁብኛል። ሰዎቼ ጥቂቶች ናቸው፤ ተሰብስበው ቢመጡብኝ ይወጉኛል፤ እኔና ቤተ ሰቤም እጠፋለን።”
31እነርሱ ግን፣ “እኅታችንን እንደ ጋለሞታ ሊያደርጋት ይገባልን?” አሉ።