ሶምሶን የጋዛን በሮች ተሸክሞ ወሰደ
ሶምሶን የጋዛን በሮች ተሸክሞ ይሄዳል፤ ከዚያም ምስጢሩን እንድታገኝ ገንዘብ የተከፈላትን ደሊላን ይወዳል። ከሦስት ውሸቶች በኋላ ልቡን ሁሉ ይነግራታል፤ ተላጭቶ ይነቃል፤ አብም እንደ ተለየው አያውቅም። ታውሮ በወፍጮ ቤት ሳለ ጠጕሩ እንደገና ያድጋል፤ እርሱም ዳግመኛ ኃይልን ይለምናል።
16 1ሶምሶን ወደ ጋዛ ሄደ፤ በዚያም አንዲት ጋለሞታ አይቶ ከእርሷ ጋራ ተኛ። 2የጋዛ ሰዎችም፣ “ሶምሶን ወደዚህ መጥቷል” የሚለውን በሰሙ ጊዜ፣ ስፍራውን ከበው ሌሊቱን ሙሉ በከተማዪቱ በር አደቡለት። “ሲነጋ እንገድለዋለን” እያሉም ሌሊቱን ሙሉ ዝም አሉ። 3ሶምሶን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በዚያ ተኛ። በእኩለ ሌሊትም ተነሥቶ የከተማዪቱን በር መዝጊያዎችና ሁለቱን መቃኖች ይዞ ከመወርወሪያው ጋራ ነቅሎ በትከሻው ላይ አደረጋቸው፤ ወደ ኬብሮን ፊት ለፊት ወዳለው ኰረብታ ጫፍ ተሸክሞ ወሰዳቸው።
4ከዚህ በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ ደሊላ የተባለችውን አንዲት ሴት ወደደ። 5የፍልስጥኤም ገዦችም ወደ እርሷ መጥተው፣ “አባብለሽ ታላቅ ኀይሉ ከምን እንደ ሆነ፣ አሸንፈን አስረን ልናስገዛው እንዴት እንደምንችል እወቂ። እያንዳንዳችንም አንድ ሺሕ መቶ ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት።
6ደሊላም ሶምሶንን፣ “ታላቅ ኀይልህ ከምን እንደ ሆነ፣ እንዴትስ ታስረህ ልትገዛ እንደምትችል ንገረኝ” አለችው።
7ሶምሶንም፣ “ገና ባልደረቁ በሰባት አዲስ የቀስት ጅማቶች ቢያስሩኝ፣ እደክማለሁ፤ እንደ ማንኛውም ሰውም እሆናለሁ” አላት።
8የፍልስጥኤምም ገዦች ገና ያልደረቁ ሰባት አዲስ የቀስት ጅማቶች አመጡላት፤ እርሷም በእነርሱ አሰረችው። 9በውስጠኛውም ክፍል አድብተው የተቀመጡ ሰዎች ነበሩባት። እርሷም፣ “ሶምሶን ሆይ፣ ፍልስጥኤማውያን ተነሡብህ!” አለችው። እርሱ ግን የተልባ እግር ክር እሳት ሲነካው እንደሚበጠስ የቀስቱን ጅማቶች በጠሰ። ስለዚህ የኀይሉ ምስጢር አልታወቀም።
10ደሊላም ሶምሶንን፣ “አሾፍህብኝ፤ ውሸትም ነገርኸኝ። አሁን እንዴት ልትታሰር እንደምትችል ንገረኝ” አለችው።
11እርሱም፣ “ገና በሥራ ባልዋሉ አዲስ ገመዶች አጥብቀው ቢያስሩኝ፣ እደክማለሁ፤ እንደ ማንኛውም ሰውም እሆናለሁ” አላት።
12ደሊላም አዲስ ገመዶች ወስዳ በእነርሱ አሰረችው፤ “ሶምሶን ሆይ፣ ፍልስጥኤማውያን ተነሡብህ!” አለችው። በውስጠኛውም ክፍል አድብተው የተቀመጡ ሰዎች ነበሩ። እርሱ ግን ገመዶቹን እንደ ክር ከክንዶቹ ላይ በጣጠሰ።
13ደሊላም ሶምሶንን፣ “እስካሁን ድረስ አሾፍህብኝ፤ ዋሸኸኝም። እንዴት ልትታሰር እንደምትችል ንገረኝ” አለችው። እርሱም፣ “የራሴን ሰባት ዘለላ ጠጕር ከሸማ ማግ ጋራ ሸምነሽ በችካል ብታጠብቂው፣ እንደ ማንኛውም ሰው እደክማለሁ” አላት።
14እርሷም በችካል አጠበቀችው፤ “ሶምሶን ሆይ፣ ፍልስጥኤማውያን ተነሡብህ!” አለችው። እርሱ ግን ከእንቅልፉ ነቅቶ ችካሉን፣ ሸማውንና ማጉን ነቀለ።
15እርሷም፣ “ልብህ ከእኔ ጋራ ሳይሆን፣ ‘እወድሻለሁ’ እንዴት ትላለህ? ሦስት ጊዜ አሾፍህብኝ፤ ታላቅ ኀይልህም ከምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም” አለችው።
16ዕለት በዕለትም በቃሏ አጥብቃ ስትወተውተውና ስታስጨንቀው፣ ነፍሱ እስከ ሞት ድረስ ታክታ መሞትን ተመኘ። 17ስለዚህ ልቡን በሙሉ ገለጠላት፤ “ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ የአባታችን ናዝራዊ ስለ ሆንሁ፣ በራሴ ላይ ምላጭ አልዋለም። ብላጭ ኀይሌ ይለየኛል፤ እደክማለሁም፤ እንደ ማንኛውም ሰውም እሆናለሁ” አላት።
18ደሊላም ልቡን በሙሉ እንደ ነገራት ባየች ጊዜ ወደ ፍልስጥኤም ገዦች ልካ፣ “ልቡን በሙሉ ነግሮኛልና እንደ ገና ውጡ” አለች። እነርሱም ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርሷ መጡ። 19በጒልበቷም ላይ አስተኝታው ሰው ጠርታ የራሱን ሰባት ዘለላ ጠጕር አስላጨችው። ልታስገዛውም ጀመረች፤ ኀይሉም ለየው። 20እርሷም፣ “ሶምሶን ሆይ፣ ፍልስጥኤማውያን ተነሡብህ!” አለችው። እርሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ፣ “እንደ በፊቱ ወጥቼ ራሴን አላቅቃለሁ” ብሎ አሰበ። አባታችን ግን ከእርሱ እንደ ተለየ አላወቀም።
21ፍልስጥኤማውያንም ይዘውት ዐይኖቹን አወጡ፤ ወደ ጋዛም አወረዱት። በናስ ሰንሰለቶችም አሰሩት፤ በወኅኒ ቤትም እህል ፈጨ። 22የራሱ ጠጕር ግን ከተላጨ በኋላ እንደ ገና ማደግ ጀመረ።
አብ ሶምሶንን እንደ ገና አበረታው
23የፍልስጥኤም ገዦችም ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ሊያቀርቡና ሊደሰቱ ተሰበሰቡ፤ “አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ። 24ሕዝቡም ባዩት ጊዜ አምላካቸውን አመሰገኑ፤ “ምድራችንን ያጠፋውን፣ የተገደሉንንም ያበዛውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ።
25ልባቸውም በተደሰተ ጊዜ፣ “ያዝናናን ዘንድ ሶምሶንን ጥሩት” አሉ። ሶምሶንንም ከወኅኒ ቤት አመጡት፤ እርሱም አዝናናቸው። በዐምዶችም መካከል አቆሙት። 26ሶምሶንም እጁን የያዘውን ልጅ፣ “ቤቱ የተመሠረተባቸውን ዐምዶች እንድዳስስ አድርገኝ፤ በእነርሱም እደገፍ ዘንድ” አለው። 27ቤቱም በወንዶችና በሴቶች ተሞልቶ ነበር፤ የፍልስጥኤም ገዦችም ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በሰገነቱም ላይ ወደ ሦስት ሺሕ የሚኾኑ ወንዶችና ሴቶች ሶምሶን ሲያዝናና ይመለከቱ ነበር። 28ሶምሶንም አባታችንን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሉዓላዊ አባት ሆይ፣ እባክህ አስበኝ። ስለ ሁለቱ ዐይኖቼ በፍልስጥኤማውያን ላይ በአንዲት ምት ፍርድ አመጣ ዘንድ፣ እባክህ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ አበርታኝ።” 29ሶምሶንም ቤቱን የተሸከሙትን ሁለቱን መካከለኛ ዐምዶች ይዞ፣ ቀኝ እጁን በአንዱ ግራ እጁን በሌላው አድርጎ ተደገፈባቸው። 30ሶምሶንም፣ “ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ልሙት” አለ። በኀይሉም ሁሉ ገፋ፤ ቤቱም በገዦቹና በውስጡ በነበሩት ሕዝብ ሁሉ ላይ ወደቀ። ስለዚህ በሞቱ ጊዜ የገደላቸው በሕይወቱ ጊዜ ከገደላቸው ይልቅ በዙ።
31ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ ወርደው ወስደውት አመጡት፤ በጾርዓና በኤስታኦል መካከል በአባቱ በማኑሔ መቃብር ቀበሩት። እስራኤልንም ሃያ ዓመት ፈርዶ ነበር።