አባታችን አዘዘ፦ እርሻውን ግዛ
የባቢሎን የከበባ ቍልሎች ቅጥሩ ላይ ደርሰው፣ ኤርምያስም በጥበቃ ሥር ሳለ፣ አባታችን በዓናቶት ያለውን የአጎቱን ልጅ እርሻ እንዲገዛና የውሉን ሰነድ አሽጎ በሸክላ ማሰሮ እንዲያስቀምጥ ይነግረዋል። ስለዚህ ተቃርኖ ይጸልያል፤ በዚህም ምድር እርሻዎች ዳግመኛ እንደሚገዙ ይነገረዋል።
32 1የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፣ ናቡከደነፆርም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ከአባታችን ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2በዚያን ጊዜ የባቢሎን ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በሚገኘው የጥበቃ ግቢ ውስጥ ታስሮ ነበር።
3የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ አስሮት ነበርና እንዲህ አለው፦ “ለምን ትንቢት ትናገራለህ? እንዲህስ ለምን ትላለህ፦ ‘አባታችን እንዲህ ይላል፤ እነሆ፣ ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ ልሰጣት ነው፤ እርሱም ይማርካታል፤
4“የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ከባቢሎናውያን እጅ አያመልጥም፤ በእርግጥም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ ከእርሱም አፍ ለአፍ ይነጋገራል፤ ዐይን ለዐይንም ይተያያሉ። 5ሴዴቅያስንም ወደ ባቢሎን ይወስደዋል፤ እስከምጐበኘውም ቀን ድረስ በዚያ ይኖራል፣ ይላል አባታችን። ባቢሎናውያንን ብትወጉም አትሳካላችሁም።’”
6ኤርምያስም እንዲህ አለ፦ “የአባታችን ቃል እንዲህ ብሎ ወደ እኔ መጣ፦
7እነሆ፣ የአጎትህ የሰሉም ልጅ ሐናምኤል ወደ አንተ መጥቶ እንዲህ ይልሃል፦ በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ፤ የመቤዠት መብቱ ያንተ ስለ ሆነ እርሱን የመግዛቱ መብት ያንተ ነውና።”
8አባታችንም እንዳለው የአጎቴ ልጅ ሐናምኤል ወደ እኔ ወደ ጥበቃው ግቢ መጥቶ፣ ‘በብንያም ምድር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ፤ የውርስ መብቱ ያንተ ነውና፣ የመቤዠቱም መብት ያንተ ነው፤ ለራስህ ግዛው’ አለኝ። ያን ጊዜ ይህ የአባታችን ቃል እንደ ሆነ ዐወቅሁ።
9ስለዚህ በዓናቶት ያለውን እርሻ ከአጎቴ ልጅ ከሐናምኤል ገዛሁ፤ ሰባት አውንስ የሚያህልም ብር መዝኜ ሰጠሁት። 10ሰነዱንም ፈርሜ አተምሁት፤ ምስክሮችንም ጠራሁ፤ ብሩንም በሚዛን መዘንሁ። 11ከዚያም የታተመውን የሽያጭ ሰነድ ከውሉና ከድንጋጌዎቹ ጋራ፣ የተከፈተውንም ቅጂ ወሰድሁ፤ 12የሽያጩንም ሰነድ በአጎቴ ልጅ በሐናምኤል ፊት፣ ሰነዱን በፈረሙት ምስክሮች ፊት፣ በጥበቃውም ግቢ ተቀምጠው በነበሩት ይሁዳውያን ሁሉ ፊት፣ ለመሕሤያ ልጅ ለናርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።
13በእነርሱም ፊት ባሮክን እንዲህ ብዬ አዘዝሁት፦
14“የሰማይ ሰራዊት አባት፣ የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላል፦ እነዚህን ሰነዶች፣ የታተመውን የሽያጭ ሰነድና የተከፈተውን ሰነድ ውሰድ፤ ረጅም ዘመንም ጸንተው እንዲቆዩ በሸክላ ማሰሮ ውስጥ አኑራቸው። 15የሰማይ ሰራዊት አባት፣ የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላልና፦ በዚህች ምድር ቤቶች፣ እርሻዎችና የወይን ተክሎች እንደ ገና ይገዛሉ።”
የኤርምያስ ጸሎት፦ ለአንተ የሚያቅትህ ምንም የለም
16የሽያጩንም ሰነድ ለናርያ ልጅ ለባሮክ ከሰጠሁ በኋላ፣ ወደ አባታችን እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ 17“አዬ፣ ጌታ አባት ሆይ! ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋ ክንድህ የፈጠርህ አንተ ራስህ ነህ፤ ለአንተም የሚያቅትህ ምንም ነገር የለም። 18ለሺዎች ታማኝ ፍቅርን ታሳያለህ፤ ነገር ግን የወላጆችን በደል ከእነርሱ በኋላ ባሉት ልጆቻቸው እቅፍ ውስጥ ትመልሳለህ፤ አንተ ታላቅ፣ ኀያል አባት ሆይ፤ የሰማይ ሰራዊት አባት ስሙ ነው። 19በምክር ታላቅ፣ በሥራ ኀያል ነህ፤ ዐይኖችህ የሰውን ልጆች መንገድ ሁሉ ይመለከታሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራውም ፍሬ ትከፍላለህ። 20በግብፅ ምድር ምልክቶችንና ድንቆችን አደረግህ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሰዎች ሁሉ መካከል ይህን እያደረግህ፣ ዛሬ እንዳለው ለራስህ ስምን አተረፍህ። 21ሕዝብህን እስራኤልን በምልክቶችና በድንቆች፣ በብርቱ እጅ፣ በተዘረጋ ክንድ፣ በታላቅ ድንጋጤም ከግብፅ ምድር አወጣህ። 22ለአባቶቻቸው ልትሰጣቸው የማልህላቸውን ይህችን ምድር፣ ወተትና ማር የምታፈስ ምድር ሰጠሃቸው። 23ገብተውም ወረሷት፤ ነገር ግን ድምፅህን አልሰሙም፤ በሕግህም አልተመላለሱም፤ እንዲያደርጉ ያዘዝሃቸውን ሁሉ ሳያደርጉ ቀሩ። ስለዚህ ይህን መከራ ሁሉ አመጣህባቸው። 24እነሆ፣ ከተማዪቱን ለመማረክ የከበባ ድልድዮች ደርሰዋል፤ ከተማዪቱም በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ምክንያት በሚወጓት በባቢሎናውያን እጅ ተሰጥታለች። የተናገርኸውም ደርሷል፤ አንተም ታየዋለህ። 25ነገር ግን አንተ፣ ጌታ አባት ሆይ፣ ከተማዪቱ በባቢሎናውያን እጅ እየተሰጠች ሳለ፣ ‘እርሻውን በብር ግዛ፤ ምስክሮችንም ጥራ’ አልኸኝ።”
26ከዚያም የአባታችን ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ብሎ መጣ፦
27“የሥጋ ሁሉ አባት እኔ ነኝ፤ የሚያቅተኝ ነገር አለን? 28ስለዚህ አባታችን እንዲህ ይላል፦ እነሆ፣ ይህችን ከተማ በባቢሎናውያን እጅ፣ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ልሰጣት ነው፤ እርሱም ይማርካታል። 29ይህችን ከተማ የሚወጓት ባቢሎናውያን መጥተው በእሳት ያቃጥሏታል፤ ሕዝቡ በጣራዎቻቸው ላይ ለበኣል ዕጣን ያጨሱባቸውን፣ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን አፍስሰው ያስቈጡኝን ቤቶች በእሳት ያቃጥላሉ።
30“የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ከወጣትነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ከማድረግ በቀር ሌላ ምንም አላደረጉም፤ እስራኤልም በእጆቻቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ምንም አላደረጉም፣ ይላል አባታችን።
31“ይህች ከተማ ከተመሠረተችበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቍጣዬንና መዓቴን አስነስታብኛለች፤ ስለዚህ ከፊቴ አስወግዳታለሁ፤ 32ይህም የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ፣ እነርሱ፣ ነገሥታታቸው፣ መኳንንታቸው፣ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ያስቈጡኝ ዘንድ ስላደረጉት ክፋት ሁሉ ነው። 33ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን መለሱልኝ። ደጋግሜ ባስተምራቸውም፣ ለመስማትም ሆነ ተግሣጽን ለመቀበል እምቢ አሉ። 34በስሜ በተጠራው ቤት ውስጥ አስጸያፊ ጣዖቶቻቸውን አኖሩ፤ እርሱንም አረከሱት። 35በቤንሕኖም ሸለቆ ለበኣል የኰረብታ መስገጃዎችን ሠሩ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ለሞሎክ ሠዉ፤ ይህን አስጸያፊ ነገር አድርገው ይሁዳን ኀጢአት እንዲያሠሩ ያላዘዝሁትን፣ በልቤም ያላሰብሁትን ነገር አደረጉ።”
ልጆቼ ይሆናሉ፤ እኔም አባታቸው እሆናለሁ
36“አሁንም ‘በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር በባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች’ ስለምትሉላት ስለዚህች ከተማ፣ የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላል፦
37“እነሆ፣ በቍጣዬ፣ በመዓቴና በታላቅ ንዴቴ ከበተንኋቸው ምድሮች ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ በሰላምም እንዲኖሩ አደርጋለሁ። 38ልጆቼም ይሆናሉ፤ እኔም አባታቸው እሆናለሁ። 39ሁልጊዜ ይፈሩኝ ዘንድ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ፤ ይህም ለእነርሱና ከእነርሱ በኋላ ለሚኖሩ ልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸዋል። 40የዘላለምም ኪዳን ከእነርሱ ጋራ አደርጋለሁ፤ መልካም ከማድረጋቸውም ፈጽሞ አልመለስም፤ ከእኔም ፈጽሞ እንዳይመለሱ ፍርሃቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። 41በእነርሱ ደስ ይለኛል፤ መልካምም አደርግላቸዋለሁ፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴም በዚህች ምድር በእውነት እተክላቸዋለሁ።”
42አባታችን እንዲህ ይላልና፦ “ይህን ታላቅ መከራ ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፣ እንዲሁ ተስፋ የገባሁላቸውን መልካም ነገር ሁሉ አመጣባቸዋለሁ። 43‘ሰውም ሆነ እንስሳ የሌለባት፣ በባቢሎናውያንም እጅ የተሰጠች የተጣለች ናት’ በምትሏት በዚህች ምድር እርሻዎች ይገዛሉ። 44በብንያም ምድር፣ በኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ በይሁዳ ከተሞች፣ በተራራማው አገር፣ በቈላውና በኔጌቭ እርሻዎች በብር ይገዛሉ፤ ሰነዶችም ይጻፋሉ፤ ይታተማሉ፤ ይመሰከርባቸዋልም፤ ከምርኮ መልሼ አመጣቸዋለሁና፣ ይላል አባታችን።”