ሕዝቅያስ ልብሱን ቀደደ
ሕዝቅያስ የሰናክሬምን ደብዳቤ ወደ አብ ቤት ወስዶ በፊቱ ይዘረጋዋል። ኢሳይያስ መልሱን ያመጣል፤ ጉረኛው በአፍንጫው መንጠቆ ይደረግበታል፤ በመጣበትም መንገድ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ከበባው በአንድ ሌሊት ያበቃል፤ እርሱም በገዛ ልጆቹ ይገደላል።
37 1ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፤ የሐዘን ልብስ ለበሰ፤ ወደ አባታችንም ቤት ገባ። 2የቤተ መንግሥት ኀላፊውን ኤልያቄምን፣ ጸሐፊውን ሳቤናንና ታላላቆቹን ካህናት ማቅ አልብሶ ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ላከ። 3እንዲህም አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ይህ ቀን የመከራ፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው። ልጆች ለመወለድ ደርሰዋል፤ የሚወልዱበት ኀይል ግን የለም። 4ምናልባት ጌታው የአሦር ንጉሥ ሕያውን አብ ለመዘባበት የላከውን የረብሻቄን ቃላት አባትህ ይሰማ ይሆናል፤ የሰማቸውንም ቃላት ይገሥጻል። ስለዚህ ለተረፈው ቅሬታ ጸሎት አቅርብ።” a a v4 ረብሻቄ የሰው ስም ሳይሆን ማዕረግ ነው፤ የአሦር ንጉሥ ዋና የጦር አዛዥ ማለት ነው።
5የንጉሡ የሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፣
6ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ አባታችን እንዲህ ይላል፤ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች የተሳደቡብኝን፣ የሰማኻቸውን ቃላት አትፍራ። 7እነሆ፣ በእርሱ ውስጥ መንፈስ አኖራለሁ፤ ወሬ ሰምቶ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል፤ በዚያም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።”
8ረብሻቄም ተመልሶ የአሦርን ንጉሥ ልብናን ሲወጋ አገኘው፤ ንጉሡ ከላኪሶ መውጣቱን ሰምቶ ነበርና። 9ንጉሡም ስለ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለ ቲርሐቃ፣ “ሊወጋህ ወጥቷል” የሚል ወሬ ሰማ። ይህንም በሰማ ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፤ 10“የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤ የምትታመንበት አምላክ፣ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም’ ብሎ አያታልልህ። 11የአሦር ነገሥታት ሁሉንም አገሮች ፈጽመው እንዴት እንዳጠፏቸው አንተ ራስህ ሰምተሃል፤ ታዲያ አንተ ትድናለህን? 12አባቶቼ ያጠፏቸውን ጎዛንን፣ ካራንን፣ ራጸፍንና በቴልሳር የነበሩትን የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አዳኗቸውን? 13የሐማት ንጉሥ፣ የአርጳድ ንጉሥ፣ የሲፈርዋይም ንጉሥ፣ የሄናና የኢዋ ነገሥታት ወዴት አሉ?”
በአብ ፊት ዘረጋው
14ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ አባታችንም ቤት ወጥቶ በአባታችን ፊት ዘረጋው። 15ሕዝቅያስም እንዲህ ብሎ ወደ አባታችን ጸለየ፤ 16“በኪሩቤል ላይ የተቀመጥህ የሰማይ ሠራዊት አባት፣ የእስራኤል አብ ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አባታችን ነህ፤ ሰማይንና ምድርን አንተ ፈጠርህ። 17አባታችን ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ አባታችን ሆይ፣ ዐይኖችህን ከፍተህ እይ፤ ሕያውን አብ ለመዘባበት የላከውን የሰናክሬምን ቃላት ሁሉ ስማ። 18አባታችን ሆይ፣ የአሦር ነገሥታት አሕዛብን ሁሉና አገሮቻቸውን ማጥፋታቸው እውነት ነው፤ 19አማልክቶቻቸውንም በእሳት ጣሉ፤ እነዚህ አማልክት አልነበሩምና፤ የሰው እጅ ሥራ፣ እንጨትና ድንጋይ ነበሩ እንጂ፤ ስለዚህ አጠፏቸው። 20አሁንም አባታችን ሆይ፣ ከእጁ አድነን፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ አባታችን መሆንህን ያውቁ ዘንድ።”
አብ መለሰ
21የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስም ወደ ሕዝቅያስ ልኮ እንዲህ አለ፤ የእስራኤል አብ እንዲህ ይላል፤ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ስለ ጸለይህ፣
22አባታችን በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ “ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ናቀችህ፣ ዘበተችብህ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ከበስተኋላህ ራስዋን ነቀነቀች። 23ማንን ዘበትህ፣ ተሳደብህ? በማን ላይ ድምፅህን ከፍ አደረግህ፣ ዐይኖችህንም በትዕቢት አነሣህ? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው! 24ጌታ አብን በባሪያዎችህ ዘበትህበት፤ እንዲህም አልህ፤ ‘በብዙ ሰረገሎቼ ወደ ተራሮች ከፍታ፣ ወደ ሊባኖስ ጥግ ወጣሁ። ረጃጅሞቹን ዝግባዎቿን፣ የተመረጡ ጥዶቿንም ቈረጥሁ፤ ወደ ሩቁ ከፍታዋ፣ ወደ ጥቅጥቅ ደኗም ደረስሁ። 25የውሃ ጒድጓዶች ቈፍሬ ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ጫማ ጫፍ የግብፅን ወንዞች ሁሉ አደረቅሁ።’ 26አልሰማህምን? ከብዙ ዘመን በፊት ይህን አደረግሁ፤ ከጥንት ዘመንም አቀድሁት። አሁንም እንዲፈጸም አደረግሁት፤ አንተ የተመሸጉ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽ ክምር እንድትለውጥ። 27ነዋሪዎቻቸው ኀይላቸው ተገፎ ደነገጡ፣ አፈሩም፤ እንደ ሜዳ ቡቃያ፣ እንደ ለጋ ሣር፣ በሰገነት ላይ እንዳለ ሣር፣ ሳያድግ እንደ ደረቀ ሆኑ። 28እኔ ግን መቀመጥህን፣ መውጣትህንና መግባትህን፣ በእኔ ላይ መቈጣትህንም አውቃለሁ። 29በእኔ ላይ ስለ ተቈጣህ፣ ትዕቢትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣ መቃጫዬን በአፍንጫህ፣ ልጓሜንም በአፍህ አገባለሁ፤ መልሼም በመጣህበት መንገድ እወስድሃለሁ።
30“ምልክትህም ይህ ይሆናል፤ በዚህ ዓመት በራሱ የበቀለውን፣ በሁለተኛው ዓመት ከዚያው የሚበቅለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ዝሩ፣ አጭዱ፤ የወይን አትክልትም ትከሉ፣ ፍሬያቸውንም ብሉ። 31ከይሁዳ ቤት የተረፈው ቅሬታ እንደ ገና ወደ ታች ሥር ይሰድዳል፣ ወደ ላይም ፍሬ ያፈራል። 32ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ይወጣልና፣ ከጽዮን ተራራም የተረፉ ጭፍሮች ይወጣሉ። የሰማይ ሠራዊት አባት ቅናት ይህን ያደርጋል።
33ስለዚህ አባታችን ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ ወደዚች ከተማ አይገባም፤ እዚህም ፍላጻ አይወረውርም፤ በጋሻም አይገጥማትም፤ በእርሷም ላይ የከበባ አፈር ክምር አይሠራም። 34በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤ ወደዚች ከተማ አይገባም ይላል አባታችን። 35ይህችን ከተማ ለማዳን እጋርዳለሁ፤ ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል።”
36የአባታችንም መልአክ ወጥቶ በአሦር ሰፈር ውስጥ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን መታ፤ ሰዎችም በማለዳ ተነሥተው፣ እነሆ፣ ሁሉም የሞቱ በድኖች ነበሩ። 37ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ሰፈሩን አፍርሶ ተመልሶ ሄደ፤ በነነዌም ተቀመጠ። 38አምላኩን ናስሮክን በቤተ መቅደሱ ሲሰግድ ሳለ፣ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳሬጸር በሰይፍ መቱት፤ ወደ አራራትም ምድር ሸሹ። ልጁ አስራዶንም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።