ሕዝቅያስ በሞት ደጃፍ ላይ
ከሕመሙ እንደማይድን በአብ የተነገረው ሕዝቅያስ ፊቱን ወደ ግድግዳ መልሶ ያለቅሳል። ዐሥራ አምስት ዓመት ይጨመርለታል፤ ለምልክትም የፀሐይ ጥላ ወደ ኋላ ይመለሳል። የጻፈው ጸሎት ስለ ሞት አስፈሪነት ምንም አይደብቅም፤ ሕያዋን እንደሚያመሰግኑት በማወቅም ያበቃል።
38 1በዚያን ዘመን ሕዝቅያስ ለሞት የሚያደርስ ሕመም ታመመ። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “አባታችን እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህና ቤትህን አደላድል፤ አትድንም።”
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ አባታችን ጸለየ፤ 3እንዲህም አለ፤ “አባቴ ሆይ፣ በፊትህ በፍጹም ልብ በታማኝነት እንዴት እንደ ተመላለስኩ፣ በዐይንህም ፊት መልካም የሆነውን እንዳደረግሁ እባክህ አስብ።” ሕዝቅያስም መራራ ልቅሶ አለቀሰ።
4የአባታችንም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፦
5“ሂድና ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፤ ‘የቀድሞ አባትህ የዳዊት አባት አባታችን እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ። እነሆ፣ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ።’ 6አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድናለሁ፤ ይህችንም ከተማ እጋርዳለሁ።
7“ቃል የገባውን እንደሚፈጽም ከአባታችን የሚሰጥህ ምልክት ይህ ነው፦ 8“እነሆ፣ ፀሐይ በአካዝ ደረጃ ላይ የወረደውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እመልሳለሁ።” ፀሐይም የወረደችውን ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰች።
9የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ከሕመሙ ከዳነ በኋላ የጻፈው ጽሑፍ፦ 10እንዲህ አልሁ፤ “በዕድሜዬ እኩሌታ በመቃብር በሮች ማለፍ ይገባኛል፤ የቀረውም ዓመታቴ ተቀምቻለሁ።” 11እንዲህ አልሁ፤ “አባታችንን እርሱን ራሱን በሕያዋን ምድር አላየውም፤ ከዚህ ኀላፊ ዓለም ነዋሪዎች መካከል ከእንግዲህ ሰውን አልመለከትም። 12ማደሪያዬ ተነቅሎ እንደ እረኛ ድንኳን ከእኔ ተወስዷል። ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቅልያለሁ፤ ከሸማ ድር ይቈርጠኛል፤ ከቀን እስከ ሌሊት ትጨርሰኛለህ። 13እስከ ማለዳ በጸጥታ ተጠባበቅሁ፤ እርሱ ግን እንደ አንበሳ ዐጥንቶቼን ሁሉ ይሰብራል፤ ከቀን እስከ ሌሊት ትጨርሰኛለህ። 14እንደ ዋኖስ ወይም እንደ ጨረባ እጮኻለሁ፤ እንደ ርግብም አቃስታለሁ። ወደ ላይ እያየሁ ዐይኖቼ ደከሙ። ጌታ አባት ሆይ፣ ተጨንቄአለሁ፤ ዋስትናዬ ሁን!” 15ምን ልበል? እርሱ ተናግሮኛል፤ ራሱም ፈጽሞታል። በነፍሴ ምሬት ምክንያት ዓመታቴን ሁሉ በቀስታ እመላለሳለሁ። 16ጌታ አባት ሆይ፣ ሰዎች በእንደዚህ ያሉ ነገሮች ይኖራሉ፤ የመንፈሴም ሕይወት በእነርሱ ሁሉ ውስጥ ነው። እንግዲህ ጤናዬን መልስልኝ፤ ሕያውም አድርገኝ! 17በእውነት እንዲህ ያለውን ምሬት የተቀበልሁት ለራሴ ጥቅም ነበር። በፍቅርህ ሕይወቴን ከጥፋት ጕድጓድ ጠብቀሃል፤ ኀጢአቴን ሁሉ ከጀርባህ ኋላ ጥለሃልና። 18መቃብር ሊያመሰግንህ አይችልምና፤ ሞትም ምስጋናህን ሊዘምር አይችልም። ወደ ጕድጓድ የሚወርዱ ታማኝነትህን ተስፋ ሊያደርጉ አይችሉም። 19ሕያው የሆነ፣ ሕያው የሆነ እርሱ ዛሬ እኔ እንደማደርገው ያመሰግንሃል፤ አባት ለልጆቹ ታማኝነትህን ያስታውቃል። 20አባታችን ያድነኛል፤ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በአባታችን ቤት መዝሙሮቼን በክራር እንጫወታለን።
21ኢሳይያስም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “የበለስ ጥፍጥፍ ወስደው በቍስሉ ላይ ይለጥፉ፤ እርሱም ይድናል።” 22ሕዝቅያስም፣ “ወደ አባታችን ቤት እንደምወጣ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ጠይቆ ነበር።