እንቍራሪቶች ምድሪቱን ወረሩ
እንቁራሪቶች ምድጃዎችንና አልጋዎችን ይወርራሉ፤ ፈርዖን የእፎይታውን ጊዜ ነገ ብሎ ይወስናል፤ ባገኘውም ጊዜ ልቡን ያደነድናል። ትቢያ አስማተኞቹ ሊያስመስሉት የማይችሉት ቅማል ይሆናል። በዝንቦቹም አብ ድንበር ያበጃል፤ ጌሤምን ይጠብቃል፤ ግብፅም ምድሪቱ የማን እንደ ሆነች ትማራለች።
8 1አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሄደህ እንዲህ በለው፤ ‘አባታችን እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ እንዲያመልኩኝ ልቀቃቸው። 2መልቀቅ ብትእምቢ ግን፣ መላ አገርህን በእንቍራሪቶች እቀጣለሁ። 3የናይል ወንዝ በእንቍራሪቶች ይርመሰመሳል፤ እነርሱም ወጥተው ወደ ቤትህ፣ ወደ መኝታ ክፍልህና ወደ አልጋህ፣ ወደ ባሪያዎችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጃዎችህና ወደ ሊጥ መቡኪያዎችህ ይገባሉ። 4እንቍራሪቶቹም በአንተ ላይ፣ በሕዝብህ ላይና በባሪያዎችህ ሁሉ ላይ ይወጣሉ።’” 5አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን በያዝህበት እጅህ በወንዞች፣ በቦዮችና በኵሬዎች ላይ ዘርጋ፤ እንቍራሪቶችንም በግብፅ ምድር ላይ አውጣ።’”
6አሮንም እጁን በግብፅ ውሃዎች ላይ ዘረጋ፤ እንቍራሪቶችም ወጥተው የግብፅን ምድር ሸፈኑ። 7ጠንቋዮቹም እንደዚሁ በስውር ጥበባቸው አደረጉ፤ እንቍራሪቶችንም በግብፅ ምድር ላይ አወጡ።
8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “እንቍራሪቶቹን ከእኔና ከሕዝቤ እንዲያስወግድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ እኔም ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲያቀርቡ እለቃቸዋለሁ።”
9ሙሴም ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “ክብሩ ያንተ ይሁን፤ ጊዜውን ራስህ ወስን፤ እንቍራሪቶቹ ከአንተና ከቤቶችህ ተለይተው በወንዙ ውስጥ ብቻ እንዲቀሩ፣ ለአንተ፣ ለባሪያዎችህና ለሕዝብህ መቼ ልጸልይ?”
10እርሱም፣ “ነገ” አለ። ሙሴም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እንዳልኸው ይሁን፤ ይህም እንደ አባታችን ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው።
11እንቍራሪቶቹ ከአንተ፣ ከቤቶችህ፣ ከባሪያዎችህና ከሕዝብህ ይርቃሉ፤ በወንዙ ውስጥ ብቻ ይቀራሉ።”
12ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም አባታችን በፈርዖን ላይ ስላመጣው እንቍራሪቶች ጒዳይ ወደ አባታችን ጮኸ። 13አባታችንም ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ እንቍራሪቶቹም በቤቶች፣ በአደባባዮችና በዕርሻዎች ውስጥ ሞቱ። 14ክምር በክምር ላይ አከማቿቸው፤ ምድሪቱም ገማች። 15ፈርዖን ግን እፎይታ እንደ ሆነ ባየ ጊዜ፣ ልቡን አደነደነ፤ አባታችን እንደ ተናገረውም አልሰማቸውም።
ከዐፈር የመጡ ትንኞች
16አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮንን እንዲህ በለው፤ በትርህን ዘርግተህ የምድሪቱን ዐፈር ምታ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ትንኝ ይሆናል።”
17እንዲሁም አደረጉ። አሮን በትሩን በያዘው እጁ የምድሩን ዐፈር መታ፤ ትንኞችም በሰውና በእንስሳት ላይ መጡ። በግብፅ ምድር ሁሉ የምድሩ ዐፈር ትንኝ ሆነ። 18ጠንቋዮቹም ትንኞችን ለማውጣት በስውር ጥበባቸው ሞከሩ፤ ነገር ግን አልቻሉም። ትንኞችም ሰውንና እንስሳትን ሸፈኑ። 19ጠንቋዮቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት። የፈርዖን ልብ ግን ደንድኖ ቀረ፤ አባታችን እንደ ተናገረውም አልሰማቸውም።
በጎሤን የተደረገ ልዩነት
20አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማለዳ ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃው ሲወጣ በፊቱ ቁም፤ እንዲህም በለው፤ ‘አባታችን እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ እንዲያመልኩኝ ልቀቃቸው።
21“ሕዝቤን ባትለቅ፣ በአንተ፣ በባሪያዎችህ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰዳለሁ። የግብፃውያንም ቤቶች በዝንብ ይሞላሉ፤ የሚቆሙባትም ምድር እንኳ ትሞላለች። 22በዚያም ቀን ሕዝቤ የሚኖሩባትን የጎሤንን ምድር እለያለሁ፤ በዚያ ዝንብ አይኖርም፤ እኔ አባትህ በምድሪቱ መካከል እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ ነው። 23በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ። ይህ ምልክት ነገ ይሆናል።’”
24አባታችንም እንዲሁ አደረገ። ብዙ የዝንብ መንጋ የፈርዖንን ቤትና የባሪያዎቹን ቤቶች ሞላ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ምድሪቱ በዝንብ መንጋ ጠፋች።
25ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፣ “ሂዱ፤ በዚች ምድር ለአምላካችሁ መሥዋዕት አቅርቡ” አለ።
26ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ተገቢ አይደለም፤ ለአባታችን የምናቀርበው መሥዋዕት ለግብፃውያን አስጸያፊ ነውና። ለእነርሱ አስጸያፊ የሆነውን በፊታቸው ብናቀርብ፣ በድንጋይ አይወግሩንምን? 27የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሄደን፣ እንዳዘዘን ለአባታችን መሥዋዕት ማቅረብ አለብን።”
28ፈርዖምም እንዲህ አለ፤ “በምድረ በዳ ለእግዚአብሔር አምላካችሁ መሥዋዕት እንድታቀርቡ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን እጅግ ሩቅ አትሂዱ። ለእኔም ለምኑ።”
29ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ዘንድ እንደ ወጣሁ ወዲያው አባታችንን እለምናለሁ፤ ነገም የዝንብ መንጋ ከፈርዖን፣ ከባሪያዎቹና ከሕዝቡ ይርቃል። ፈርዖን ግን ሕዝቡ ሄዶ ለአባታችን መሥዋዕት እንዳያቀርብ በመከልከል ዳግመኛ አያታልል።” 30ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጥቶ አባታችንን ለመነ። 31አባታችንም ሙሴ እንደ ለመነው የዝንብ መንጋ ከፈርዖን፣ ከባሪያዎቹና ከሕዝቡ አስወገደ፤ አንድም አልቀረም። 32ፈርዖን ግን በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም አልለቀቀም።