በአምልኮና በሥርዓት ያለ ክብር
በጉባኤው ውስጥ ሁለት ችግሮች አሉ፦ ወደ አብ ሲጸልዩ ራስን መሸፈን ወይም አለመሸፈን፣ እንዲሁም ባለጠጎች ቀድመው ሲበሉ ድሆች የሚራቡበት የጌታ እራት። አንዳንዶች የደከሙትና የታመሙት በዚህ ምክንያት ነው፤ ሥጋውን ሳይለዩ ይበላሉና። እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።
11 1እኔ ክርስቶስን እንደምመስል፣ እናንተም እኔን ምሰሉ።
2በሁሉ ነገር ስለምታስቡኝና ወጎቹን ለእናንተ እንዳስተላለፍሁ ጠብቃችሁ ስለያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። 3ነገር ግን እንድታውቁ የምፈልገው ይህ ነው፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ አባታችን ነው። 4ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። 5ራሷን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ግን ራሷን ታዋርዳለች፤ ይህም ራሷ እንደ ተላጨ ነው። 6ሴት ራሷን መከናነብ እምቢ ካለች፣ ጠጕሯ ይቈረጥ፤ ነገር ግን ጠጕሯ መቈረጥ ወይም ራሷ መላጨት ለሴት ነውር ስለሆነ፣ ራሷን ትከናነብ። 7ወንድ የአባታችን መልክና ክብር ስለሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። 8ወንድ ከሴት አልመጣምና፤ ሴት ግን ከወንድ መጣች። 9ደግሞም ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረም፤ ሴት ግን ስለ ወንድ ተፈጠረች። 10ስለዚህ ሴት ስለ መላእክቱ በራሷ ላይ የሥልጣን ምልክት ሊኖራት ይገባል።
11ሆኖም በጌታ ሴት ያለ ወንድ አትሆንም፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። 12ሴት ከወንድ እንደ መጣች፣ እንዲሁ ወንድ በሴት በኩል ይመጣል፤ ሁሉም ከአባታችን ነው። 13ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ራሷን ሳትከናነብ ወደ አባታችን ልትጸልይ ይገባታልን? 14ለወንድ ረጅም ጠጕር ውርደት እንደ ሆነበት ተፈጥሮ ራሱ አያስተምራችሁምን? 15ለሴት ግን ረጅም ጠጕር ቢኖራት ክብሯ ነው፤ ጠጕሯ መከናነቢያ እንዲሆናት ተሰጥቷታልና። 16ስለዚህ ነገር ለመከራከር የሚፈልግ ቢኖር፣ እኛ እንደዚህ ያለ ልማድ የለንም፤ የአባታችንም አብያተ ክርስቲያናት የላቸውም።
የጌታ ማዕድ ተዋረደ
17ይህን ትእዛዝ ስሰጥ ግን፣ መሰብሰባችሁ ለክፉ እንጂ ለበጎ ስላልሆነ አላመሰግናችሁም። 18በመጀመሪያ፣ በማኅበር በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳለ እሰማለሁና፤ ከፊሉንም አምናለሁ። 19በመካከላችሁ ያሉት እውነተኞች ይገለጡ ዘንድ፣ መለያየት በመካከላችሁ ሊኖር የግድ ነውና። 20እንግዲህ በአንድ ቦታ ስትሰበሰቡ፣ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም። 21ስትበሉ እያንዳንዱ የራሱን እራት አስቀድሞ ይበላልና፤ አንዱ ይራባል፣ ሌላውም ይሰክራል። 22የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የአባታችንን ማኅበር ትንቃላችሁ፣ የሌላቸውንም ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? ላመስግናችሁን? በዚህ ነገር አላመሰግናችሁም።
23እኔ ለእናንተ ያስተላለፍሁትን ከጌታ ተቀብዬአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት እንጀራ አንሥቶ፣
24አመስግኖም ቈረሰውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ እኔን ለማሰብ ይህን አድርጉ” አለ። 25እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ እኔን ለማሰብ ይህን አድርጉ” አለ።
26ይህን እንጀራ በበላችሁና ይህን ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።
27ስለዚህ ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ ባልተገባ ኹኔታ የጠጣ ሁሉ፣ የጌታ ሥጋና ደም በደለኛ ይሆናል። 28ሰው ራሱን ይፈትን፣ ከዚያም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ። 29ሥጋውን ሳይለይ የሚበላና የሚጠጣ ሁሉ፣ በራሱ ላይ ፍርድን ይበላል ይጠጣልና። 30ስለዚህ ከእናንተ ብዙዎች ደካሞችና ሕሙማን ናቸው፣ ብዙዎችም አንቀላፍተዋል። 31ራሳችንን ብንመረምር ኖሮ ግን፣ ባልተፈረደብንም ነበር። 32ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ፣ ከዓለም ጋራ እንዳንኰነን ይቀጣናል። 33ስለዚህ፣ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሆይ፣ ለመብላት በምትሰበሰቡ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34የተራበ ቢኖር፣ መሰብሰባችሁ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም በመጣሁ ጊዜ አስተካክላለሁ።