ከአባቶቻችን ውድቀት የተገኙ ማስጠንቀቂያዎች
እስራኤል ደመናው፣ ባሕሩና ያው መንፈሳዊ ምግብ ነበራቸው፤ ቢሆንም በምድረ በዳ ወደቁ። ይህም ለማስጠንቀቂያ ተጻፈ። ከጣዖት አምልኮ መሸሽ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን አብ ታማኝ ነው፤ መውጫም ይሰጣል። የቀረበላችሁን ብሉ፤ ሁሉንም ለክብሩ አድርጉ።
10 1ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፤ አባቶቻችን ሁሉ ከደመናው በታች እንደ ነበሩ፣ ሁሉም በባሕር መካከል እንዳለፉ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ። 2ሁሉም በደመናውና በባሕሩ ውስጥ ወደ ሙሴ ተጠመቁ። 3ሁሉም ያንኑ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ 4ሁሉም ያንኑ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ። 5አባታችን ግን ከእነርሱ በአብዛኞቹ ደስ አላለውም፤ በምድረ በዳ ተጥለው ወድቀዋልና።
6እነርሱ እንደ ተመኙ እኛ ክፉ ነገርን እንዳንመኝ፣ ይህ ሁሉ ለእኛ ምሳሌ ሆነ። 7ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንደ ነበሩ ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ ከዚያም ሊጫወቱ ተነሡ።” 8ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት በዝሙት ኀጢአት አንሥራ፤ በአንድ ቀን ውስጥ ፳፫ ሺህ ሞቱ። 9ከእነርሱ አንዳንዶቹ ክርስቶስን እንደ ፈተኑ፣ በእባቦችም እንደ ጠፉ፣ እኛ አንፈትነው። 10ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙ፣ በአጥፊውም እንደ ጠፉ፣ እናንተ አታጒረምርሙ። 11ይህ ሁሉ ለእነርሱ እንደ ምሳሌ ሆኖ ደረሰባቸው፤ የዘመናት ፍጻሜ ለደረሰብን ለእኛም ማስጠንቀቂያ ይሆን ዘንድ ተጻፈ። 12እንግዲያስ የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13ለሰው ሁሉ ከሚገጥመው በቀር ምንም ፈተና አልያዛችሁም። አባታችንም ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይፈቅድም፤ ነገር ግን ፈተናውን ልትታገሡት እንድትችሉ ከእርሱ ጋር መውጫውን ደግሞ ያዘጋጃል።
14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። 15ለአስተዋዮች እንደምናገር እናገራለሁ፤ የምለውን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16የምንባርከው የበረከት ጽዋ በክርስቶስ ደም መካፈል አይደለምን? የምንቈርሰው እንጀራ በክርስቶስ ሥጋ መካፈል አይደለምን? 17አንድ እንጀራ ስላለ፣ ሁላችን ያንኑ አንዱን እንጀራ ስለምንካፈል፣ እኛ ብዙዎች አንድ ሥጋ ነን። 18የእስራኤልን ሕዝብ ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ በመሠዊያው ተካፋዮች አይደሉምን? 19እንግዲያስ ምን እያልሁ ነው? ለጣዖት የተሠዋ ምግብ ምንም ነው፣ ወይስ ጣዖት ምንም ነው ማለቴ ነውን? 20አይደለም፤ ነገር ግን አባታችንን የማያውቁ የሚሠዉት፣ ለአባታችን ሳይሆን ለአጋንንት ይሠዋሉ፤ እናንተ ከአጋንንት ጋር ተካፋዮች እንድትሆኑ አልፈልግም። 21የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ የጌታን ማዕድና የአጋንንትን ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። 22ወይስ ጌታን ለቅናት እናስነሣዋለንን? ከእርሱ እንበረታለንን?
23“ሁሉ ተፈቅዶአል”፤ ነገር ግን ሁሉ አይጠቅምም። “ሁሉ ተፈቅዶአል”፤ ነገር ግን ሁሉ አያንጽም። 24ማንም የራሱን ጥቅም አይሻ፤ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ። 25ስለ ሕሊና ምንም ሳትጠይቁ፣ በሥጋ መሸጫ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ 26“ምድርና በውስጧ ያለው ሁሉ የአባታችን ነውና።” 27የማያምን ሰው ወደ ግብዣ ቢጠራችሁ መሄድም ብትፈልጉ፣ ስለ ሕሊና ምንም ሳትጠይቁ፣ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። 28ነገር ግን አንድ ሰው፣ “ይህ የተሠዋ ነው” ብሎ ቢነግራችሁ፣ ስለ ነገራችሁ ሰውና ስለ ሕሊና ሲባል አትብሉት፤ 29የማለውም የራሳችሁን ሕሊና ሳይሆን የሌላውን ነው። ነጻነቴ በሌላው ሕሊና ለምን ይፈረድበታል? 30እኔ በምስጋና ብበላ፣ ስለማመሰግንበት ነገር ለምን እወቀሳለሁ?
31እንግዲያስ ብትበሉ፣ ብትጠጡ፣ ወይም ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ፣ ሁሉን ለአባታችን ክብር አድርጉት። 32ለአይሁድ ቢሆን፣ ለግሪኮች ቢሆን፣ ለአባታችን ቤተ ክርስቲያን ቢሆን መሰናክል አትሁኑ፤ 33እኔም የብዙዎች እንዲድኑ፣ የራሴን ጥቅም ሳልሻ የብዙዎችን ጥቅም እንጂ፣ በሁሉ ነገር ሁሉን ደስ ለማሰኘት እጥራለሁ።