የዳዊት ቤት እየበረታ ሄደ
የሳኦል ቤት እየደከመ ሲሄድ አበኔር በአንዲት ቁባት ምክንያት ይከሰሳል፤ አብ የማለውን መንግሥት ለዳዊት ሊያስረክብ ወደ እርሱ ይዞራል፤ እስራኤልንም ይዞ ይመጣል። ኢዮአብ የአሣሄልን ደም ለመበቀል አበኔርን በበሩ ላይ ይገድለዋል። ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ይሄዳል፣ ይጾማል፣ ይያለቅሳልም፤ በዚህም እርሱ ተካፋይ እንዳልነበረ ሁሉም ያውቃል።
3 1በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የተደረገው ጦርነት ረጅም ጊዜ ዘለቀ። ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ፤ የሳኦል ቤት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ ሄደ። 2በኬብሮንም ለዳዊት ወንዶች ልጆች ተወለዱ። የበኵር ልጁ አምኖን ነበር፤ እናቱም የይዝራኤል ሴት አኪኖዓም ነበረች፤ 3ሁለተኛው ኪልዓብ ነበር፤ እናቱም የቀርሜሎሱ የናባል መበለት አቢግያ ነበረች፤ ሦስተኛው የጌሶር ንጉሥ የተልማይ ልጅ የመዓካ ልጅ አቤሴሎም ነበር፤ 4አራተኛው የሐጊት ልጅ አዶንያስ ነበር፤ አምስተኛው የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያ ነበር፤ 5ስድስተኛው የዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደ ይትሬዓም ነበር። እነዚህ በኬብሮን ለዳዊት የተወለዱ ልጆች ናቸው።
አበኔር ከዳዊት ጋራ ተባበረ
6በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ጦርነቱ በቀጠለበት ጊዜ፣ አበኔር በሳኦል ቤት ውስጥ ራሱን እያጠናከረ ሄደ። 7ሳኦልም ራጽጳ የተባለች የአያ ልጅ ቁባት ነበረችው። ኢሳቦስቴም አበኔርን፣ “ከአባቴ ቁባት ጋራ ለምን ተኛህ?” አለው።
8አበኔርም በኢሳቦስቴ ቃል እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለይሁዳ ያደረ የውሻ ራስ ነኝን? ዛሬ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፣ ለወንድሞቹና ለወዳጆቹ ታማኝነትን እያሳየሁ፣ ለዳዊት እጅ አላሳልፍሁህም። አንተ ግን ዛሬ ስለዚህች ሴት ትከስሰኛለህ! a a v8 ‘የውሻ ራስ’ የሚለው ጥንታዊ ስድብ ሆኖ፣ ዋጋ ለሌለው ከዳተኛ ወይም ጠላት ይነገር ነበር። 9ለዳዊት አባታችን የማለለትን ካላደረግሁለት፣ አባታችን በአበኔር እንዲህ ያድርግ፣ ከዚህም የባሰ ያድርግ፤ 10ይኸውም መንግሥትን ከሳኦል ቤት አዛውሮ፣ የዳዊትን ዙፋን ከዳን እስከ ቤርሳቤህ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ለማጽናት ነው።”
11ኢሳቦስቴም ስለ ፈራው፣ ለአበኔር ሌላ ቃል መመለስ አልቻለም።
12አበኔርም ስለ ራሱ ወደ ዳዊት መልእክተኞችን ልኮ፣ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋራ ኪዳንህን አድርግ፤ እጄም ከአንተ ጋራ ሆኖ እስራኤልን ሁሉ ወደ አንተ ያዞራል” አለ።
13ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “መልካም፤ ከአንተ ጋራ ኪዳን አደርጋለሁ። ነገር ግን አንድ ነገር እሻለሁ፤ ስትመጣ አስቀድመህ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህ በቀር ፊቴን አታይም።” 14ዳዊትም ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢሳቦስቴ መልእክተኞችን ልኮ፣ “በመቶ የፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ያጫሁትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” አለ።
15ኢሳቦስቴም ልኮ ከባልዋ ከላይስ ልጅ ከፈልጥኤል ወሰዳት። 16ባልዋም እስከ ባሁሪም ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ። አበኔርም፣ “ተመለስ” አለው፤ እርሱም ተመለሰ።
17አበኔርም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋራ ተነጋግሮ እንዲህ አለ፤ “ዳዊት በእናንተ ላይ ንጉሥ እንዲሆን ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ትሹ ነበር። 18አሁንም አድርጉት፤ አባታችን ዳዊትን፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት እጅ ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያንና ከጠላቶቻቸው ሁሉ አድናለሁ’ ብሎ ቃል ገብቶለታልና።”
19አበኔርም ደግሞ ለብንያም ተናገረ፤ ከዚያም እስራኤልና የብንያም ቤት ሁሉ ሊያደርጉ የተስማሙበትን ሁሉ ለዳዊት ሊነግር ወደ ኬብሮን ሄደ። 20አበኔርም ከሃያ ሰዎች ጋራ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፣ ዳዊት ለአበኔርና ለሰዎቹ ግብዣ አደረገ። 21አበኔርም ዳዊትን፣ “ሄጄ እስራኤልን ሁሉ ወደ ጌታዬ ወደ ንጉሡ እሰበስባለሁ፤ ከአንተም ጋራ ኪዳን ያደርጋሉ፤ አንተም ልብህ በሚሻው ሁሉ ላይ ትነግሣለህ” አለው። ዳዊትም አበኔርን አሰናበተው፤ እርሱም በሰላም ሄደ።
ኢዮአብ አበኔርን ገደለ
22በዚያም ጊዜ የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮአብ ብዙ ምርኮ ይዘው ከወረራ ተመለሱ። አበኔር ግን በኬብሮን ከዳዊት ጋራ አልነበረም፤ ዳዊት አሰናብቶት ነበርና፣ እርሱም በሰላም ሄዶ ነበር። 23ኢዮአብና ሰራዊቱ ሁሉ በደረሱ ጊዜ፣ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጥቶ ነበር፤ ንጉሡም አሰናበተው፤ እርሱም በሰላም ሄደ” ተብሎ ተነገረው።
24ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ እንዲህ አለ፤ “ምን አደረግህ? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ነበር፤ ለምን አሰናበትኸው? አሁንም ሄደ! 25የኔር ልጅ አበኔር ሊያታልልህ፣ መውጫ መግቢያህንና የምታደርገውን ሁሉ ሊያውቅ እንደ መጣ ታውቃለህ።”
26ኢዮአብም ከዳዊት ዘንድ ወጥቶ፣ በአበኔር ኋላ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ከሲራ ጕድጓድ መልሰው አመጡት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም። 27አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፣ ኢዮአብ ለብቻው ሊያናግረው እንደ ፈለገ መስሎ በበሩ መካከል ወደ ጎን ወሰደው፤ በዚያም ሆድ ዕቃውን ወግቶ ገደለው፤ ሞተም፤ ይኸውም ስለ ኢዮአብ ወንድም ስለ አሳሄል ደም ነበር። 28ከዚያም በኋላ ዳዊት በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔና መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም የተነሣ በአባታችን ፊት ለዘላለም ንጹሓን ነን። 29ደሙም በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይውደቅ! በኢዮአብ ቤትም ፈሳሽ ያለበት ወይም ለምጻም፣ በበትር የሚመረኰዝ፣ በሰይፍ የሚወድቅ ወይም እንጀራ የሚያጣ ሰው አይታጣ።” 30ስለዚህ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ በገባዖን ጦርነት ወንድማቸውን አሳሄልን ስለ ገደለ አበኔርን ገደሉት።
ዳዊት ስለ አበኔር አለቀሰ
31ዳዊትም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋራ ያሉትን ሕዝብ ሁሉ፣ “ልብሳችሁን ቅደዱ፤ ማቅ ልበሱ፤ በአበኔርም ፊት አልቅሱ” አላቸው። ንጉሡ ዳዊትም ከሬሳው ሳጥን ኋላ ሄደ። 32አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በመቃብሩ ዘንድ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሰ። 33ንጉሡም ለአበኔር እንዲህ ብሎ ሙሾ አወጣ፤ “አበኔር ሞኝ እንደሚሞት በሞተ መሞት ነበረበትን? 34እጆችህ አልታሰሩም፣ እግሮችህም በሰንሰለት አልተጠፈሩም። በክፉዎች ፊት እንደሚወድቅ ሰው ወደቅህ።” ሕዝቡም ሁሉ እንደ ገና አለቀሰለት።
35ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ገና ቀን ሳለ ዳዊት ምግብ እንዲበላ ሊያስገድዱት መጡ፤ ዳዊት ግን፣ “ፀሓይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ማናቸውንም ነገር ብቀምስ፣ አባታችን እንዲህ ያድርግብኝ፣ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ!” ብሎ ማለ።
36ሕዝቡም ሁሉ ተመለከተ፤ ደስም አለው፤ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ሁሉ ደስ አሰኘው። 37በዚያም ቀን ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል ሁሉ የኔር ልጅ አበኔር እንዲገደል ንጉሡ እንዳልፈለገ አወቁ። 38ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ “ዛሬ በእስራኤል አንድ አለቃና ታላቅ ሰው እንደ ወደቀ አታውቁምን? 39ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም ደካማ ነኝ፤ እነዚህም ሰዎች የጽሩያ ልጆች ከኔ ይልቅ ብርቱ ናቸው። አባታችን ክፉ ለሚያደርገው ሰው እንደ ክፋቱ ይከፍለው።”