በአንቺ ነውር የለም
ሰውየው ሴቲቱን በየአካሏ ያመሰግናታል፤ ሙሽራዬ፣ እኅቴ ብሎ ይጠራታል፤ በእርሷ ዘንድ ምንም ነውር እንደሌለ ይናገራል። እርሷ የተቈለፈ የአትክልት ስፍራ፣ የታተመ ምንጭ፣ ለእርሱ ብቻ የሆነች ናት። በመጨረሻ እርሷ ትመልሳለች፤ ነፋሱን ትጠራለች፤ ያንን የአትክልት ስፍራ ራሷ ትከፍታለች።
4 1ውዴ ሆይ፣ እንዴት ውብ ነሽ፤ እንዴት ውብ ነሽ! ዐይኖችሽ ከመሸፈኛሽ ጀርባ ያሉ ርግቦች ናቸው። ጠጒርሽ ከገለዓድ ተራራ ተዳፋት የሚንደረደር የፍየሎች መንጋ ይመስላል። 2ጥርሶችሽ አሁን ተሸልተው ከመታጠቢያ እንደሚወጡ የበጎች መንጋ ናቸው፤ እያንዳንዷ መንታ የወለደች ናት፤ ከእነርሱም መካከል ልጅ ያጣች አንዲትም የለችም። 3ከንፈሮችሽ እንደ ደማቅ ቀይ ክር ናቸው፤ አፍሽም ያማረ ነው። ጒንጮችሽ ከመሸፈኛሽ ጀርባ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው። 4አንገትሽ እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ በድንጋይ ረድፎች የተሠራ ነው፤ ሺህ ጋሻዎችም በእርሱ ላይ ተሰቅለዋል፤ ሁሉም የጦረኞች ጋሻ ናቸው። 5ሁለቱ ጡቶችሽ በአበቦች መካከል እንደሚሰማሩ ሁለት የሚዳቋ ግልገሎች፣ የሚዳቋ መንታዎች ናቸው። 6ቀኑ እስኪነፍስ ጥላዎቹም እስኪሸሹ ድረስ፣ ወደ ከርቤ ተራራ፣ ወደ ዕጣን ኮረብታም እሄዳለሁ። 7ውዴ ሆይ፣ ፍጹም ውብ ነሽ፤ በአንቺም ምንም ነውር የለም።
8ሙሽራዬ ሆይ፣ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ። ከአማና ጫፍ፣ ከሴኔርና ከኤርሞን ጫፍ፣ ከአንበሶች ጒረኖ፣ ከነብሮች ተራራ መኖሪያ ዝቅ ብለሽ ተመልከች። 9እኅቴ፣ ሙሽራዬ ሆይ፣ ልቤን ማረክሽው፤ በአንዲት የዐይንሽ ቅጽበት፣ በአንዲት የአንገትሽ ሐብል ዕንቍ ልቤን ማረክሽው። 10እኅቴ፣ ሙሽራዬ ሆይ፣ ፍቅርሽ እንዴት ውብ ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ እንዴት ይበልጣል፤ የሽቶዎችሽም መዐዛ ከማንኛውም ሽቱ ይበልጣል። 11ሙሽራዬ ሆይ፣ ከንፈሮችሽ ማር ያንጠፈጥፋሉ፤ ማርና ወተት ከምላስሽ ሥር ናቸው፤ የልብስሽም መዐዛ እንደ ሊባኖስ መዐዛ ነው።
12እኅቴ፣ ሙሽራዬ የተቈለፈ የአትክልት ስፍራ ናት፤ የተቈለፈ ምንጭ፣ የታተመ ፈሳሽ ናት። 13ቅርንጫፎችሽ ምርጥ ፍሬዎች ያሉት የሮማን አትክልት ናቸው፤ ሄናና ናርዶስ፣ 14ናርዶስና ዛዕፈራን፣ ቃሊሞስና ቀረፋ፣ ከዕጣን ዛፍ ሁሉ ጋር፣ ከከርቤና ከእሬት ጋር፣ ከሁሉም ምርጥ ሽቱዎች ጋር። a a v14 ቃሊሞስ እንደ ሽቱ የሚያገለግል ጥሩ መዐዛ ያለው ሸምበቆ ነው። 15አንቺ የአትክልት ስፍራ ምንጭ፣ የሕያው ውሃ ጒድጓድ ነሽ፤ ከሊባኖስም የሚወርዱ ፈሳሾች ነሽ። 16ሰሜናዊ ነፋስ ሆይ፣ ንቃ፤ ደቡባዊ ነፋስ ሆይ፣ ና! በአትክልቴ ላይ ንፈስ፤ ሽቱዎቹ እንዲፈሱ አድርግ። ውዴ ወደ አትክልቱ ይምጣ፤ ምርጥ ፍሬዎቹንም ይብላ።