ተላላ ተላላነቱን ይደግማል
የሦስት ዓይነት ሰዎች ዝርዝር ማለት ይቻላል። ሊከበር፣ ሊቀጠር ወይም ሊፈወስ የማይችል ሰነፍ፤ በር በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር በአልጋው ላይ የሚገላበጥ ታካች፤ ካቆሰለ በኋላ «እየቀለድሁ ነበር» የሚል አታላይ። ጕድጓድ የሚቈፍር ራሱ ይወድቅበታል።
26 1በበጋ እንደሚወርድ በረዶ፣ በመከር ወቅትም እንደሚዘንብ ዝናብ፣ ክብር ለተላላ አይገባውም። 2እንደሚንፈራፈር ድንቢጥ፣ ወይም እንደሚበር ጨረባ፣ ያለ ምክንያት የተነገረ እርግማን አያርፍም። 3ለፈረስ አለንጋ፣ ለአህያ ልጓም፣ ለተላሎች ጀርባም በትር ነው። 4ለተላላ እንደ ተላላነቱ አትመልስለት፤ አለዚያ አንተ ራስህ እንደ እርሱ ትሆናለህ። 5ለተላላ እንደ ተላላነቱ መልስለት፤ አለዚያ በራሱ ዐይን ጥበበኛ ይሆናል። 6በተላላ እጅ መልእክት የሚልክ፣ የራሱን እግር ይቈርጣል፤ ዐመፅንም ይጠጣል። 7በተላላ አፍ ያለ ምሳሌ፣ እንደ ዐንካሳ ሰው ቅል እግር ነው። 8ለተላላ ክብርን መስጠት፣ በወንጭፍ ድንጋይን እንደ ማሰር ነው። 9በተላላ አፍ ያለ ምሳሌ፣ በሰካራም እጅ እንዳለ እሾኽ ነው። 10ተላላን የሚቀጥር ወይም ማንኛውንም መንገደኛ የሚቀጥር፣ ሁሉን እንደሚያቈስል ቀስተኛ ነው። 11ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ፣ ተላላም ተላላነቱን እንዲሁ ይደግማል። 12በራሱ ዐይን ጥበበኛ የሆነ ሰው ታያለህን? ከእርሱ ይልቅ ለተላላ ተስፋ አለው።
13ሰነፍ ሰው፣ “በመንገድ ላይ አንበሳ አለ! በአደባባዩም አንበሳ አለ!” ይላል። 14በር በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፣ ሰነፍ ሰውም በዐልጋው ላይ እንዲሁ ይገላበጣል። 15ሰነፍ ሰው እጁን በወጭቱ ውስጥ ይከታል፤ ወደ አፉ መልሶ ለማምጣትም ይታክታል። 16ሰነፍ ሰው ጥበብ ባለው መልስ ከሚመልሱ ሰባት ሰዎች ይልቅ፣ በራሱ ዐይን ጥበበኛ ነው።
17የራሱ ባልሆነ ጠብ ውስጥ ጣልቃ የሚገባ መንገደኛ፣ ውሻን ጆሮውን ይዞ እንደሚጐትት ነው።
18የእሳት ችቦ፣ ፍላጻና ሞት እንደሚወረውር ዕብድ፣ 19ባልንጀራውን አታሎ፣ “ቀልጄ ነበር!” የሚል ሰው እንዲሁ ነው።
20ዕንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ ሐሜተኛም ከሌለ ጠብ ይበርዳል። 21ከሰል ለፍም፣ ዕንጨትም ለእሳት እንደሚሆን፣ ጠበኛ ሰውም ጥልን እንዲሁ ያነድዳል። 22የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤ ወደ ሆድ ውስጥም ዘልቆ ይወርዳል።
23ክፉ ልብ ያለው ለስላሳ ከንፈር፣ የሸክላ ዕቃን እንደሚሸፍን ብረቶ ነው። 24ጠላት በከንፈሩ ራሱን ይሰውራል፣ በልቡ ውስጥ ግን ተንኰልን ይሰበስባል። 25ለዛ ባለው ቃል ሲናገር አትመነው፤ ሰባት ርኵሰቶች ልቡን ሞልተውታልና። 26ጥላቻው በተንኰል ቢሰወርም፣ ክፋቱ በጉባኤ ፊት ይጋለጣል። 27ጒድጓድ የሚቈፍር ወደ እርሱ ይወድቃል፤ ድንጋይም የሚያንከባልለው ላይ ተመልሶ ይንከባለላል። 28ሐሰተኛ ምላስ የሚያደቅቃቸውን ይጠላል፤ አሞጋጋሽ አፍም ጥፋትን ያመጣል።