ብረት ብረትን ይስላል
ወዳጅነት በቅንነት ይመረመራል። የተገለጠ ተግሣጽ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል፤ የወዳጅ ማቁሰል የታመነ ነው፤ ብረት ብረትን ይስለዋል። ስለ ነገም መመካትን ያስጠነቅቃል፤ ምስጋናንም የባሕርይ መፈተኛ አድርጎ ያያል፤ ከዚያም ሀብት ለዘላለም ስለማይኖር በበጎችና በከብቶች ይደመደማል።
27 1ነገ ስለሚሆነው ነገር አትመካ፤ አንድ ቀን ምን እንደሚያመጣ አታውቅምና። 2የገዛ አፍህ ሳይሆን ሌላ ሰው ያመስግንህ፤ የገዛ ከንፈርህ ሳይሆን እንግዳ ያወድስህ። 3ድንጋይ ከባድ ነው፤ አሸዋም ሸክም ነው፤ የተላላ ሰው ማስቈጣት ግን ከሁለቱም ይከብዳል። 4ቍጣ ጨካኝ ነው፤ መዓትም የሚያጥለቀልቅ ነው፤ በቅናት ፊት ግን ማን ሊቆም ይችላል? 5ግልጥ ተግሣጽ ተሰውሮ ከሚኖር ፍቅር ይሻላል። 6የወዳጅ ቍስል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን አታላይ ነው። 7የጠገበ ሰው የማር ወለላን ይረግጣል፤ ለተራበ ግን መራራውም ነገር እንኳ ጣፋጭ ይሆናል። 8ከቤቱ የሚንከራተት ሰው ከጎጆዋ እንደምትንከራተት ወፍ ነው። 9ዘይትና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ የወዳጅ ጣፋጭነትም ከልብ ከመነጨ ምክር ይመጣል። 10ወዳጅህን ወይም የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ መከራ በመጣብህ ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትሂድ፤ ከሩቅ ወንድም ይልቅ በቅርብ ያለ ጎረቤት ይሻላል። 11ልጄ ሆይ፤ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኝ፤ የሚያፌዝብኝን ሁሉ መልስ እሰጠው ዘንድ። 12ብልኅ ሰው አደጋን አይቶ ይሸሸጋል፤ የዋህ ግን ገፍቶ ሄዶ ይቀጣል። 13ለእንግዳ ዋስ የሆነውን ሰው ልብስ ውሰድ፤ ለባዕድ ሴት ዋስ በሆነ ጊዜ ልብሱን በማስያዣነት ያዝ። 14ማልዶ በመነሣት ባልንጀራውን በታላቅ ድምፅ የሚባርክ ሰው፤ እንደ መርገም ይቈጠርበታል። 15ጨቃጫቂ ሚስት በዝናብ ቀን እንደ ማያቋርጥ ጠብታ ናት። 16እርሷን መግታት ነፋስን እንደ መግታት ነው፤ ወይም ዘይትን በቀኝ እጅ እንደ መጨበጥ ነው። 17ብረት ብረትን ይስላል፤ ሰውም ሰውን ይስላል። 18በለስን የሚንከባከብ ፍሬዋን ይበላል፤ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከበራል። 19ውሃ ፊትን እንደሚያሳይ፤ እንዲሁ ልብ ሰውን ያሳያል። 20ሲኦልና ጥፋት ከቶ አይጠግቡም፤ የሰውም ዐይኖች ከቶ አይጠግቡም። a a v20 ሲኦል የሙታን ዓለም ነው፤ አባዶን የጥፋት ስፍራ ነው፤ ሁለቱም በአንድነት ከቶ የማይሞላ ረኀብን ይስላሉ። 21ማቅለጫው ለብር፤ እቶኑም ለወርቅ ነው፤ ሰውም በሚያገኘው ምስጋና ይፈተናል። 22ተላላውን ሰው በሙቀጫ ውስጥ በዘነዘና ብትወቅጠው፤ ከእህሉ ጋራ እንኳ፤ ተላላነቱ ከእርሱ አይለይም። 23የመንጋህን ሁኔታ በሚገባ ዕወቅ፤ ለከብቶችህም ጥንቃቄ አድርግ። 24ሀብት ለዘላለም አይኖርምና፤ ዘውድም ለልጅ ልጅ ሁሉ አይጸናም። 25ሣሩ ሲያልፍ፤ አዲሱም ቡቃያ ሲበቅል፤ የተራራውም ዕፅዋት ሲሰበሰቡ፤ 26ጠቦቶቹ ልብስህን ይሰጡሃል፤ ፍየሎቹም የእርሻ ዋጋ ይሆኑሃል፤ 27ለአንተ ምግብ፤ ለቤተ ሰብህም ምግብ የሚበቃ የፍየል ወተት ይኖራል፤ ገረዶችህንም ለመመገብ ይበቃል።