እንደ አንበሳ ደፋር
ሥልጣንና ገንዘብ በአንድነት። ያመፀች ምድር ብዙ ገዢዎች አሏት፤ ክፉ ገዢ እንደሚያጠቃ ድብ ነው፤ ክፉዎች ሲነሡ ሰዎች ይሸሸጋሉ። ኃጢአትን መሸሸግ አያከናውንም፤ መናዘዝ ግን ምሕረትን ያገኛል፤ ለመበልጸግ መቸኮልም ሰውን የሚያጠፋ ነገር ተብሎ ደጋግሞ ይጠራል።
28 1ክፉዎች የሚያሳድዳቸው ሳይኖር ይሸሻሉ፤ ጻድቃን ግን እንደ አንበሳ ደፋር ናቸው። 2አገር በምታምፅበት ጊዜ ብዙ ገዦች ይኖሯታል፤ አስተዋይና ዐዋቂ ሰው ሲኖር ግን ጸንታ ትኖራለች። 3ድኻ ሆኖ ችግረኛውን የሚጨቍን ሰው ምግብ የማያስቀር አውዳሚ ዝናብ ይመስላል። 4ሕግን የሚተዉ ክፉዎችን ያመሰግናሉ፤ ሕግን የሚጠብቁ ግን ይቃወሟቸዋል። 5ክፉ ሰዎች ፍትሕን አያስተውሉም፤ አባታችንን የሚሹ ግን ፈጽመው ያስተውሉታል። 6በቅንነት የሚመላለስ ድኻ፣ መንገዱ ጠማማ ከሆነ ባለጠጋ ይሻላል። 7ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤ የሆዳሞች ባልንጀራ ግን አባቱን ያሳፍራል። 8ሀብቱን በአራጣና በዐመፃ ትርፍ የሚያበዛ፣ ለድኾች ለሚራራ ሰው ያከማቸዋል። 9ማንም ሕግን ለመስማት እምቢ ቢል፣ ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው። 10ቅኖችን ወደ ክፉ መንገድ የሚያስት፣ እርሱ ራሱ በጕድጓዱ ውስጥ ይወድቃል፤ ነውር የሌለባቸው ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ። 11ባለጠጋ በራሱ ዓይን ጥበበኛ ነው፤ አስተዋይ ድኻ ግን አጥርቶ ያየዋል። 12ጻድቃን ሲያሸንፉ ታላቅ ክብር ይሆናል፤ ክፉዎች ሲነሡ ግን ሰዎች ይሸሸጋሉ። 13ኀጢአቱን የሚሰውር አይከናወንለትም፤ የሚናዘዝና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። 14ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈራ ብፁዕ ነው፤ ልቡን የሚያደነድን ግን ወደ መከራ ይወድቃል። 15እንደሚያገሣ አንበሳ ወይም እንደሚያጠቃ ድብ፣ በችግረኛ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ ገዥ እንዲሁ ነው። 16አስተዋይነት የጐደለው ገዥ ጨካኝ አስጨናቂ ነው፤ ዐመፃ ትርፍን የሚጠላ ግን ዕድሜውን ያረዝማል። 17በደም ባለውለታ የተጫነ ሰው እስከ ሞት ድረስ ሸሽቶ ይኖራል፤ ማንም አይደግፈው። 18በቅንነት የሚመላለስ ይጠበቃል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን በድንገት ይወድቃል። 19መሬቱን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ከንቱ ነገርን የሚከታተል ግን ድኽነት ይጠግባል። 20ታማኝ ሰው በበረከት ይትረፈረፋል፤ ለመክበር የሚቸኩል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። 21አድልዎ ማድረግ መልካም አይደለም፤ ሰው ስለ አንድ ቍራሽ እንጀራ ግን በደል ያደርጋል። 22ስስታም ሰው ሀብትን ለማግኘት ይቸኩላል፤ ድኽነት እንደሚደርስበትም አያውቅም። 23ሰውን የሚገሥጽ በመጨረሻ ይበልጥ ሞገስን ያገኛል፤ በአንደበቱ ከሚያሞካሽ ይልቅ። 24አባቱን ወይም እናቱን ዘርፎ፣ “ኀጢአት አይደለም” የሚል፣ ለሚያጠፋ ሰው ባልንጀራ ነው። 25ስግብግብ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ በአባታችን የሚታመን ግን ይበለጽጋል። 26በራሱ ልብ የሚታመን ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚመላለስ ግን ይጠበቃል። 27ለድኾች የሚሰጥ ምንም አይጐድልበትም፤ ዓይኑን ከእነርሱ የሚሰውር ግን ብዙ ርግማንን ይቀበላል። 28ክፉዎች ሲነሡ ሰዎች ይሸሸጋሉ፤ ሲጠፉ ግን ጻድቃን ይበራከታሉ።