ራእይ በሌለበት
ስለ ገዢዎች፣ ስለ ቍጣና ስለ ልጆች። ጻድቃን ሲበዙ ሕዝብ ደስ ይለዋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ያቃስታል። ሰነፍ ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ በንግግሩ የሚቸኩል ሰው ከሰነፍ ይልቅ የከፋ ነው። ራእይ በሌለበት ሕዝብ ልቅ ይሆናል።
29 1ብዙ ጊዜ እየተገሠጸ ለመስማት እምቢ የሚል ሰው፣ ድንገት ይሰበራል፤ ፈውስም አይገኝለትም። 2ጻድቃን ሲበረክቱ፣ ሕዝቡ ደስ ይለዋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን፣ ሕዝቡ ያቃስታል። 3ጥበብን የሚወድድ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤ የጋለሞታዎች ባልንጀራ ግን ሀብቱን ያባክናል። 4ንጉሥ በፍትሕ ለአገር ጽናትን ይሰጣል፤ መማለጃን በመጐምጀት ግን ያፈርሰዋል። 5ባልንጀራውን የሚያቆላምጥ ሰው ለእግሩ መረብ ይዘረጋል። 6ክፉ ሰው በገዛ ኀጢአቱ ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ይዘምራል፤ ደስም ይለዋል። 7ጻድቅ ለድኾች ፍትሕ ያስባል፤ ክፉ ግን እንዲህ ያለ ማስተዋል የለውም። 8ዘባቾች ከተማን ያቃጥላሉ፤ ጥበበኞች ግን ቍጣን ያበርዳሉ። 9ጠቢብ ሰው ከሞኝ ጋራ ወደ ፍርድ ሲሄድ፣ ሞኙ ይቈጣል፤ ይሳለቃልም፤ ሰላምም የለም። 10ደም የሚጠሙ ነውር የሌለበትን ይጠላሉ፤ ቅኖችንም ለመግደል ይፈልጋሉ። 11ሞኝ ቍጣውን ሁሉ ይገልጣል፤ ጠቢብ ግን ይገታዋል፤ ራሱንም ያረጋጋል። 12አንድ ገዥ ውሸትን ቢያዳምጥ፣ ሹማምንቱ ሁሉ ክፉዎች ይሆናሉ። 13ድኻውና ጨቋኙ የሚያመሳስላቸው ይህ ነው፦ አባታችን የሁለቱንም ዐይን ያበራል። 14ንጉሥ ድኾችን በቅንነት ቢፈርድ፣ ዙፋኑ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። 15በትርና የተግሣጽ ቃል ጥበብን ይሰጣሉ፤ ለራሱ የተተወ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል። 16ክፉዎች ሲበረክቱ፣ ዐመፅ ይበዛል፤ ጻድቃን ግን የክፉዎችን ውድቀት ያያሉ። 17ልጅህን ቅጣው፤ ዕረፍትን ይሰጥሃል፤ ልብህንም ደስ ያሰኛል። 18ራእይ በሌለበት፣ ሕዝቡ ልቅ ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን ብፁዕ ነው። 19ባሪያ በቃል ብቻ አይገሠጽም፤ ቢያስተውልም እንኳ፣ አይታዘዝም። 20በንግግሩ የሚቸኩል ሰው ታያለህን? ከእርሱ ይልቅ ለሞኝ ተስፋ አለው። 21ባሪያን ከልጅነቱ ጀምሮ ብታቀማጥለው፣ በመጨረሻ እንደ ወራሽ ይሆናል። 22ቍጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ፈጣን ቍጡም ብዙ ኀጢአት ይሠራል። 23የሰው ትዕቢት ዝቅ ያደርገዋል፤ ትሑት መንፈስ ግን ክብርን ያገኛል። 24የሌባ ተባባሪ የገዛ ራሱ ጠላት ነው፤ መርገምን ይሰማል፤ ነገር ግን ምንም አይናገርም። a a v24 “መርገም” ማለት ወንጀሉን ያየ ሰው ሁሉ ቀርቦ እንዲመሰክር የሚያስገድድ ይፋዊ መሐላ ነው። 25ሰውን መፍራት ወጥመድ ይዘረጋል፤ በአባታችን የሚታመን ግን ተጠብቆ ይኖራል። 26ብዙዎች የገዥን ሞገስ ይፈልጋሉ፤ ለሰው ፍትሕ ግን ከአባታችን ይመጣል። 27ዐመፀኛ ሰው ለጻድቃን አስጸያፊ ነው፤ ቅን ሰውም ለክፉዎች አስጸያፊ ነው።