የአጉር ኑዛዜ
አጉር እንደ ደከመና የራሱ የሆነ ጥበብ እንደሌለው ለአብ ይናዘዛል፤ ከዚያም አንድ ነገር ይለምናል፦ ድህነትም ባለጠግነትም ሳይሆን የሚበቃውን እንጀራ ብቻ። ቀሪው በጣቶቹ ይቈጥራል፦ ፈጽሞ የማይጠግቡ አራት ነገሮች፣ እጅግ የሚያስደንቁ አራት፣ ትንሽ ሆነው ጠቢባን የሆኑ አራት።
30 1የያቄ ልጅ የአጉር ቃላት፤ ራእዩ። ሰውየው እንዲህ ይላል፦ ደክሞኛል፣ አባቴ ሆይ፤ ደክሞኛል፣ አባቴ ሆይ፣ ዝልፍልፍም ሆኛለሁ። 2በእርግጥ ሰው ለመባል እጅግ ደንዳና ነኝ፤ የሰውም ማስተዋል የለኝም። 3ጥበብን አልተማርኩም፤ የቅዱሱንም ዕውቀት የለኝም። 4ወደ ሰማይ ዐርጎ የወረደ ማን ነው? ነፋስን በእጁ መዳፍ የሰበሰበ ማን ነው? ውሃዎችን በልብስ የጠቀለለ ማን ነው? የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የመሠረተ ማን ነው? ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ነው? በእርግጥ ታውቃለህ! a a v4 አጉር እነዚህን ነገሮች ያደረገ ማን እንደ ሆነ፣ የልጁም ስም ማን እንደ ሆነ ይጠይቃል። ኢየሱስ ለዚህ እንቆቅልሽ መለሰ፦ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ ያረገ ማንም የለም” (ዮሐንስ ፫፥፲፫)። አብ ልጅ አለው። 5የአባታችን ቃል ሁሉ እውነት ሆኖ ይገኛል፤ በእርሱ ለሚጠለሉ እርሱ ጋሻ ነው። 6በቃሉ ላይ አንዳች አትጨምር፤ አለዚያ ይገሥጽሃል፤ ሐሰተኛም ሆነህ ትገኛለህ። 7ሁለት ነገር ከአንተ እጠይቅሃለሁ፤ ሳልሞት እነርሱን አትከልክለኝ፦ 8ሐሰትንና ውሸትን ከእኔ አርቅ፤ ድኽነትንም ሀብትንም አትስጠኝ፤ የድርሻዬ የሆነውን እንጀራ ብቻ መግበኝ፣ 9ጠግቼ ብሆን አንተን ክጄ፣ “እግዚአብሔር ማን ነው?” ልል እችላለሁ፤ ወይም ድኻ ብሆን ሰርቄ የአምላኬንም ስም ላረክስ እችላለሁ። 10ባሪያን ለጌታው አታማ፤ አለዚያ ይረግምሃል፤ አንተም በደለኛ ሆነህ ትገኛለህ። 11አባቱን የሚረግም፣ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ። 12በራሱ ዐይን ንጹሕ የሆነ፣ ዳሩ ግን ከርኵሰቱ ያልታጠበ ትውልድ አለ። 13ዐይኑ እንደ ምን የተኰፈሰ ትውልድ አለ፤ አስተያየቱም እንደ ምን የንቀት ነው! 14ጥርሱ ሰይፍ የሆነ፣ መንጋጋ ጥርሱም ቢላዋ የሆነ ትውልድ አለ፤ ድኻውን ከምድር፣ ችግረኛውንም ከሰዎች መካከል ለመብላት። 15አልቅት ሁለት ሴቶች ልጆች አሏት፤ “ስጪ” “ስጪ” የሚሉ። ፈጽሞ የማይጠግቡ ሦስት ነገሮች አሉ፤ “በቃ” የማይሉ አራት ነገሮች፦ 16መቃብር፣ መካን ማኅፀን፣ በውሃ የማይጠግብ ምድር፣ “በቃ” የማይል እሳትም። 17አባቱን የሚያፌዝ፣ እናቱንም መታዘዝ የሚንቅ ዐይን፣ የሸለቆ ቍራዎች ይነቅሉታል፤ የአሞራ ጫጩቶችም ይበሉታል። 18ለእኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፤ የማልረዳቸውም አራት ነገሮች፦ 19በሰማይ ላይ ያለው የንስር መንገድ፣ በዐለት ላይ ያለው የእባብ መንገድ፣ በባሕር መካከል ያለው የመርከብ መንገድ፣ ከወጣት ሴት ጋራ ያለው የወንድ መንገድ። 20የአመንዝራ ሴት መንገድ ይህ ነው፦ ትበላለች፤ አፍዋንም ትጠርጋለች፤ “ምንም ክፉ ነገር አላደረግሁም” ትላለች። 21ምድር በሦስት ነገር ትንቀጠቀጣለች፤ በአራት ነገርም መታገሥ አትችልም፦ 22ባሪያ ንጉሥ ሲሆን፣ ተላላም በምግብ ሲጠግብ፤ 23የተጠላች ሴት በመጨረሻ ስታገባ፣ ባሪያም ሴት እመቤትዋን ስትተካ። 24በምድር ላይ አራት ትንንሽ ነገሮች አሉ፤ ሆኖም እጅግ ጥበበኞች ናቸው፦ 25ጒንዳኖች ኀይል የሌላቸው ወገን ናቸው፤ ሆኖም ምግባቸውን በበጋ ያከማቻሉ፤ 26ሽኮኮዎች ብርቱ ያልሆኑ ወገን ናቸው፤ ሆኖም መኖሪያቸውን በዐለት ላይ ያደርጋሉ፤ 27አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ሆኖም ሁሉም በተሰለፉ ጓዶች ይገሰግሳሉ፤ 28እንሽላሊትን በእጅህ ልትይዛት ትችላለህ፤ ሆኖም በነገሥታት ቤተ መንግሥት ትገኛለች። 29በአረማመዳቸው የተዋቡ ሦስት ነገሮች አሉ፤ በጒዟቸውም የተዋቡ አራት ነገሮች፦ 30አንበሳ፣ ከአራዊት ሁሉ ብርቱ የሆነ፣ ከምንም ፊት ወደ ኋላ የማይመለስ፤ 31የሚኵራራ ዶሮ፣ ተባዕት ፍየል፣ ሠራዊቱ ከእርሱ ጋራ ያለ ንጉሥም። 32ራስህን ከፍ ከፍ በማድረግ ተላላ ብትሆን፣ ወይም ክፉ ነገር አሲረህ ከሆነ፣ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን። 33ወተትን መጭመቅ ቅቤን ያስገኛል፤ አፍንጫን መጭመቅ ደምን ያስገኛል፤ ቍጣንም መጭመቅ ጠብን ያስገኛል።