ንጉሥሽ ወደ አንቺ ይመጣል
በአህያ ላይ ተቀምጦ እልል በሚሉ ሕዝብ መካከል ይገባል፤ ከዚያም ነጋዴዎችን ከአብ ቤት ያስወጣል። ስለ ሥልጣኑ ሲጠየቅ መልስ ለመስጠት እምቢ ይላል፤ ይልቁንም አንድ ነገር ብለው ሌላ ስለሚያደርጉ ሁለት ልጆች፣ ወራሹንም ስለሚገድሉ ገበሬዎች ይናገራል።
21 1ወደ ኢየሩሳሌም ተቃርበው በደብረ ዘይት አጠገብ ወዳለችው ወደ ቤተ ፋጌ በደረሱ ጊዜ፣ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርትን አስቀድሞ ላከ፤
2እንዲህም አላቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወዲያውኑ የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደ እኔ አምጡልኝ። 3ማንም ነገር ቢላችሁ፣ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉ፤ ጌታም ወዲያውኑ ይልካቸዋል።”
4ይህ የሆነው ነቢዩ የተናገረው እንዲፈጸም ነበር፦ 5“ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤ ‘እነሆ፣ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያ ላይ፣ በጭነት አህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’”
6ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7አህያይቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሳቸውን በእንስሳቱ ላይ ጫኑ፤ ኢየሱስም በልብሶቹ ላይ ተቀመጠ። 8ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፎች ቅርንጫፎችን ቈርጠው በመንገድ ላይ አነጠፉ። 9በፊቱና በኋላው የነበሩት ሕዝብ፣ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ! በአባታችን ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር። a a v9 “ሆሳዕና” ማለት “አድነን!” ማለት የሆነ የዕብራይስጥ ጩኸት ነው፤ እዚህ ላይ የደስታ፣ የምስጋናና የአቀባበል ጩኸት ሆኖ ያገለግላል።
10ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ፣ ከተማዋ ሁሉ ተናወጠች፤ “ይህ ማን ነው?” እያሉ ጠየቁ።
11ሕዝቡም፣ “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ።
ኢየሱስ የአባቱን ቤት መልሶ ይወስዳል
12ኢየሱስም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በዚያ ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችን ገበታና የርግብ ሻጮችን ወንበር ገለበጠ።
13እንዲህም አላቸው፤ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት።”
14ዕውሮችና አንካሶች በቤተ መቅደስ ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። 15የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ያደረገውን ተአምራት፣ እንዲሁም ሕፃናቱ በቤተ መቅደስ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ!” እያሉ ሲጮኹ ባዩ ጊዜ ተቈጡ፤
16እንዲህም አሉት፤ “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህን?” ኢየሱስም፣ “አዎን፤ ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው።
17ትቷቸውም ከከተማይቱ ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ።
ተራሮችን የሚያንቀሳቅስ እምነት
18ማለዳም ወደ ከተማይቱ ሲመለስ ተራበ።
19በመንገድ ዳር የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሄደ፤ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። “ከእንግዲህ ለዘላለም ፍሬ አታፍሪ!” አላት፤ ወዲያውኑም ዛፊቱ ደረቀች።
20ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተደነቁ፤ “በለሲቱ እንዴት እንዲህ ፈጥና ደረቀች?” ብለው ጠየቁ።
21ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ሳትጠራጠሩ እምነት ቢኖራችሁ፣ በበለሲቱ ላይ የሆነውን ከማድረግ ባሻገር፣ ይህችን ተራራ እንኳ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተጣል’ ብትሏት ይሆናል። 22በጸሎትም የምትለምኑትን ሁሉ ብታምኑ ትቀበሉታላችሁ።”
የወልድ ሥልጣን ተጠየቀ
23ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሲያስተምር፣ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው፣ “እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” ብለው ጠየቁት።
24ኢየሱስም መልሶ፣ “እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ መልሱን ንገሩኝ፤ እኔም እነዚህን በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 25የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው?” እርስ በርሳቸውም እንዲህ ብለው ተነጋገሩ፤ “‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤
26‘ከሰው’ ብንል ግን፣ ሕዝቡን እንፈራለን፤ ሁሉም ዮሐንስን እንደ ነቢይ ይቈጥሩታልና።”
27ኢየሱስንም መልሰው፣ “አናውቅም” አሉት። እርሱም፣ “እኔም እነዚህን በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አለ።
ሁለት ልጆች፦ ቃል ወይስ ተግባር
28“ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ መጀመሪያው ቀርቦ፣ ‘ልጄ፣ ዛሬ ሄደህ በወይኑ አትክልት ሥራ’ አለው።” 29እርሱም፣ ‘አልሄድም’ ብሎ መለሰ፤ በኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ። 30ወደ ሁለተኛውም ሄዶ እንዲሁ አለው፤ ይህኛውም፣ ‘እሺ፣ ጌታዬ፣ እሄዳለሁ’ ብሎ መለሰ፤ ነገር ግን አልሄደም። 31“ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ የትኛው ነው?” “መጀመሪያው” አሉ። ኢየሱስም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና ጋለሞታዎች ከእናንተ ይልቅ ቀድመው ወደ አባታችን መንግሥት ይገባሉ” አላቸው።
32“ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ ወደ እናንተ መጥቶ ነበር፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም፤ ቀራጮችና ጋለሞታዎች ግን አመኑት። ይህን ካያችሁም በኋላ፣ ተጸጽታችሁ ልታምኑት አልወደዳችሁም።”
የወይኑ አትክልትና የተጣለው ልጅ
33“ሌላ ምሳሌ ስሙ፤ አንድ ባለርስት የወይን አትክልት ተከለ፤ ዙሪያውንም አጥር አደረገለት፤ በውስጡም የወይን መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ማማም ሠራ፤ ለገበሬዎችም አከራይቶ ወደ ሩቅ አገር ተጓዘ። 34የመከር ጊዜ በቀረበ ጊዜ፣ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሪያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 35ገበሬዎቹ ግን ባሪያዎቹን ያዙ፤ አንዱን ደበደቡ፣ ሌላውን ገደሉ፣ ሌላውንም በድንጋይ ወገሩ። 36ደግሞም ከፊተኞቹ የሚበዙ ሌሎች ባሪያዎችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጓቸው። 37በመጨረሻም፣ ‘ልጄን ያከብሩታል’ ብሎ ልጁን ወደ እነርሱ ላከ። 38ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፣ ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። 39ያዙትም፤ ከወይኑ አትክልት ውጭ አውጥተው ገደሉት። 40እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት በሚመጣ ጊዜ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን ያደርጋቸዋል?”
41እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉ ሰዎች በጭካኔ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየወቅቱ ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት።
42ኢየሱስም፣ “በመጻሕፍት፦ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከአባታችን ዘንድ ሆነ፤ በዓይናችንም ድንቅ ነው’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው።
43“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የአባታችን መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል። 44በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ የሚወድቅበትም ይፈጨዋል።”
45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ ተረዱ። 46ሊይዙትም ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ ቈጠሩት ፈሩ።