ኢየሱስ የሰንበት ጌታ
ሁለት የሰንበት ግጭቶች ተቃዋሚዎቹን በቍጣ ይሞሉአቸዋል። ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ወደ አብ ከጸለየ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ይሰይማል፤ ከዚያም በሜዳ ላይ ያስተምራል፦ ለድሆችና ለተራቡ ብፅዕና፣ ለጠገቡና በሰው ዘንድ ለተመሰገኑ ወዮታ፣ ለጠላት ፍቅር፣ እንዲሁም ሰምቶ የማያደርግ መሠረት እንደማይሠራ ማስጠንቀቂያ።
6 1በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእህል እርሻዎች መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት እየቀጠፉ በእጃቸው እያሹ በሉ። 2ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “በሰንበት ቀን ማድረግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ?” አሉ።
3ኢየሱስም መልሶ፣ “ዳዊት ከእርሱ ጋር የነበሩትና እርሱ በተራቡ ጊዜ ያደረገውን፣ 4ወደ አባታችን ቤት እንዴት እንደ ገባ፣ የገጸ ኅብስቱን እንጀራ ወስዶ እንደ በላ፣ ለጓደኞቹም እንደ ሰጠ፣ ይህም ከካህናት በቀር ለማንም ሊበላ ያልተፈቀደ ሲሆን፣ አላነበባችሁምን?” አላቸው። 5ከዚያም፣ “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው” አላቸው።
6በሌላም ሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች አንድ ሰው ነበረ። 7ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከሱበትን ምክንያት ለማግኘት፣ በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይከታተሉት ነበር።
8እርሱ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው፣ “ተነሥተህ በዚህ ቁም” አለው። እርሱም ተነሥቶ ቆመ። 9ኢየሱስም፣ “እኔ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት ቀን መልካም ማድረግ ወይስ ክፉ ማድረግ፣ ነፍስ ማዳን ወይስ ማጥፋት ተፈቅዷልን?” አላቸው። 10ሁሉንም ዞሮ ተመለከተና ያን ሰው፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም እንዳለው አደረገ፤ እጁም ዳነች።
11እነርሱ ግን በቍጣ ተሞልተው ኢየሱስን ምን እንደሚያደርጉት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ተመረጡ
12በዚያም ወራት ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ አባታችን ሲጸልይ አደረ። 13በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፤ ከእነርሱም ዐሥራ ሁለት መረጠ፤ ሐዋርያትም ብሎ ሰየማቸው፤ 14ጴጥሮስ ብሎ የሰየመውን ስምዖንን፣ ወንድሙንም እንድርያስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን፣ ፊልጶስንና በርተሎሜዎስን፣ 15ማቴዎስንና ቶማስን፣ የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብን፣ ቀናተኛ የተባለውንም ስምዖንን፣ 16የያዕቆብን ልጅ ይሁዳን፣ ከዳተኛም የሆነውን የአስቆሮቱን ይሁዳን መረጠ።
የአባታችን ኀይል ሕዝቡን ይፈውሳል
17ከእነርሱም ጋር ወርዶ በደልዳላ ስፍራ ቆመ፤ ከእርሱም ጋር ብዙ ደቀ መዛሙርቱና ከይሁዳ ሁሉ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከጢሮስና ከሲዶና ዳርቻ የመጡ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። 18እነርሱም እርሱን ለመስማትና ከበሽታቸው ለመፈወስ መጡ፤ በርኩሳን መናፍስት የተሠቃዩትም ዳኑ። 19ኀይል ከእርሱ ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።
20ዐይኑንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “እናንተ ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የአባታችን መንግሥት የእናንተ ናትና።
21“እናንተ አሁን የተራባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። 22ሰዎች ሲጠሏችሁ፣ ሲያገሏችሁም፣ ሲሰድቧችሁም፣ ስማችሁንም እንደ ክፉ አድርገው ሲያወግዙ፣ ስለ ሰው ልጅ ብፁዓን ናችሁ። 23በዚያ ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ዘልላችሁም ፈንድቁ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ ያሳዳጆቻችሁ አባቶች ነቢያትን እንዲሁ ያደርጉባቸው ነበርና።
24እናንተ ባለ ጠጎች ግን ወዮላችሁ፤ መጽናናታችሁን አስቀድማችሁ ተቀብላችኋልና። 25እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፤ ታዝናላችሁ ታለቅሳላችሁም። 26ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ ያሞጋሾች አባቶች ሐሰተኞችን ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።
ጠላቶቻችሁን ውደዱ
27ነገር ግን እናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፤ 28የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚያንገላቷችሁ ጸልዩ። 29ጕንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላውንም አዙርለት፤ ልብስህን ከሚወስድ ቀሚስህንም አትከልክለው። 30ከሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ያንተን ከሚወስድም መልሰህ አትጠይቅ። 31ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።
32የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ምስጋና አለላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉ። 33መልካም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን ምስጋና አለላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ይህንኑ ያደርጋሉ። 34ዳግመኛ ልትቀበሉ ተስፋ አድርጋችሁ ብታበድሩስ ምን ምስጋና አለላችሁ? ኀጢአተኞችም እኩሉን ለመመለስ ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። 35እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ሳትጠብቁ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። 36አባታችሁ መሐሪ እንደ ሆነ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ።
አትፍረዱ
37አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም። አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅርም ይባልላችኋል። 38ስጡ፤ ይሰጣችሁማል፤ ተደቅቆ፣ ተነቅንቆ፣ ተትረፍርፎ መልካም መስፈሪያ በጒያችሁ ይሰጣችኋል። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና።”
39ደግሞም ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱም ወደ ጕድጓድ አይወድቁምን? 40ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ የተሟላ ትምህርት የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። 41በወንድምህ ዐይን ያለውን ጕድፍ ስለ ምን ታያለህ፤ በገዛ ዐይንህ ያለውን ግንድ ግን ስለ ምን አትመለከትም? 42በገዛ ዐይንህ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፣ በዐይንህ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ! አስቀድመህ ከዐይንህ ግንዱን አውጣ፤ ከዚያም የወንድምህን ዐይን ጕድፍ ለማውጣት በግልጥ ታያለህ።
በፍሬያችሁ ትታወቃላችሁ
43መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ አያፈራምና፤ ክፉም ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። 44ዛፍ ሁሉ በገዛ ፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾህ በለስ አይለቀምም፤ ከኵርንችትም ወይን አይለቀምም። 45መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉው መዝገብ ክፉውን ያወጣል፤ አፍ ከልብ ሙላት ይናገራልና።
በዐለት ላይ ሥሩ
46የምለውን ሳታደርጉ ስለ ምን፣ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ? 47ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርግ ሁሉ የሚመስለውን አሳያችኋለሁ፤ 48ቈፍሮ ዐምቆ መሠረቱን በዐለት ላይ የመሠረተ ቤት የሚሠራ ሰው ይመስላል። ጎርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት መታው፤ መልካም ሆኖ ተሠርቶ ነበርና ሊያናውጠው አልቻለም። 49ቃሌን ሰምቶ የማያደርግ ግን መሠረት ሳይኖረው በመሬት ላይ ቤት እንደ ሠራ ሰው ይመስላል። ጎርፉም መታው፤ ወዲያውም ወደቀ፤ የዚያም ቤት መፍረስ ታላቅ ነበረ።”