ኢዮብ መለሰ፤ ክፉዎች ለምን ይበለጽጋሉ?
ኢዮብ ወዳጆቹ ችላ ባሉት ማስረጃ ይመልሳል። ክፉዎች እስኪያረጁ ይኖራሉ፤ ኀይለኞችም ይሆናሉ። ልጆቻቸው ይዘፍናሉ፤ እግዚአብሔርንም ተወን ካሉት በኋላ በሰላም ይሞታሉ። የጠገበውም የተመረረውም በአንድነት በዐፈር ውስጥ ይተኛሉ። መጽናናታቸው ሐሰት ነው ይላል።
21 1ኢዮብም መልሶ እንዲህ አለ፤ 2“ቃሌን በጥሞና አድምጡ፤ የምታጽናኑኝም ይህ ይሁን። 3ስናገር ታገሡኝ፤ ከተናገርሁም በኋላ ማላገጥ ትችላላችሁ። 4እኔስ ቅሬታዬ በሰው ላይ ነውን? ታዲያ ትዕግሥቴ ለምን አያልቅም? 5ተመልከቱኝ፤ ተደንግጡም፤ እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ። 6ይህን ባሰብሁ ጊዜ እደነግጣለሁ፤ ሰውነቴም በመንቀጥቀጥ ይያዛል። 7ክፉዎች ለምን በሕይወት ይኖራሉ? ለምንስ እያረጁ በኀይል ይበረታሉ? 8ልጆቻቸው በዐይናቸው ፊት ከእነርሱ ጋር ተደላድለውና ተረጋግተው ይኖራሉ፤ ዘራቸውም በፊታቸው ጸንቷል። 9ቤቶቻቸው ሰላም ናቸው፤ ከፍርሃትም ነጻ ናቸው፤ የእግዚአብሔርም በትር አይወርድባቸውም። 10ኰርማቸው ያዳቅላል እንጂ ከቶ አይጎድልም፤ ላማቸው ጥጃ ትወልዳለች እንጂ አታስወርድም። 11ታናናሾቻቸውን እንደ መንጋ ይለቅቋቸዋል፤ ልጆቻቸውም ይዘላሉ። 12ከበሮና በገና እያጀቡ ይዘምራሉ፤ በእንቢልታም ድምፅ ደስ ይላቸዋል። 13ዘመናቸውን በብልጽግና ያሳልፋሉ፤ በሰላምም ወደ መቃብር ይወርዳሉ። 14ነገር ግን እግዚአብሔርን እንዲህ ይሉታል፤ ‘ተወን! መንገድህን ማወቅ አንፈልግም። 15ሁሉን ቻዩ፣ ልናገለግለው የሚገባ ማን ነው? ብንጸልይለትስ ምን እንጠቀማለን?’ 16ነገር ግን ብልጽግናቸው በገዛ እጃቸው አይደለም፤ የክፉዎች ምክር ከእኔ የራቀ ነው። 17የክፉዎች መብራት ስንት ጊዜ ይጠፋል? ጥፋታቸውስ ስንት ጊዜ ይደርስባቸዋል? እግዚአብሔርስ በቍጣው ስንት ጊዜ ሥቃይን ያከፋፍላል? 18ስንት ጊዜስ በነፋስ ፊት እንዳለ ጭድ ይሆናሉ? ዐውሎ ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደውስ ገለባ ናቸው? 19እናንተ፣ ‘እግዚአብሔር የሰውን ቅጣት ለልጆቹ ያከማቻል’ ትላላችሁ። ይልቁንስ ለሰውዬው ራሱ ይክፈለው፤ እርሱም ያውቀው ዘንድ። 20የገዛ ዐይኖቹ ጥፋቱን ይዩ፤ የሁሉን ቻዩንም ቍጣ ይጠጣ። 21ወሮቹ ተቈርጠው ባለቁ ጊዜ፣ ከእርሱ በኋላ ስለሚቀረው ቤተ ሰቡ ምን ግድ አለው? 22ከፍ ያሉትን የሚፈርደው እርሱ ሆኖ ሳለ፣ ማንም እግዚአብሔርን ዕውቀት ሊያስተምረው ይችላልን? 23አንዱ ሙሉ ጕልበቱ ሳለ ይሞታል፤ ፍጹም ተዘልሎና ተረጋግቶ፣ 24ሰውነቱ ተመግቦ፣ የዐጥንቶቹም ቅልጥም ገና እርጥብ ሆኖ ይሞታል። 25ሌላው ደግሞ ነፍሱ መርራ ይሞታል፤ ደግ ነገርን ከቶ ሳይቀምስ። 26አብረው በዐፈር ውስጥ ይተኛሉ፤ ትልም ሁለቱንም ይሸፍናቸዋል። 27እነሆ፣ ሐሳባችሁን፣ ክፉ ልታደርጉብኝም የምትሸርቡትን ሤራ ዐውቃለሁ። 28እናንተ እንዲህ ትላላችሁና፤ ‘የተከበረው ሰው ቤት አሁን ወዴት አለ? ክፉዎች የኖሩበትስ ድንኳን የት ነው?’ 29በመንገድ የሚያልፉትን ጠይቃችሁ አታውቁምን? የሚሰጡትንስ ማስረጃ አትቀበሉምን? 30ክፉው ሰው በጥፋት ቀን ይተርፋል፤ በቍጣም ቀን ያመልጣል። 31ፊት ለፊት የሚወቅሰው ማን ነው? ስለ ሥራው ባደረገውም ነገር የሚከፍለው ማን ነው? 32ወደ መቃብር ይወሰዳል፤ በመቃብሩም ላይ ጥበቃ ይደረጋል። 33የሸለቆው ዐፈር ይጥመዋል፤ ሰው ሁሉ ይከተለዋል፤ ከእርሱ በፊት የነበሩትም ቍጥር የላቸውም። 34ታዲያ በከንቱ ቃላት እንዴት ታጽናኑኛላችሁ? መልሳችሁ ከሐሰት በቀር ሌላ ምንም አይደለም።”