አጽናኝ የሌለው እንባ
ሰባኪው አጽናኝ የሌለውን ግፍ አይቶ ሙታን ከሕያዋን ይሻላሉ ይላል። አብዛኛውን ሥራ የሚገፋው ቅንዓት ነው። ሆኖም ሁለት ከአንድ ይሻላሉ፤ ስትወድቅ የሚያነሣህ፣ የሚያሞቅህ፣ ከጎንህ ጸንቶ የሚቆም ይኖራልና። ተወዳጅ ንጉሥም እንኳ ብዙም ሳይቆይ ተፈላጊነቱን ያጣል።
4 1እንደ ገና ተመለከትሁ፤ ከፀሐይ በታች የሚፈጸመውን በደል ሁሉ አየሁ፤ የተጨቈኑት በእንባ ነበሩ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ጨቋኞቻቸው ኀይሉን ይዘው ነበር፤ አሁንም አጽናኝ አልነበራቸውም። 2ስለዚህ ቀድሞ የሞቱት ሙታን፣ ገና በሕይወት ካሉት ሕያዋን ይልቅ ደስተኞች እንደሆኑ ተናገርሁ። 3ከሁለቱም ይልቅ ገና ያልተወለደው፣ ከፀሐይ በታች የሚደረገውን ክፋት ያላየው ይሻላል። 4ድካምና ብልኀት ሁሉ ከአንዱ ባልንጀራ በሌላው ላይ ከሚቀናው ቅናት እንደሚመነጭ አየሁ። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስን እንደ መከተል ነው። 5ሞኙ እጁን አጣጥፎ ራሱን ያጠፋል። 6በጸጥታ የሆነ አንድ እፍኝ፣ በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይሻላል።
7እንደ ገና ከፀሐይ በታች ከንቱ የሆነ ነገር አየሁ፦
8ብቻውን የሆነ ሰው አለ፤ ጓደኛ፣ ልጅ ወይም ወንድም የለውም፤ ድካሙ ፍጻሜ የለውም፤ ዐይኖቹም በሀብት አይጠግቡም። “ለማን እደክማለሁ?” ብሎ ይጠይቃል፤ “ራሴንስ ከመልካም ነገር ለምን እከለክላለሁ?” ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ክፉ ድካም ነው።
9ሁለት ከአንድ ይሻላሉ፤ ለድካማቸው መልካም ዋጋ ያገኛሉና፦ 10አንዱ ቢወድቅ፣ ሌላው ያነሣዋል። ብቻውን ለሚወድቀው ግን ወዮለት፤ የሚያነሣው የለውምና። 11ደግሞም ሁለት ሆነው አብረው ቢተኙ፣ ይሞቃቸዋል። ብቻውን የሆነ ግን እንዴት ይሞቀዋል? 12ብቻውን የሆነ ይሸነፋል፤ ሁለት ሆነው ግን ይቋቋማሉ። ባለ ሦስት ፈትል ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም።
ጥበበኛው ጐበዝና ሞኙ ንጉሥ
13ድኻ ቢሆንም ጥበበኛ የሆነ ጐበዝ፣ ሽማግሌ ከሆነና ከእንግዲህ ማስጠንቀቂያን መቀበል ከማያውቅ ሞኝ ንጉሥ ይሻላል። 14ጐበዙ ሊነግሥ ከእስር ቤት ወጥቶ መጥቶ ሊሆን ይችላል፤ ወይም በዚያው መንግሥት ውስጥ ድኻ ሆኖ ተወልዶ ሊሆን ይችላል። 15ከፀሐይ በታች የሚኖሩትን ሕያዋን ሁሉ፣ የንጉሡ ምትክ የሆነውን ጐበዝ ሲከተሉ አየሁ። 16በፊቱ የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ቍጥር የላቸውም ነበር። ከኋላ የመጡት ግን በእርሱ ደስ አልተሰኙም። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስን እንደ መከተል ነው።